Connect with us

«በሰው ልጅ አፈጣጠር እደነቃለሁ»- የፊልም ባለሙያ ናርዶስ አዳነ

«በሰው ልጅ አፈጣጠር እደነቃለሁ»- የፊልም ባለሙያ ናርዶስ አዳነ
Photo: Social Media

መዝናኛ

«በሰው ልጅ አፈጣጠር እደነቃለሁ»- የፊልም ባለሙያ ናርዶስ አዳነ

በለምለሚቷ ዲላ ተወልዳ አዲስ አበባን መኖሪያዋ አድርጋለች። ውቢቷ ሀዋሳም ፍቅር መግባ አሳድጋታለች። ምን በልጅነቷ የእግር ኳስ ጨዋታን ታዘወትር ነበር። እግር ኳስ ተጫዋች መሆንን የተመኘችበት ወቅትም ነበር ያኔ ባፍላነት ዕድሜዋ። ስታድግ የህክምና ዶክተር ሆና ወገኖቿን የመረዳት ፅኑ ምኞት ነበራት። የሰጧትን የሚቀበል ብሩህ አዕምሮ የታደለች ንቁ ልጅ ነበረች። በትምህርት ቤት ቆይታዋ እጅግ በጣም ጥሩ ውጤት ከሚያስመዘግቡ የደረጃ ተማሪዎች ተርታም ነበረች። ኋላ ላይ የግል ጉዳይ ትምህርቱን እንድታቋርጥ ቢያደርጋትም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት መከታተል ጀምራ ነበር።

ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በማርኬቲንግ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቃለች። ሀዋሳ እያለች ሰንበት ትምህርት ቤት ላይ አዘውትራ እንቅስቃሴ ታደርግበት የነበረው የኪነ ጥበብ ክፍል የዛሬ ማረፊያ ሙያዋ መነሻ፤ ወደ ፊልም ሥራ ለመግባት መቅረቢያ ሆናት። ከ10 ያላነሱ አማርኛ ፊልሞች፣ የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎች ላይ የተሰጣትን ገፀ ባህሪይ በብቃት በመተወን በተመልካቾች ዘንድ ታላቅ አክብሮት፣ እውቅናና ዝናን አትርፋለች። የሥራ ባልደረቦቿ ተግባቢና አመለ ሸጋ መሆኗን የሚነግሩላት ይህቺ ወጣት ተዋናይ የዓመቱ ምርጥ ተዋናይ በመሆን በዕጩነት የቀረበችበት ጊዜም አለ። በተለያዩ ማስታወቂያ ሥራዎች ላይም ተሳትፋለች።

አንድ ወቅት ሀዋሳ በተካሄደ የቁንጅና ውድድር በማሸነፍ «ወይዘሪት ሀዋሳ» በመባል የቁንጅና አክሊል ደፍታለች ተዋናይት ናርዶስ አዳነ። አሁን ላይ በኢትዮጵያ በፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ወጣትና ስመ ጥር ከሆኑ ተወዳጅና ዝነኛዋ ናርዶስ አዳነ ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራት ቆይታ የእረፍት ጊዜ የትና በምን? እንዴትና ከማን ጋር ታሳልፋለች? ማህበራዊና ቤተሰባዊ ሕይወቷ ምን እንደሚመስል? ጠይቀን ከእርሷ ያገኘነውን ምላሽ በሚከተለው መልክ አሰናድተን አቅርበነዋል መልካም ንባብ።

ማህበራዊ ተሳትፎ

በሥራና በልዩ ልዩ አጋጣሚ የምታገኛቸው ሰዎች ጋር በአጭር ጊዜ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያለው ወዳጅ ያህል በቀላሉ የመግባባት ችሎታ አላት። ከሰርግና ልዩ ልዩ ድግሶች ጥሪ ይልቅ የታመመን በመጠየቅና የተቸገረን ስትችል ባቅምዋ ካለፈም በሃሳብ ቀርቦ ችግሩን መካፈል ውስጣዊ ሰላሟን ከፍ ያደርግላታል።

የእረፍት ጊዜ

“የእረፍት ጊዜዬን እረፍት የሚሰጡኝ ቦታዎች ላይ መገኘትን አዘወትራለሁ።” ትላለች። ከማህበራዊ ጉዳይና ቤተሰብ ጥየቃ የሚተርፈው የእረፍት ጊዜዋ ቤተ ክርሲቲያን ሄዳ ሃይማኖታዊ አምልኮን መፈፀምና መፅሀፍ ቅዱስ ማንበብ፣ እቤት ስትሆን መፅሀፍትን ማንበብና ፊልሞችን ማየት የሚያስደስትዋት ሰላምም የሚሰጡኝ መገኛዎቼ ናቸው በማለት ትገልፃለች።

ከሙያዋ ጋር የተገናኙ ፅሁፎችን ማንበብ፣በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረግ፣ ከቤተሰብና ከጓደኞችዋ ጋር ቤት ውስጥ ልዩ ድባብ በመፍጠር የማይረሳ አስደሳች የዕረፍት ቀን ታሳልፋለች። ለመዝናኛ የምትገኝባቸው ቦታዎችን ትመርጣለች።

የማህበረሰቡን ባህል በጠበቀ መልኩ የተዘጋጁ ቀለል ያሉ አለባሳትን ትመርጣለች። በእረፍት ሰዓትዋ ምቾት ያለው (እስኒከር) ጫማ በትሸርት መልበስ ያስደስታታል።ወቅታዊ ፋሽን እየተከታተሉ መዘነጥ ብዙም አያስደስታትም። ናርዶስ ጋር በስራ አጋጣሚ አልያም ተወዳጅተው ቀርበው ገበታ አብረው ቢቀርቡ እራሷ የምታዘው ምግብ ሽሮ ሊሆን እንደሚችል ፈፅሞ አይጠርጥሩ። ምክንያቱም ናርዶስ እጅግ የምትወደው የምግብ አይነት ስለሆነ።

ተፈጥሯዊ ነገሮች እጅግ የሚመስጥዋት ናርዶስ አምላክ ምድር ላይ ካስገኛቸው ፍጥረቶቹ የሰው ልጅ አፈጣጠር እጅግ የሚያስደንቃት መሆኑን ትናገራለች። አምላክ የሰው ልጅን ወይም ይሄን አስደነቂ ፍጡር እንዴት ድንቅ አድርጎ እንደፈጠረው ደጋግሜ አስባለሁ በማለት በሰው ልጅ ልዩ አፈጣጠር መደነቅዋን ትገልፃለች።

የአርቲስትዋ መልዕክት

“ከምንግዜም በላይ አብሮነት፣ አንድነትና ህብረት የሚያስፈልገን ሰዓት አሁን ነው። ከመጣው መጥፎ አጋጣሚ ፈጣሪ እንዲረዳን እኛ ቀድመን የእርስ በእርስ መዋደድና የአብሮ መቆም እሴታችንን ማጠንከር ይገባናል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ እራሱንና ወገኑን ከበሽታው ጠብቆ በመረዳዳት ይህን ክፉ ጊዜ አብሮ እንዲሻገር አደራዬ ነው።” ከወጣትዋ ተወዳጅ የማስታወቂያና የፊልም ባለሙያዋ ናርዶስ አዳነ ጋር ያደረግነው አጭር ቆይታ በዚህ መልክ ቋጨነው ።ቸር እንሰንብት።

አዲስ ዘመን ግንቦት 23/20

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in መዝናኛ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top