Connect with us

ግብጽ እና የውርደት ታሪክን ለመድገም ያለመ ሩጫዋ!!

ግብጽ እና የውርደት ታሪክን ለመድገም ያለመ ሩጫዋ!!
The Tis Abay (River Nile) falls in #Ethiopia

ባህልና ታሪክ

ግብጽ እና የውርደት ታሪክን ለመድገም ያለመ ሩጫዋ!!

ግብጽ እና የውርደት ታሪክን ለመድገም ያለመ ሩጫዋ!!
ከተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) በድሬቲዩብ

‘‘ግብፃውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፤ ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም፤ እግዚአብሔር እጁን በዘረጋ ጊዜ ረጂው ይሰነካከላል ተረጂውም ይወድቃል፣ ሁሉም በአንድ ላይ ይጠፋሉ፤’’ (ኢሳ. ፴፩፣፫)፡፡

እንደ መንደርደሪያ
ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪኳ ከውጪ ኃይላት ጋር ያደረገቻቸው ጦርነቶች ተገዳ እንጂ ወዳ፣ ፈልጋና ፈቅዳ የገባችበት አልነበረም፡፡ ከደባርቅ እስከ መቅደላ፣ ከጉራዕ እስከ ጉንደት፣ ከዶጋሊ እስከ ዐድዋ ድረስ- ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ‘እምቢ ለነጻነቴ’ በሚል ወኔ ለነጻነት፣ ለፍትሕ የተዋጉት፣ የተዋደቁት እንጂ ሌሎችን በማን አለብኝነት በግፍ የወረሩበት ጦርነት በታሪክ አልተመዘገበም፡፡

ለአብነትም ያህል ከታሪክ መዛግብት እናጣቅስ፡፡ የዐድዋ ጦርነት ከመካሄዱ በፊት ዐፄ ምኒልክና የጦር ባለሟሎቻቸው ሳይቀሩ ወራሪውን የኢጣሊያ ጦር፤ እባካችሁ የሰው ልጅ ደም በከንቱ ከሚፈስ በግፍ፣ በኃይል ከወራረችሁት፣ ከያዛችሁት መሬታችን በሰላም ልቀቁ፤ በማለት ደጋግመው ጠይቀው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ለዚህ ለኢትዮጵውያን የሰላምና የዕርቅ ልመና ጆሮ ደባ ልበስ ያሉት ኢጣሊያኖች በፈቀዱትና በወደዱት የጦርነት መንገድ በዐድዋ ግንባር አሳፋሪ ሽንፈትንና ውርደትን ነበር የተከናነቡት፡፡

አስገራሚው ነገር ከድሉ በኋላ እንኳን ዐፄ ምኒልክ ለውጪ ሀገራት በጻፉት ደብዳቤያቸው፤ ‘‘የእነዚህ ሁሉ ክርስትያን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያሰብኩ ድል አድረኩ ብዬ ደስ አይለኝም፤’’ በማለት ይህን ጦርነት እርሳቸውና ሕዝባቸው ተገደው የገበቡበት- ለፍትሕ፣ ለእውነትና ለነጻነት የተደረገ ጦርነት መሆኑን በማስረገጥ- የኢትዮጵያውያንን ላቅ ያለ ሰብአዊነትና የመንፈስ ልእልናን በዓለም መድረክ ከፍ አድርገው አሳይተውበታል፡፡

ግብጻውያን ሆይ ከታሪክ ተማሩ
ኢትዮጵያውያን በሰላምና በፍቅር መንገድ ለሚመጣ ሁሉ የዕርቅና የሰላም ሰው ናቸው፡፡ በተቃራኒው በትእቢት መንፈስ ለሚመጣ አጉራ-ዘለል ግን ደረታቸው ለጦር እግራቸውን ለጠጠር ሳይሰስቱ ለነጻነታቸው፣ ለሀገራቸው፣ ለእውነትና ለፍትሕ ወደኋላ የማይሉ ጀግኖች ሕዝቦች መሆናቸውን ግብጻውያን ዘንግተውታል፣ ወይም ሐቁን እያወቁ ባላየ ለማለፍ እየሞከሩ ነው፡፡ እናም ይህን የታሪክ እውነት መገንዘብ ያለፈለጉ የሚመስሉት ግብጻውያን ጦር አውርድ ዛቻቸውንና ማስፈራራታቸውን በሰፊው ተያይዘውታል፡፡

