ሃጫሉ ምንድነው ያለው? | (ዮሐንስ መኮንን)
አርቲስት ሃጫሉ ሑንዴሳ ከኦ ኤም ኤን ጋር በኦሮምኛ ያደረገውን ቃለመጠይቅ አደመጥኩት። የአርቲስቱን ቃለመጠይቅ ዋና ዋና ሀሳቦች ኦሮምኛ ለማይሰሙ ወገኖች መልእክቱ እንዲደርስ ምንም ዓይነት የራሴን አስተያየት ሳልጨምርበት ዋና ዋና አሳቦቹን ብቻ ላጋራችሁ።
• ወያኔዎች (እነ ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት) Offer አቅርበውልኝ ነበር። ደኅንነቶች ቤት እና መኪና (እንድመርጥ) አሳይተውኝ እምቢ ብያለሁ፤
• አሁን ብረት እየነገድኩ ያለሁት የኦሮሚያ ባንክ ሥራ አስኪያጅ 10,000,000 (አሥር ሚሊዮን) ብር አበድሮኝ ነው።
• አሁን ኦሮሞን እየጨቆነ ያለው ኦሮሞ ነው፤
• ዶ/ር ዐብይ አንድም የኦሮሞን ጥያቄ አልመለሰም። የኦሮሞን ሥነ ልቡና አልጠበቀም፤
• በወያኔ ዘመን ኦሮሞ ሲገደል ቢያንስ ይሰማ ነበር። አሁን አይሰማም። ምክንያቱም የሚገድሉን ሰዎቹ አይደሉም። እኛው ነን የምንጋደለው፤
• ነፍጠኞች ድሮ የኦሮሞ ጠላት ነበሩ። ዛሬም የኦሮሞ ጠላት ናቸው። ወደፊትም የኦሮሞ ጠላት ናቸው፤
• TPLF ጭራዋን የትግራይ ህዝብ ውስጥ ሸጉጣ ስትፈጀን ነበር። ነፍጠኞች ጭራቸውን የአማራ ህዝብ ውስጥ ሸጉጠው ሲፈጁን ነበር። መንግሥቱ ኃይለማርያም ብቻ ነው ጭራውን አግድም የሸጎጠው፤
• ከአሁን በኋላ ማንም ሰው ከየትኛውም ብሔር መጥቶ ሥልጣን ላይ ሊቀመጥ ይችላል። ነገር ግን ሥልጣን ላይ እንዲቆይ ማድረግ የሚችለው ኦሮሞ ነው። ሥልጣን ላይም እንዳይቆይ ማድረግ የሚችለው ኦሮሞ ብቻ ነው፤
• በዶክተር ዐብይ ዘመን ኦሮሞ ተጠቅሟል። የተጠቀመው የነፍጠኞችን ስድብ ነው፤
• ዶ/ር ዐብይ ጦር አዝምቶ ጃዋርን እንዲገድለው፣ አንድ የኦሮሞ ምሁር እንዲገድል ነፍጠኞች ሌት ተቀን እየሠሩ ነው፤
• ይኼ ምኒልክ የተቀመጠበት ፈረስ (ጊዮርጊስ ያለው ሀውልት) የተሠረቀ ፈረስ ነው። ገላን አካባቢ ከሚኖር ሲዳ ደበሌ ከተባለ ገበሬ ነው የተሠረቀው።
• ዛሬም ይኼንን ፈረስ ሳየው እናደዳለሁ። የተሠረቀብን ፈረስ ነው። አስፈላጊ ከሆነ ይህ ትውልድ የተሰረቀውን ፈረስ ሊጠይቅ ይችላል፤
• ምኒልክ ወደ ኦሮሚያ ሲመጣ በአህያ ላይ ተቀምጦ ነበር የመጣው። … ፈረስ ላይ መቀመጥ የት ያውቅበትና ነው?
• ምናልባት ሰው እየጎተተለት ፈረስ ላይ ተቀምጦ ይሆናል። ዛሬም በየዓመቱ የዓድዋን ድል እናከብራለን የሚሉ ሰዎች ፈረስ ላይ እንደንጉሱ አስቀምጠው ሌሎች ፈረሱን ሲጎትቱላቸው አያለሁ።
• ፈረሱ ለባለቤቱ ሊመለስ ይገባል። ይህ የማይቀር ጉዳይ ነው።
• ምኒልክ ጨካኝ ወንጀለኛ ነው። ክፉ ቢሆን አይደለም እንዴ የአርሶ አደር ፈረስ የሚሠርቀው ?
• የህዝብ ንጹህ ደም በእጁ ላይ ያለበትን ሰው ሀውልቱን እንዴት ከቤትህ አጠገብ (ቤተመንግሥት) ታቆማለህ?
————————-
የእኔ ሀሳብ!
ስለትናንትናችን ቆመን ስንላቀስ ዛሬአቸውን በአግባቡ የሚጠቀሙ አስተዋዮች ነገአችንን ደግመው ይቀሙናል!