Connect with us

ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ በገዥው ፓርቲ ላይ መረር ያለ መግለጫ አወጣ

ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (#ኢዜማ) በገዥው ፓርቲ ላይ መረር ያለ መግለጫ አወጣ
Photo: Facebook

ፓለቲካ

ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ በገዥው ፓርቲ ላይ መረር ያለ መግለጫ አወጣ

ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (#ኢዜማ) በገዥው ፓርቲ ላይ መረር ያለ መግለጫ አወጣ

አንኳር ነጥቦች
– ዘላቂ ውጤት ያላቸውን ሥራዎች የሕዝብ ፈቃድ ያላገኘ አስተዳደር የሕዝብ ፍላጎት ሳይታወቅ በዚህ የሽግግር ወቅት ሊተገብር እንደማይገባ በፅኑ እናምናለን።

– ገዢው ፓርቲ በደቡብ ክልል የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያዘጋጀው የክላስተር አወቃቀር/ምደባ አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሰት ሕገ ወጥ የሆነ፣ ደቡብ ክልል ሲዋቀር የተሠራውን ስህተት በመድገም ተመሣሣይ ችግርን በአንድ ዓይነት መፍትሄ ለመቅረፍ ደግሞ የሚሞክር (የትልቁን ደቡብ ችግር ትንንሽ ደቡቦች በመፍጠር ለመፍታት)፣ ከባለፈው ችግር ትምህርት ያልወሰደ ሂደት ነው።

– በዚህ ከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እና ጥንቃቄ በሚፈልግ ወቅት በደቡብ ክልል ራስን በራስ ለማስተዳደር የቀረቡ ግልጽ ጥያቄዎችን በፍፁም መመለስ የማይችል፣ ለችግሩ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኝት ዓላማ ያደረገ ጥረት አመፅ እና ብጥብጥ ለማንሳት ለሚሞክሩ ኃይሎች ስንቅ እንደማቀበል የሚቆጠር ነው።

– ከኅብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ቀጥተኛ እና ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ሲገባ ጊዜያዊ እና የሕዝቡን ጥያቄ የማይፈቱ አማራጮችን በማቅረብ የሕዝብን እውነተኛ የፍትህ እና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ማፈን ተገቢ አይደለም።

– ገዢው ፓርቲ ከሕግ አግባባ ውጪ በሆነ የመብት ሰጪ እና ነሺነት የሕዝብን ተቀባይነት ለማግኘት የሚያደርገውን ሩጫ በአስቸኳይ እንዲያቆም ኢዜማ አጥብቆ ያሳስባል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በዚህ ምክንያት በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ለሚደርስ እያንዳንዱ ጉዳት ቀጥተኛ ተጠያቂ በራሱ ተነሳሽነት ጉዳዩን እየገፋ ያለው ገዢው ፓርቲ እንደሚሆን በግልፅ መታወቅ አለበት።

ራስን በራስ የማሰተዳደር ጥያቄ መሰረታዊ፣ የምንደግፈው እና ተግባራዊ እንዲሆን የምንታገልለት ጥያቄ ነው!

ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከረጅም ጊዜ የአምባገነን ሥርዓቶች መፈራረቅ እና ሥርዓቶቹን አስወግዶ ሕዝብን እውነተኛ የሥልጣን ባለቤት ለማድረግ ከተደረገ የብዙዎችን መስዕዋትነት የጠየቀ ትግል በኋላ ወደእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር ለማደርግ የሚያስችል ዕድል ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት አግኝታለች። ለ27 ዓመታት ሀገራችንን ዘውግን መሰረት ባደረገ አምባገነናዊ ፖለቲካዊ ሥርዓት ሲመራ የነበረው አገዛዝ ውስጥ የነበሩ የለውጥ አይቀሬነትን የተረዱ ግለሰቦች ለረጅም ጊዜ ሲደረግ የነበረውን ትግል በተወሰነ ደረጃ አግዘው ሥልጣን መያዛቸው የሚታወስ ነው። እነዚህ ኃይሎች ሥልጣን ላይ ከመውጣታቸው በፊት ለተፈፀሙ ጥፋቶች ይቅርታ ጠይቀው ሀገራችን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር ማድረግ እንዳለባት እንደሚያምኑ እና ይህንንም ሽግግር ጠንካራ መደላድል ላይ ለማስቀመጥ ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ እስከሚደረግ ድረስ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚጠቅሙ የመንግሥት ተቋማት ጠንካራ እና ገለልተኛ ሆነው እንዲዋቀሩ እንዲሁም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ማነቆ የሆኑ የፖለቲካ ምህዳሩን ያጠበቡ ሕጎችን እና አሠራሮችን ለመቀየር (ለማሻሻል) ቃል ገብተው ነበር።

