በአዲስአበባ ቅርሶች ሊፈርሱ ነው
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአደባባይ ቅርሶች አይፈርሱም እያለ በጎን ግን አፍራሽ ግብረ ሃይል እየላከባቸው መሆኑን ፒያሳ አካባቢ የሚገኙ ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡
ከሰሞኑ የከተማዋ አስተዳደር ከመስቀል አደባባይ እስከ ማዘጋጃ ቤት ፕሮጀክት ውስጥ የሚገኙ 7 ህንፃዎች ታሪካዊ ይዞታቸውን እንደጠበቁ የሚታደሱ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡
ይሁንና አስተዳደሩ ይህን ባለ ማግስት የአራዳ ክፍለ ከተማ በሁለት ቀናት ውስጥ እቃችሁን ካላወጣችሁ ቤቶቹን በላያችሁ ላይ እናፈርሳቸዋለን ሲል ማስጠንቀቂያ ሰጥቶናል ይላሉ፤ በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ስር ያሉ የንግድ ተቋማት፡፡
አንበሳ መድሃኒት ቤትና ኒዬን አዲስን ጨምሮ በፕሮጀክቱ ስር የተጠቃለሉ በቅርስነት የተመዘገቡ ታሪካዊ ቤቶችም ይገኛሉ፡፡
ውል የተፈራረምነው ከኪራይ ቤቶች አስተዳደር ጋር በመሆኑ፤ጉዳዩን አስረድተን የፌዴራል ኪራይ ቤቶች አስተዳደር ለ7 ቀናት ያክል በፍርድ ቤት እንዲታገድ አስደርጎልናል፤ አሁንም ግን ዋስትና የለንም ሲሉ ነው ቅሬታቸውን ለኢትዬ ኤፍ ኤም ያሰሙት፡፡
ከ17 የንግድ ድርጅቶች ውስጥ አምስት የሚሆኑት በቅርስነት የተመዘገቡ ናቸው የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ቤቶቹን ለማፍረስ የመጡ ቡድኖች ማንነታቸውን የሚገጽ መታወቂያም ይሁን ደብዳቤ ለማሳዬት ፈቃደኞች አለመሆናቸውን ነው የነገሩን፡፡
ነገር ግን ክፍለ ከተማው የላካቸው መሆኑን እናውቃለን፤ ጉዳዩ ግልጽነት የጎደለውና ህጋዊ አካሄድን የተከተለ አይደለም ብለዋል፡፡
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በነዚህ የንግድ ተቋማት ላይ የከተማ አስተዳደሩ ቀጥተኛ መብት እንደሌለው በመግለጽ፤ፕሮጀክቱ በሚከናወንበት ሁኔታ ላይ እየተነጋገርን ባለንበት ሰዓት ይህ መፈጠሩ ትክክል ባለመሆኑ በፍርድ ቤት እንዲታገድ አድርገናል ብሏል፡፡
የኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ክብሮም ገ/መድህን ኮርፖሬሽኑ ለሃገራዊ ፕሮጀክቶች ሁሌም ተባባሪ ነው፤ ነገር ግን አካሄዱ ህግና ስርዓትን በጠበቀ መልኩ መሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡
በቅርስነት የተመዘገቡ ቤቶችንም በሚመለከትም ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በ2010 ዓ/ም በተፈራረምነው የጋራ መግባቢያ ሰነድ ላይ ቅርሶች እንደማይፈርሱ ተቀምጧል ብለውናል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት በበኩሉ ቤቶቹን አፈርሳለሁ የሚል አካል ከመጣ ለእኛ እንዲያሳውቁን ነግረናቸዋል አሁንም መምጣት ይችላሉ ብሏል፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ግን ወደ ከንቲባ ጽህፈት ቤቱ ቢሄዱም ተጨባጭ ምላሽ እንዳልሰጣቸው ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡
(ኢትዮ ኤፍ ኤም)