ከሰሞኑንም ‘‘Egypt Daily News’’ የተባለ የበይነ-መረብ ጋዜጣ የግብጹ ፕሬዚደንት፣ ጄ/ል አብዱል ፈታህ አል ሲሲ፤ ‘’የግብጽ ብሔራዊ ጦር በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ የግብጽን ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም ለማስከበር በተጠንቀቅ ላይ እንዲቆም፤’’ የሚመክር ዜናን አስነብቦናል፡፡ ግብጽ ሀገራችን ኢትዮጵያ በገዛ ወንዟ ላይ የጀመረችውን ታላቁን የኅዳሴ ግድብ የመጨረሻው ምዕራፍ መጀመሪያ የሆነውን- የውኃ ሙሌት ከቀናት በኋላ ለመጀመር ማሳወቋን ተከትሎ የተለመደውን የያዙን ልቀቁኝ ጨዋታዋን ተያይዛዋለች፡፡

ይህ ጨዋታዋ ደግሞ ሁለት መልክ ያለው ነው፡፡ ግብጽ በዓባይ ጉዳይ ላይ ቁጭ ብለን መደራደር ይኖርብናል በማለት ራሷን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለሕግ ተገዢና ሰላማዊ መሆኗን ለማሳየት ትታትራለች፡፡ ግብጽ ከዛቻና ከማስፈራሪያዋ ባሻገርም ያለ የሌለ ኃይሏን ተጠቅማ ኢትዮጵያ ከሁለት ሳምንት በኋላ የኅዳሴውን ግድብ ለመሙላት የወሰነችውን ውሳኔዋን ለማስለወጥ ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከዐረብ ሊግ ድ/ት እስከ ተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት የምትችለውን ሁሉ ሙከራ እያደረገች ነው፡፡

በሌላ ገጹ ደግሞ ግብጽ የዓባይ ውኃ ጉዳይ ከእጇ ያመለጠ መስሎ ሲሰማት ህልውናችን በሆነው በዓባይ ውኃ ጉዳይ ላይማ ድርድር ብሎ ነገር አይኖርም ዓይነት አንድምታ ያለው ወታደራዊ ማስፈራሪያና ዛቻዋን እያከታተለችው ነው፡፡

በመሠረቱ ይህ የግብጽ ዛቻ ዛሬ የጀመረ አይደለም፡፡ የግብጽ መሪ የነበሩት አንዋር ሳዳት ከእስራኤል ጋር ከገቡበት ከስድስቱ ቀናት ጦርነት መጠናቀቅ በኋላ ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግራቸው እንዲህ ብለው ነበር፤ ‘‘the only issue that could take Egypt to war again is water’’ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረክ ሰላማዊና ለሕግ ተገዢ መስለው ለመታየት የሚፈልጉት ግብጻውያን- የዓባይን ውኃ በተመለከተ በዓለም መድረክ የእንደራደር ሐሳባቸውን ቢያቀርቡም በእልፍኛቸውና በጓዳቸው ግን ሁሌም ዛቻና ማስፈራሪያ የተቀላቀለበት የጦር አውርድ ዐዋጅ ተለይቷቸው አያውቅም፡፡