ሥርዓቱን ለመቀየር ትግል ሲያደርግ እና መስዕዋትነት ሲከፍል የነበረው ሕዝብ እና አብዛኞቹ የፖለቲካ ኃይሎችም ይህንን ዕድል በአጭር ጊዜ የፖለቲካ ስሌት ከማየት ይልቅ ሥልጣን ላይ የወጣው ኃይል ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገውን ሽግግር የሚያግዙ ሥራዎች ለመሥራት ቃል እስከገባ እና ይህንን ቃል የሚጠብቅ እስከሆነ ድረስ በረጅም ጊዜ ቀስ በቀስ የሚገነባ ሀገራዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ከፉክክር ውጪ በሆነ መልኩ ማገዝ እንደሚያስፈልግ አምኖ ምንም እንኳን ሥልጣን የያዙት ከሕዝብ ውክልና ውጪ ቢሆንም እስከ ምርጫው ድረስ ሥልጣን ላይ እንዲቆዩ ዕድል መስጠትን መርጧል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)ም ከተመሰረተ ጀምሮ ለሀገር መረጋጋት እና ሰላም ቅድሚያ በመስጠት የፉክክር ጉዳዮችን ምርጫው ለሚደረግበት ጊዜ አቆይቶ ለሁላችንም የሚበጀውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ከሚፈልጉ አካላት ሁሉ ጋር በትብብር መንፈስ ሲሠራ ቆይቷል። በኢዜማ ዕምነት ቀጣዩ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ያለው የሽግግር ወቅት በዋነኛነት ሀገርን ለማረጋጋት እና ምርጫውን ነፃ እና ፍትሃዊ ለማድረግ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች ማከናወኛ ነው። ዘላቂ ውጤት ያላቸውን ሥራዎች የሕዝብ ፈቃድ ያላገኘ አስተዳደር የሕዝብ ፍላጎት ሳይታወቅ በዚህ የሽግግር ወቅት ሊተገብር እንደማይገባ በፅኑ እናምናለን።

የኮቪድ-19 ወረርሺኝ መከሰትን ተከትሎ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ እንደማይችል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ካሳወቀ በኋላ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ባስቀመጠው የአምስት ዓመት ገደብ ውስጥ ምርጫው መደረግ ስላልቻለ ምርጫ ተደርጎ የሕዝብ ውክልና ያለው መንግሥት እስኪኖር ድረስ ሀገራችንን ማን ያስተዳድር የሚል ጥያቄ መነሳቱ ይታወሳል።

ይህን ጥያቄ ተከትሎ ከነበሩት አማራጮች መካከል በድንገተኛ እና ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ማድረግ ሳይቻል ሲቀር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የራሱን እና የአስፈጻሚውን አካል ሥልጣን የዜጎችን ደህንነት፣ የሀገር ሉዓላዊነትን እና ምርጫውን ነፃ እና ፍትሃዊ ከማድረግ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ብቻ ገድቦ ምርጫውን እስከ አንድ ዓመት ለሚደርስ ጊዜ ማራዘም የሚያስችለውን ሥልጣን ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል እንዲሰጠው ምክረ ሀሳብ አቅርበን ነበር። ነገር ግን መንግሥት በወሰደው የሕገ መንግሥት ትርጉም አማራጭ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ያቀረበለት ምክረ ሀሳብ ላይ ተመስርቶ የኢፌዴሪ ፌደሬሽን ምክር ቤት ምርጫው የሚካሄድበትን ጊዜም ሆነ የመንግሥትን ሥልጣን ያልገደበ ውሳኔ አሳልፏል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት ምርጫው የሚካሄድበትን ጊዜ በወረርሺኙ ምክንያት ክፍት አድርጎ የተወው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወረርሺኙ ባይጠፋም እንኳን በተጨማሪ ጥንቃቄ፣ ጊዜ እና በጀት ምርጫውን ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ (Scenario) እንዳለ ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ከገለፀ በኋላ እና ምርጫው ያለገደብ እንዲራዘም የመጨረሻ ውሳኔ የሰጡት የምክር ቤቱ አብዛኛዎቹ አባላት «ምርጫው በቶሎ እንዲካሄድ እፈልጋለሁ» ብሎ በይፋ የተናገረው ገዢ ፓርቲ አባል መሆናቸው ውሳኔው የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን ግልፅ ያልሆነ ዓላማ እንዳነገበም እንድንጠራጠር አድርጎናል።

