Connect with us

የዋልታ ዶክመንታሪ ውሸት ከሆነ እውነቱን ለምን አታቀርቡትም?

የዋልታ ዶክመንታሪ ውሸት ከሆነ እውነቱን ለምን አታቀርቡትም?
Photo: Social Media

ኢኮኖሚ

የዋልታ ዶክመንታሪ ውሸት ከሆነ እውነቱን ለምን አታቀርቡትም?

የዋልታ ዶክመንታሪ ውሸት ከሆነ እውነቱን ለምን አታቀርቡትም?
(አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ)

ማታ በዋልታ የቀረበውን የአቶ ድንቁ ደያስን የሕይወት ታሪክ የሚያትት ዶክመንታሪ ያየሁት ከአንድ ጀለሴ ጋር ነበር፡፡ ዶክመንታሪው ሲጠናቀቅም እኔ በሰውየው ጭካኔ ስገረም ጀለሴ ‹‹ወይኔ ወይኔ›› ይል ጀመር፡፡

‹‹ምን ሆነህ ነው?›› ባልኩት ጊዜም ‹‹አቶ ድንቁ በልግሥናቸው የሚታወቁ እንጂ በወንጀል የሚከሰሱ ሰው አይደሉም›› አለኝ፡፡

‹‹ምን ያህል ገንዘብ ለበጎ አድራጎት ሰጥተው ነው በልግስናቸው የሚታወቁት?›› ብዬ ስጠይቀውም ‹‹እኔ የማወራው ስለ ገንዘብ ሳይሆን ስለ ነጥብ ነው! ኮሌጃቸው እኮ እንዴት ያለ ለጋስ መሰለህ! እኔ እራሱ 3.8 ይዤ የተመረቅኩት ከእሳቸው ኮሌጅ ነው›› ካለኝ በኋላ አስከትሎም ‹‹ዛሬ የቀረበው የዋልታ ዶክመንታሪ ከምድር ወደ ሙሕር ከመሸጋገሩ በፊት ተመራቂዎቻቸው ሰብሰብ ብለን ካላስቆምነው ነገ ደግሞ የእኛን ውጤት የሚመለከት ዶክመንታሪ መሠራቱ አይቀርም›› እያለ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡

(ያው ጀለሴ ‹‹ከምድር ወደ ሙሕር›› ሲል አቶ ድንቁ ገበሬዎችን አፈናቅለው ወሰዱት ከተባለው መሬት ወዳስመረቁት ወጣት ከመሸጋገሩ በፊት ለማለት ፈልጎ ነው፡፡)

እኔን ያስገረመኝ ግን ኮሌጅ ከፍተው ያስተማሯቸው ወጣቶች ሳይሆኑ ማሰልጠኛ ከፍተው ወታደሮች ሲያሰለጥኑ ነበር ሲባል መስማቴ ነው፡፡ እናም ይህ ነገር እውነት ከሆነ አቶ ድንቁ ትንሽ ጊዜ ቢያገኙ ኖሮ አራት ኪሎ ለመግባት ባይሞክሩ እንኳን የራሳቸውን ቤተ-መንግሥት በማስገንባት ከባለሃብትነት ወደ ንጉሥነት ሽግግር ማድረጋቸው አይቀርም ነበር፡፡

በነገራችን ላይ ባለሃብቱ ዛሬ እድል ፊቷን አዞረችባቸው እንጂ ለዚህ ደረጃ ያደረሳቸው ዶክመንታሪ የሠራባቸው ይሄው ሥርዓት ነው፡፡ ከአዳማ እስከ ሶደሬ ያለው ሕዝብ ላይ ብዙ ግፍ ሲፈጽሙ ‹‹ጎሽ›› እንጂ ‹‹ጃስ›› ያላቸው አካል አልነበረም፡፡ ‹‹ለሕዝብ አሳቢ ባለሃብት›› በሚል ሥም በሕዝብ የሚበለጽጉ ግለሰብ ሲሆኑ መንግሥት ሊያስቆማቸው አልሞከረም፡፡ በትምህርት የዳበረ ብቁ ወጣት በመፍጠር ፈንታ ውጤት ይዞ የሚወጣ ዜጋ ሲያመርቱ መንግሥት ቀጣሪ እንጂ ተቆጣጣሪ ሆኖ አልተገኘም፡፡

