የፍትህ መዶሻ ይዛ ፍትህ የምትጠይቅ ሀገር
(አለማየሁ ገበየሁ ~ እንግሊዝ)
ኢትዮጵያ አይኗን በጨው ካጠበችው ግብፅና አይኗን በአግባቡ መታጠብ ካቃታት ሱዳን ጋር እሰጥ አገባ ከገባች አመታትን አስቆጠረች ። ድርድሩ የፓለቲካውና ዲፕሎማሲውን መንገድ ይከተል በሚል እንጂ በጉንጭ አልፋው ንግግር ውጤት ይገኛል ተብሎ አይጠበቅም ።
ፈጣጣዋ ግብፅ የቅኝ ግዛቶችን ውል ከትከሻዋ ላይ ማውረድ አትፈልግም ። ከግፈኛዋ እንግሊዝ የተቀበለችውን የውሃ ድርሻ እንደ ጄነራል ክፍ አድርጎታል ። ይህን ማእረግ ወደ ሻምበልነት የሚያወርድ ተጋፊ ሃይልን አትቀበልም ። እናም በእሷ ቀመር የውሃው ባለቤትነት የሚመዘነው ከሚመነጭበት ቦታ ሳይሆን በተፈጥሮ ቀድሞ በያዘ ነው – ላለው ይጨመርለታል የሚባለውን የወንጌል ጥቅስ እንድናስታውስ በማድረግ ።
ሱዳን ከቅኝ ገዢዋ መሃንዲስ የሚበቃትን ያህል ድርሻ ተቀብላለች ። የአባይ ወንዝና የግድቡ ወሬ ሲነሳ የምታዳምጠው አይናር የማይጠፋውን አይኗን እየሞዥቀች ነው ። አይናሩ ሲለቃት ግድቡ ይጠቅመኛል ከኢትዮጽያ ጎን ነኝ ትላለች ። አይናሩ አንቆ ሲይዛት የግብጽ ማስፈራሪያ ነው ቀድሞ የሚሰማት ። ያኔ ግብፅን በአረብኛ ማናገር ትጀምራለች – አቋም እንዲኖራት አትፈልግም ።
እነዚህ ሀገሮች ከያዙት ህገወጥ ጥቅምም ሆነ ከሚያስተሳስራቸው ፖለቲካዊ ውግንና አንጻር ወደ መሃል ተስበው የሚመጡ አይደሉም ። ወደታች ወርደው የእውነት ባልጩት ላይ ከቆሙ ድንጋዩ ያበቀለው አልጌ አዳልጦ እንደሚጥላቸው ይረዳሉ ። የሚደራደሩት አዲሱን እውነት ለመቀበልና የቆየውን ክብር ለማጣት አይደለም ።
ለዚያም ነው በተለይ ግብፅ ከድርድር ይልቅ አደራዳሪን ምርኩዝ ማድረግ የምትመርጠው ። ለቡራኬ ሰጪዎች ትልቅ ቦታ አላት ። ድሮ ለዚህ ያበቃቻት እንግሊዝ ዛሬ ባትጠቅማትም አሜሪካንን መተካት አላቃታትም ። ትላልቆቹ በስሟ እንዲያስፈራሩላትና የረባሽ ሀገራትን ጆሮ እንዲቆነጥጡላት ትፈልጋለች ። የያዘችው እውነት ለዛሬው አለም ባይሰራም አይኗን አፍጣ አለም መንግስታት ፊት ስሞታ ታቀርባለች ። ጩኸቷን እንዲጮሁላት አጥብቃ ነው የምትሰራው ። አልፋም ትሄዳለች – ሁሉንም አማራጮች እጠቀማለሁ የሚል ማስፈራሪያ በመልቀቅ ።
እንደሚታወቀው የውሃው መነሻም ሆነ የግድቡ መድረሻ ከኢትዮጵያ ነው ወይም ኢትዮጵያ ናት ። በውሃ የመጠቀም አለማቀፋዊ መብቷ ጥያቄ ውስጥ ባይገባም የምትደራደረው ግን በድርድር ተጎጂልን ከሚሏት ፈጣጣ ሀገራት ጋ ነው ። ድርድሩን አለም ይውቅልኝ ፣ ፍትሃዊነቱንም ይገንዘብልኝ የምትለው የሌሎችም አጋር መሆናን ለማሳየት ነው ። ሀገሬ ግን ነገ ጠባ እየከሰሷት ፣ አለፍ ሲልም እያስፈራሯት ፍትሃዊ አካሄዴ ይታወቅልኝ በሚል ባዘነች።
እንደ እውነቱ ከሆነ ግድቡን ለመስራትም ሆነ ውሃውን ለመሙላት የማንንም ፍቃድ መጠየቅ አያስፈልግም ። መጠንቀቅ ያለብን ሌሎችን በጭፍን ጥላቻ ላለመጉዳታችን ብቻ ነው ። ከዚያ ውጪ ወንዙም ግድቡም የኛ ነው ። በያዝነው ነገር ላይ መያዛችንን ከማይቀበል ቡድን ጋር ለምን ሃይላችንን እናጠፋለን ? ብለህ ብለህ አልቀበል ካለህ የያዝከውን አስተማማኝ የፍትህ መዶሻ በራስህ ጠረጼዛ ላይ መምታት ተገቢ ነው ። ከዚያ ለፍርድ አፈጻጸም ወደሚመለከተው አካል በየአድራሻው መላክ – ይኸው ነው ። ውሃውን መሙላት ስትጀምር ትላንት አልቀበል ያለህ ሁሉ ሰልፉን ካንተ ጋ ያሳምራል ፤ ቋንቋውንም ይለውጣል ። ዋ ! የሚልህን ረስቶ ‹ እባክህ › ማለት ይጀምራል ። አለም የምታሳየን እውነት ይሄንን ነው ። ከወሬው ቀንሰን ይህን ለማድረግ እንፍጠን ። ያኔ የመታኸው መዶሻ ጠብቆ መግባቱን ቢያንስ ቢያንስ ደግሞ ትክክል መሆኑን ትገነዘባለህ ።
በርግጥ ሌሎችን ተደግፎም ሆነ በራሱ የሚያስፈራራው ቡድን ምንም አያመጣም ብሎ መዘናጋት ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል ። ግልጽ ጦርነት ባይከፍትብህ እንኳ ሌሎችን በገንዘብ በመግዛት ጥቅምህን ለመናድ ሌት ተቀን ይሰራል ። ሱዳን እና የኛ ሀገር ባንዳዎችን በዋናነት እንደሚጠቀም መጠራጠር አይኖርብንም ። ግድቡ ድንበር ላይ እንዲሰራ መደረጉ ምናልባት የሚጎዳንም በዚህ መሰሉ አጣብቂኝ ግዜ ነው ። እናም በአንድ በኩል ግድቡን ለመጨረስ እየተጉ በሌላ በኩል ግድቡንና አካባቢውን በአስተማማኝ መከላከያ ማጠር ያስፈልጋል ። የሀገር ቤቶችን ባንዳዎች እግር በእግር ተከታትሎ ግባቸውን ለማጨናገፍ ፣ የጆሮ ጠቢውን መስሪያ ቤት ሚና ከመቼውም ግዜ በላቀ መልኩ ማሳደግ ተመራጭ ይሆናል ።