ይህ የ«ሕገ መንግሥት ትርጉም» ለመንግሥት ያልተገደበ ሥልጣን በሰጠ ማግስት በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኙ ዞኖች ካነሱት ራስን በራስ ማስተዳደር ጥያቄ ጋር ተያይዞ መንግሥት አስጠናሁ ያለውን ክልሉን ወደ አምስት የሚከፍል ምክረ ሀሳብ ለመትገበር እንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ ተረድተናል።

ገዢው ፓርቲ በደቡብ ክልል የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያዘጋጀው የክላስተር አወቃቀር/ምደባ አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሰት ሕገ ወጥ የሆነ፣ ደቡብ ክልል ሲዋቀር የተሠራውን ስህተት በመድገም ተመሣሣይ ችግርን በአንድ ዓይነት መፍትሄ ለመቅረፍ ደግሞ የሚሞክር (የትልቁን ደቡብ ችግር ትንንሽ ደቡቦች በመፍጠር ለመፍታት)፣ ከባለፈው ችግር ትምህርት ያልወሰደ ሂደት ነው። ከሁሉ በላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለችብትን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበ፣ ጭራሹንም የረሳ ነው።

ሀገራችን በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ባለው ኮሮና ቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጡ እና ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ የሚገኝበት፣ ወረርሺኙን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተወሰዱ እርምጃዎች ምክንያት 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለመግፋት የተገደድንበት፣ የንግድ እና አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ የተቀዛቀዘበት ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች። ከዚህ በተጨማሪ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ የሚመጣብንን ጫና ለመቋቋም ከመቼውም ጊዜ በላይ ሀገራዊ አንድነት የሚያስፈልግበት እና ጫፍ የረገጠ ፅንፈኛ አመለካከት ያላቸው ኃይሎች ምርጫው መራዘሙን እንደሽፋን በመጠቀም ብጥብጥ ለማስነሳት ቀጠሮ በያዙበት ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚፈልግ ወቅት ላይ እንገኛለን።

በዚህ ከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እና ጥንቃቄ በሚፈልግ ወቅት በደቡብ ክልል ራስን በራስ ለማስተዳደር የቀረቡ ግልጽ ጥያቄዎችን በፍፁም መመለስ የማይችል፣ ለችግሩ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኝት ዓላማ ያደረገ ትልቁን ደቡብ ክልል ወደ አነስተኛ ደቡብ ክልሎች ለመቀየር የሚደረግ ጥረት አመፅ እና ብጥብጥ ለማንሳት ለሚሞክሩ ኃይሎች ስንቅ እንደማቀበል የሚቆጠር ነው።

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 47 ንዑስ አንቀፅ 2 መሰረት የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የየራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። ከሁለት አስር ዓመታት በላይ በተግባር የተፈተሸው ሕገ መንግሥት ያረጋገጠው የብሔር ብሔረሰቦችን መብት አስከብራለሁ ብሎ ካስቀመጠው ተቃራኒ የሕዝቦች መብት ከመከበር ይልቅ የብሔራዊ አንድነት፣ ሰላም እና የሕዝቦች አብሮ መኖርን አደጋ ላይ መጣሉን ነው። ይህ ሕገ መንግሥት በሥልጣን እስከቆየ ድረስ ሀገራችን ኢትዮጵያ ተረጋግታ እንደ ሀገር የመቀጠሏ ብሎም ሕዝቦቿ በነፃነት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የመኖር መብታቸው የሚከበርበት መንገድ እንደሌለ በተግባር ተፈትኖ ግልጽ ሆኗል። ይልቁንም የተለያዩ አጀንዳ ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች ይህንን የሕገ መንግሥት ክፍተት ተጠቅመው ወደማያባራ እና መጨረሻ ወደሌለው የማንነት፣ የክልልነት እንዲሁም የሀገር እንሁንነት ጥያቄዎችን ሊያስከትል ይችላል።

