Connect with us

የህዳሴ ግድብ እንደዘንድሮ በሙሉ አቅም የተሰራበት ጊዜ እንደሌለ ተገለጸ

የህዳሴ ግድብ እንደዘንድሮ በሙሉ አቅም የተሰራበት ጊዜ እንደሌለ ተገለጸ
Photo: EPA

ኢኮኖሚ

የህዳሴ ግድብ እንደዘንድሮ በሙሉ አቅም የተሰራበት ጊዜ እንደሌለ ተገለጸ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከተጀመረ አንስቶ የተከናወኑ ሥራዎች ሲመዘኑ በ2012 ዓ.ም የላቀ ሥራ መሰራቱን

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ አስታወቁ ።

የግድቡ ግንባታ በሁሉም መስክ የተሳካ የሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝም አመለከቱ ።

ሥራ አስኪያጁ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ፣ ፕሮጀክቱ በሙሉ አቅም በሁሉም አቅጣጫ በሶስት ሽፍት እየተሰራ ነው ። የግድቡ የሲቪል ኢንጅነሪንግ ሥራው 87 በመቶ ፣የብረታ ብረት ሥራዎቹ ደግሞ ከ 31 በመቶ በላይ ፤ የኤሌክትሮ ሜካኒካል የተርባይንና የጀነሬተር ሥራዎች አፈጻጸምም 45 በመቶ ፤ አጠቃላይ የፕሮጀክቱን አፈጻጸም ደግሞ 74 በመቶ ደርሷል።

ከዚህ ቀደም ችግር የነበረባቸው የቅድመ ሀይል ማመንጫ የብረታ ብረት ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ተነስተው በአዲስ መተካታቸውን ያመለከቱት ሥራ አስኪያጁ፤ የግድቡ የግርጌ የውሃ ማስተንፈሻ (የቦተም አውትሌት) እንዲሁም ከቅድመ ሀይል ማመንጨት ጋር የተገናኙ የሁለት ጀነሬተር ተርባይን ሥራዎች ተጠናቅቆ በኮንክሪት እየተሞሉ መሆኑን አብራርተዋል።

የ 11 ቀሪ ዩኒቶች የብረታ ብረት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተው ፣ ሌሎች ለሲቪል ኮንትራክተሮች የተሰጡ ሥራዎች ደግሞ በቅርቡ እንደሚጀመሩ አስታውቀዋል። ለሁለቱ ቅድመ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የሚሆን የብረታ ብረት ሥራዎች ተከናውነው ኮንክሪት እየተሞሉ መሆኑን ጠቁመዋል። በቀጣይም የጀነሬተር ተርባይን ተከላ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

በግድቡ በተለይም የመካከለኛው ውሃ ይፈስበት የነበረው ቦታ ርዝመቱ 525 ሜትር የነበረ ሲሆን፤ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ 560 ሜትር ለማድረስ ከፍተኛ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ ጎንና ጎኖቹም በኮንክሪት እየተሞሉ መሆኑን አስታውቀዋል ። የግድቡ ሥራ ከተጀመረ አንስቶ እንደዚህ ዓመት በሁሉም አቅጣጫ በሙሉ አቅም የተሰራበት ጊዜ አለመኖሩን ጨምረው ተናግረዋል።

የግድቡ ግንባታ በሁሉም መስክ የተሳካ የሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያመለከቱት ኢንጅነር ክፍሌ፣ በኤሌክትሮ ሜካኒካሉም፣ በሲቪሉም፣ በብረታ ብረት ሥራውም በሶስት ሽፍት ያለ እረፍት እየተሰራ ነው፤ ይህም በጣም አስደሳችና እስከ ዛሬ ያልተሰራበት አካሄድ ነው›› ብለዋል።

‹‹በዚህ ዓመት ውሃ ሙሌቱ ይጀመራል ስላልን ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ ያለው የግድቡ ሥራ አፈጻጸም በራሱ የውሃ ሙሌት እንዲጀመር አስገዳጅ ነው›› ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹የመካከለኛውን የግድቡን ክፍል ከ 525 ወደ 560 ሜትር ከፍ እያደረግን ስለምንሄድ ውሃ ሙሌቱ ያስፈልጋል፤ በዚህም 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትር ኩዩብ ውሃ እንይዛለን። በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ሁሉም ነገር ተስተካክሎልን ከሰራን ወደ 590 ሜትር ስለምናደርሰው ውሃ የመያዝ አቅማችን 16 ነጥብ 5 ሜትር ኩዩብ ይሆናል›› ብለዋል።

ሥራ አስኪያጁ “በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ውሃ መያዝ አትችልም ከተባለ የሚፈጠረው ነገር የግድቡን ሥራ ማቆም ነው፤ ምክንያቱም 560 ሜትር ከተደረሰ በኋላ ስትራክቸሩ በጣም ትልቅ በመሆኑ ግንባታው በምንና እንዴት እንደሚነሳ ማሰብ ይከብዳል፤ ከዚህ አንጻር የውሃውን ሙሌት የሚያመጣው የሥራው አስገዳጅነት ነው” ብለዋል።
የታላቁን ግዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም አሁን ላይ 74 በመቶ ማድረስ ተችሏል ።

አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2012

Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top