ከሰሞኑንም ግብጽና ግብጻውያን ከዓለም በወታደራዊ ሳይንስ፣ በታጠቁት እጅግ በተራቀቀ ዘመናዊ የጦር መሳሪያና የሠራዊት ብዛት ተወዳዳሪ የሌላቸው መሆናቸውን የሚገልጽ ዜናን ማስነበቡን ሥራዬ ብለው ተያይዘውታል፡፡ ይህ ደግሞ መልእክቱ ለማንና ለምን እንደሆነ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን በጣሙን ግልጽ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ለግብጽና ለግብጻውያን አንድ የታሪክ ሐቅ ደግመን ደጋግመን ልንነነግራቸው ግድ ይለናል፡፡ ‘‘ከታሪክ ለመማር የማይፈልጉ ሁሉ ታሪክን ለመደገም የተፈረደባቸው ናቸው፡፡’’ የሚል የቆየ አንድ አባባል አለ፡፡ ግብጽ ከትናንትናው የውርደትና የቅሌት ታሪኳ ለመማር የፈቀደች አይመስልም፡፡ እናም ‘የጦር አውርድ’ ነጋሪት ጉሰማዋን ተያይዘዋለች፡፡ ግብጽ ይህን ፉከራዋንና ዛቻዋን ተግባራዊ ለማድረግ ብትሞክር አፀፋዊ ምላሹ ምን ሊሆን እንደሚችል ቆም ብላ የታሪክ መዛግብትን ማገላበጥ ይኖርባታል፡፡

ታሪክ እንደዘገበው ከመቶ አርባ ዓመታት ገደማ በፊት ግብጽ ኢትዮጵያን በየአቅጣጫው በመውረር የዓባይን ምንጭ ለመያዝ ያደረጉት ሙከራ ከአንዴም ሁለቴም በአሳፋሪ ሽንፈትና ውርደት ነው የተጠናቀቀው፡፡ ግብጻውያን ከመጀመሪያው የጉንደት ሽንፈታቸው በኋላም አውሮፓውያንና አሜሪካውያን ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች የጦር መሪዎች ጭምር በተሳተፉበት የጉራዕ ጦርነት የግብጽ ወራሪ ኃይል አሳፋሪ ሽንፈትን ነበር የተከናነበው፡፡

በኢትዮጵያው ንጉሥ በዐፄ ዮሐንስ የተመራው የኢትዮጵያ ጦር ከአንዴም ሁለቴ በግብጽ ላይ ያደረሰውን ሽንፈትና ውርደት በተመለከተ አሜሪካዊው ከፍተኛ መኮንን- ኮሎኔል ዊልያም ዳይ የጉንደትንና የጉራዕን ጦርነት ታሪክ በጻፈበት መጽሐፉ እንዲህ ሲል ነበር ስለጦርነቱና ስለኢትዮጵያውያን ጀግንነት ምስክርነቱን የሰጠው፤

የግብጽ መድፎችና ሮኬቶች በሚያስፈራ ቅንጅት እየተምዘገዘጉ ወደኢትዮጵያውያን የጦር ሰፈር ይበራሉ፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ርምጃቸውን ሳያጥፉ የግብጽን ጦር በጀግንነት መፋለም ያዙ … አንዳንችም ዓይነት አቤቱታ፣ አንዳንችም ዓይነት ኤሎሄ በደም የተነከረውን እጅ ሊገታው አልቻለም፡፡ በጦር ተቸክለው የተጋደሙ ወይ የሚንጠራሩ፣ እጃቸው የተቆረጠ ወይ አንገታቸው ከትከሻቸው ተቀንጥሶ ሊወድቅ የተቃረበ አካላት ድል አድራጊውን ኢትዮጵያ ጦር ማረኝ፣ ማረኝ ይላል፡፡ ግን ማን ሊሰማ፣ ጭፍጨፋውን የሚያቆም ምንም ኃይል አልነበረም፡፡ የግብጽ ጦር ተፈርዶበት ነበር፤ ከጥይቱ ቢያመልጡ፣ ከጎራዴው አያመልጡም ነበር፣ ዱላውን ሲከላከሉ ጦሩ ይቀስፋቸው ነበር፡፡