ሕገ መንግሥቱ በራሱ ምሉዕ ካለመሆኑም በተጨማሪ ከፍተኛ የአፈፃፀም ጉድለት አለበት። በሥልጣን ላይ የነበረው መንግሥት እራሱ ባረቀቀው ሕገ መንግሥት ውስጥ ከተቀመጡት አካሄዶች ባፈነገጠ መልኩ የተወሰነ ቡድን ፍላጎትን ለማሟላት እና በፖለቲካ ጥቅም አሳዳጅነት ብሎም ለሕዝብ እና ለሀሳቡ ካለው ንቀት በሕዝብ ቁጥር አነስተኛ የሆኑ አካባቢዎችን በክልልነት ሲያካልል እና እውቅና ሲሰጥ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸውን አካባቢዎች በመጨፍለቅ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልልን መስርቷል። በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት አሁን ለፌደሬሽን ምክር ቤት «ክልል እንሁን» የሚል ጥያቄ ያስገቡት ዞኖችን ክልል እንዳይሆኑ ለመከልከል ምንም ሕጋዊም ሆነ የሞራል ምክንያት የለም።

ከምስረታው ጀመሮ በብዙሀን ቅቡልነት ያልነበረው የዚህ ክልል አደረጃጀት ክልሉ ከተመሰረተ በኋላ ሲተገበሩ በነበሩ አግላይ ፖሊሲዎች፣ የሀብት እና የሥልጣን ከፍፍል ኢፍትሃዊነት እናም የመልካም አስተዳደር እጦት በብዙ የክልሉ ማኅበረሰብ ዘንድ የክልልነት ጥያቄዎች እንዲነሱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል። ለዚህም ከኅብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ቀጥተኛ እና ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ሲገባ ጊዜያዊ እና የሕዝቡን ጥያቄ የማይፈቱ አማራጮችን በማቅረብ የሕዝብን እውነተኛ የፍትህ እና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ማፈን ተገቢ አይደለም።

በኢዜማ ዕምነት ራስን በራስ ማሰተዳደር ጥያቄ መሰረታዊ፣ የምንደግፈው እና ተግባራዊ እንዲሆን የምንታገልለት ጥያቄ ነው። በእርግጥ አሁን በሥራ ላይ ባለው የፌደራል አወቃቀር መሰረት ዘውግን መሰረት አድርጎ የሚደረግ የአስተዳደር አከላለል ራስን በራስ ከማስተዳደር ይልቅ አካባቢውን ለዘውግ ማንነት የባለቤትነት ካርታ መስጫ መንገድ እንደሆነ ግልጽ ነው። ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በክልል ወይም በዞን ደረጃ ብቻ የሚመለስ አለመሆኑንም በጽኑ እናምናለን። በደቡብ ክልል የተነሱ ጥያቄዎችን የወለደው የተዛባው ሕገ መንግስታዊ የመስፈርት አጣብቂኝ፣ በሌብነት የተዘፈቀ ሥርዓት፤ ፍትህ ማጣት፤ የሃብት ክፍፍል ኢፍትሃዊነት፤ እንደልብ ተንቀሳቅሶ ሰርቶ ሃብት በማፍራት የንብረቱ ህጋዊ ባለቤት የመሆን ብሎም በሰላም የመኖር መሰረታዊ መብት መነፈግ እና የመሳሰሉት አስተዳደራዊ በደሎች ጥርቅም መሆኑን እንረዳለን። አሁን የተጀመረው እንቅስቃሴ ችግሮቹን ማከፋፈል እና ማሰራጨት እንጂ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችል ስላልሆነ ከበደሎቹም ባሻገር የወደፊት መጪ ስጋቶች ፍንትው ብለው እየታዩ ነው። ወደፊት ሀብት የሚፈስባቸው ከተሞች ባለቤትነት እና በሕዝብ ስም የሚፈፀሙ የበጀት ምዝበራዎች ከስጋቶቹ መካከል ዋነኞቹ ናቸው። በራስ የሚተዳደደር ክልል እና ዞን መሆንን መፈለግ የእነዚህ በደሎች እና መጪ ስጋቶቸ ውጤት መሆኑን በቅጡ እንደሚረዳ ፓርቲ አሁን ለመሄድ እየታሰበበት ያለው መንገድ ለበደሎቹም ሆነ ለስጋቶቹ መፍትሄ እንደማይሆን ጠንቅቀን እናውቃለን።

እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የሕዝቦች በየትኛውም ደረጃ ያለ የሥልጣን እርከን ባለቤትነት መረጋገጥ ቁልፍ እርምጃ ነው። ይህ ደግሞ ሊሳካ የሚችለው እያንዳንዱ ዜጋ ከታችኛው የሥልጣን እርከን ጀምሮ የሚያሰተዳድሩትን አመራሮች መምረጥ ሲችል ነው። መሰል የዜጎች ሕጋዊ የሥልጣን ባለቤትነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በየትኛውም ቦታ የሚካሄድ የትኛውም ዓይነት ዘላቂ ውጤት ያለው ውሳኔ የዜጎችን መሰረታዊ ጥያቄ መልስ መስጠት የሚችል እንዳልሆነ ፍንትው ያለ ሃቅ ነው።