በመሆኑም በሚገርም ፍጥነት ፈርጣማ ባለሃብት እንዲሆኑ የፈቀደላቸውን መንግሥት ዞር ብለው ሲያዩት ደካማ ሆኖ ታያቸው፡፡ ለፍሬ ያበቃቸውን ሥርዓት ሲገመግሙት ከገለባ ቀለለባቸው፡፡ እናም ሕዝብ ላይ ያሻቸው ሲያደርጉ ዝም ያላቸውን ሥርዓት ‹‹ባስወግደው’ስ ማን ይጠይቀኛል›› በማለት እስከ ማሰብ ደረሱና ሕልማቸውን ለማሳካት ደፋ ቀና ሲሉ ተለማማጩ መንግሥት ‹‹ሕዝቡን እንጂ እኔን መንካት አትችልም›› ብሎ ድባቅ በመምታት ከወጡበት ከፍታ ቁልቁል አምዘገዘጋቸው፡፡ ዶክመንታሪ ሠርቶ ገመናቸውን ገለጠባቸው፡፡

ታዲያ የሚያስገርመው ነገር የአቶ ድንቁ ወይንም ደግሞ የመንግሥት ድርጊት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሥርዓቱ ባለሃብቱን በጫንቃው ያዘላቸው በአደጋ ጊዜ አጥቂ ወይንም ደግሞ ተከላካይ እንዲሆኑት እንጂ ከባላንጣ ጋር ወግነው እንዲወጉት አይደለም፡፡ ስለሆነም በፖለቲካው ሜዳ ውስጥ አጥቂ ሆነው ሲከሰቱ መንግሥትም የራሱን ጥቃት መፈጸሙ የሚጠበቅ ነው፡፡

በሌላ መልኩ ግን እነ ጃዋር ከባለሃብቱ ጎን ተሰልፈው ማረብረባቸው ያስገርማል፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ያለው ድጋፍ መንግሥትን ብቻ ሳይሆን ሕዝብን እንደመናቅ የሚቆጠር ነውና…

ምንም እንኳን መንግሥት ባለሃብቱን ሰለባው ያደረጋቸው ባላንጋራው መሆን የጀመሩ እለት ቢሆንም…. ይሄንንም ሲያደርግ በዜጎች ላይ የፈጸሟቸውን ግፎች፣ የጣሷቸውን ሕግጋት፣ ያልከፈሉትን ግብርና የተቀራመቱትን መሬት በመዘርዘር ነው፡፡ እናም ‹‹ባለሃብቱ ጠቃሚ ነበሩ›› ከተባለ ባፈናቀሏቸው ሰዎች ፈንታ ያሰፈሯቸውን፣ በሕገወጥነታቸው ፈንታ ሕጋዊነታቸውን፣ በጥፋታቸው ምትክ ትክክለኝነታቸውን ሳይዘረዝሩ ብሎም የተበደሉትን ሰዎች ሳያናግሩ ለባለሃብቱ ማረብረብ መንግሥትን ለመንቀፍ ሕገወጥነትን መደገፍ ነው፡፡ ግለሰብን ለመታደግ ወገንን መበደል ነው፡፡

ስለሆነም በትናንቱ ዶክመንታሪ ‹‹ባለሃብቱ ባልሠሩት ሥራ ሥማቸው ጠፍቷል›› የሚል አካል የሠሩትን መልካም ሥራ በራሱ ሚዲያ ማቅረብ ይገባዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የዜጎችንና የአገርን ጉዳት ችላ ብሎ የራስን ጥቅም ታሳቢ በማድረግ የሚጮህ ጩኸት እርባና አይኖረውም፡፡

Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top