እንደ መውጫ
በርካታ የታሪክ ድርሳናት እደሚመሰክሩት ሀገራችን ኢትዮጵያ የጀግኖች ሕዝቦች መኖሪያ ምድርና የዓለማችን ታላላቅ ሃይማኖቶች ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ በመዘመኗ ሁሉ ከውጪ በግፍና በማን አለብኝነት ሊወሯት የመጡትን ጠላቶቿን ሁሉ በፈጣሪ፣ በአምላኳ ኃይልና በጀግኖች ልጆቿ የተባባረ፣ የአንድነት ክንድ ድል አድርጋ ወደመጡበት በሃፍረት መልሳቸዋለች፡፡ የዐድዋውን አሳፋሪ ሽንፈት ለመበቀል ከዐርባ ዓመት በኋላ በዘመናዊ መሳሪያ የታጠቁና የመርዝ ጭስ ጋዝ የተሸከሙ የጦር አውሮፕላኖችን ያዘመተው ፋሽስቱ ቤኒቶ ሞሶሉኒ፤ በሮማ አደባባይ ለሕዝቡ ባደረገው ንግግር እንዲህ ነበር ያለው፤
‘‘ኢጣሊያ ታላቅ ገናና ሀገር መሆኗን ኢትዮጵያና ዓለም ሁሉ ሊያውቅ ይገባል፡፡ የሮማን ታላቅነት የተገዳዳሩ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿም በታላቁና በኃያሉ ክንዴ ስር ይወድቃሉ፤ ይንበረከካሉ፡፡ ኢትዮጵያም አምላኬ የምትለው እግዚአብሔር ከኃያሉ ክንዴ ሊያድናት የሚችል ከሆነ የእኔም እግዚአብሔር ልጨምርላት እችላለሁ፡፡’’

በተመሳሳይ የፋሽስቱ የጦር መሪ የነበረው ግራዚኒያ ለአለቃው ለሞሶሉኒ እንዲህ ሲል ነበር ቃል የገባለት፤ ‘‘ኢትዮጵያን ከሕዝቦቿ ጋር በእጅ አስረክብሃለሁ፤ ካልሆነም ኢትዮጵያን አስረክብሃለሁ፡፡’’ ይህን የትእቢት ቃል የተናገረው የፋሽስት ጦር በሀገራችን ከአምስት ዓመታት የጣርና የጭንቀት ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያውን አርበኞች ክንድ ተደቁሶ በሃፍረትና በውርድት ኢትዮጵያን ለቆ ወደመጣበት ተመልሷል፡፡

ይህን የኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን አኩሪ የጀግንነት ታሪክ ዘንግተው ባከማቹት የጦር መሳሪያና የሰራዊት ብዛት ለሚኩራሩት ግብጻውያን እባካችሁ በጉራዕና በጉንደት ከሆነባችሁ አሳፋሪ ታሪካችሁ ተማሩ፡፡ በተጨማሪም የዓባይን ውኃ በፍትሐዊነት አብረን እንጠቀም፣ ዓባይ ለሁላችንም ይበቃል፣ የትብብር እንጂ የፉክክር መንፈስ አይበጀንም ላለች ሀገራችን ኢትዮጵያ፤ ‘‘የጆሮ ዝሆን ይስጠን’’ ብላ በእብሪትና በማን አለብኝነት ለምትፎክረው ግብጽና በጎኗ ለቆሙ ተባባሪዎቿ ሁሉ ይህን የቅዱስ መጽሐፍ ቃል ላስታውሳቸው እወዳለኹ፤

‘‘ግብፃውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፤ ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም፤ እግዚአብሔር እጁን በዘረጋ ጊዜ ረጂው ይሰነካከላል ተረጂውም ይወድቃል፣ ሁሉም በአንድ ላይ ይጠፋሉ፡፡’’ (ኢሳ. ፴፩፣፫)፡፡

ሰላም!!

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top