ዛሬም ቢሆን በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ከሚነሳው፤ እኛም እንደ ሀገራዊ ፓርቲ ካሉን መዋቅሮች ከሚደርሱን መረጃዎች እንደተገነዘብነው ትላንት አፋኝ እና ኢ-ዴሞክራሲያዊ ከሆነው ሥርዓት ጋር ተባባሪ በመሆን በሕዝባቸው ላይ ለደረሰው መከራ ቀዳሚ ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ካድሬዎች በውሳኔ ሰጪነት ሥልጣን ላይ ናቸው። ለውጥ እንዲመጣ ዋጋ የከፈሉ፣ ለፍትህ እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እንዲሁም ለሕዝባቸው እኩል ተጠቃሚነት የታገሉ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች በየደረጃው ባሉ የመንግሥት ውሳኔዎች ላይ ሀሳባቸው ሊሰማ ሲገባ ዛሬም በእነዚህ የመንግሥት አካላት ተፅዕኖ እየደረሰባቸው እንደሆነም ጭምር የምንረዳው ሃቅ ነው።

ገዢው ፓርቲ ይሄን ያልታደሰና የመለወጥም ፍላጎት እያሳየ ባልሆነው የካድሬና የባለሥልጣናት መዋቅሩ በደቡብ ክልል እየቀረበ ያለውን ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ለማፈን እያደረገ ያለው ሩጫ የሕዝብን መሰረታዊ ጥያቄ የማይመልስ ብቻ ሳይሆን ፓርቲው እያሳየ ያለውን የመብት ሰጪ እና ነሺነት ፍላጎትንም የሚያሳይ ነው። ይህ በየግዜው ከለውጡ አጠቃላይ መንፈስ እየራቀ የመጣው የገዢው ፓርቲ ፍላጎት በሀገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፍም ጭምር ነው።

ገዢው ፓርቲ በአንድ በኩል በኮቪድ-19 ወረርሸኝ እና ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ባለው ጫና እግር ከወረች ተይዣለው በማለት ስድሰተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ላልተወሰነ ግዜ እያራዘመ በሌላ በኩል በዚሁ ጭንቅ ጊዜ ዘላቂ ውጤታ ያላቸው ትልልቅ ሥራዎችን ያለሕዝብ ምክክር እና ውሳኔ በራሱ እያከናወነ ይገኛል። ገዢው ፓርቲ ከሕግ አግባባ ውጪ በሆነ የመብት ሰጪ እና ነሺነት የሕዝብን ተቀባይነት ለማግኘት የሚያደርገውን ሩጫ በአስቸኳይ እንዲያቆም ኢዜማ አጥብቆ ያሳስባል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በዚህ ምክንያት በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ለሚደርስ እያንዳንዱ ጉዳት ቀጥተኛ ተጠያቂ በራሱ ተነሳሽነት ጉዳዩን እየገፋ ያለው ገዢው ፓርቲ እንደሚሆን በግልፅ መታወቅ አለበት።

በደቡብ ክልል የምትኖሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ኢዜማ ደቡብ ክልል የሕዝቡን ፍላጎት ባሟላ መልኩ እንደገና እንዲዋቀር እንደሚፈልግ እንድትረዱ እና ለምታነሱት ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ትክክለኛ እና ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት አሁን ያለንበት ጊዜ እንደማይፈቅድ እና የእናንተን ፍላጎት የሚያስፈጽሙ በእናንተው የተመረጡ ወኪሎቻችሁ ሳይኖሩ እኔ አውቅልሃለው በሚሉ ካድሬዎች ሊከወን የሚቻል እንዳልሆነ በመረዳት ቀጣዩ ምርጫ ተደርጎ ፍላጎቶቻችሁን የሚያስፈጽሙ ወኪሎቻችሁን እስክትመርጡ እና በጥያቄያችሁ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጋችሁ በሕዝበ ውሳኔ መወሰን የምትችሉበት ሁኔታ እስኪመቻች በተለመደው ኢትዮጵያዊ ጨዋነት እና ትዕግስት እንድትጠብቁ አበክረን እንጠይቃለን። ይህንን ተረድታችሁ ለጋራ ሀገራችን መረጋጋት እና ሰላም በማሰብ ጥያቄዎቻችሁን በሰከነ መንገድ ለመፍታት ለምታሳዩት ትዕግስት ከወዲሁ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የከበረ ምስጋና ያቀርባል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top