Connect with us

የዘንድሮውን ግንቦት ሃያ የማከብርበት ምክንያት…

የዘንድሮውን ግንቦት ሃያ የማከብርበት ምክንያት…
Photo: Social media

መዝናኛ

የዘንድሮውን ግንቦት ሃያ የማከብርበት ምክንያት…

የዘንድሮውን ግንቦት ሃያ የማከብርበት ምክንያት…
(አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ)

ዋቀዮም ድብርቴን በተመለከተ ጊዜ ከእኔ ቀጥሎ ያለውን ባለ አንድ መኝታ ኮንዶሚንየም አንዲት ውብ ኮረዳ እንዲትከራየው ፈቀደ፡፡ ከዚያን ቀን አንስቶም የዚህ ወግ ጸሐፊ የሆነው ወንደላጤ የደስታ ስሜት ይሰማው ጀመር፡፡

ኮረዳዋ ጎረቤቴ ከሆነች ወር አካባቢ ይሆናታል፡፡ እድሜዋ ከ25-27 ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ ይገመታል፡፡ ነዶ ጸጉሯ ቢከፋፈል ሶስት መለስተኛ የራስ ቅሎችን ለመሸፈን ይበቃል፡፡ የከንፈሯ ውበት፣ የጥርሷ ንጣት፣ የአፍንጫዋ ሰልካካነት ከፍ ሲል ባሏ፣ ዝቅ ሲል ጭንብሏ ለመሆን ያነሳሳል፡፡ ዘወትር የምትለብሰው ማስኳ ከፊቷ ላይ ተለጥፎ ሲታይ አሰፍታው እንጂ ገዝታው አይመስልም፡፡

በተረፈ ያን የመሰለ የቆዳ ጥራት ያጎናጸፋት ከልጅነቷ ጀምራ በሳኒታይዘር እየታጠበች አድጋ ካልሆነ በቀር የለገዳዲ ውሃ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ለዚያም ነው ከቤቷ ወጣ ስትል ኮሪደሩ ሳኒታይዘር ሳኒታይዘር የሚሸተው፡፡

ቆንጆዋን ልጅ የተግባባኋት ወደ ብሎካችን በመጣች ማግሥት ሲሆን የምንጋባበት ቀን እስኪደርስ ድረስ ከቀን እስከ ማታ ኮሪደር ላይ ተጎልቼ በወጣች በገባች ቁጥር ስሽቆጠቆጥላትና ስታዘዛት ከሰነበትኩ በኋላ… ትናንትና አመሻሽ ላይ ‹‹ና ቡና ጠጣ›› ብላ ወደ ቤቷ የምገባበትን እድል ፈጠረችልኝ፡፡

በዚህም መሠረት ከሳሎኗ አረፍ ብዬ በቤቷ ፈንታ ፊቷን እያየሁ ሳስቸግራት ‹‹ቴሌቪዥን ተመልከት›› ብላ ሪሞቱን አቀበለችኝ፡፡ በመሆኑም ቻናሉን ኢሳት ላይ ካደረኩ በኋላ ቴሌቪዥኑን ትቼ የማር እንጀራ የሚመስል ኮምፎርት የተነጠፈበትን አልጋዋን በሁለት ዐይኔ ስመለከት ሁለት ትራሶች ተጋድመው ዐየሁ፡፡ ሶስተኛ ዐይኔን ሳበራው ደግሞ ከሰሙ ባለፈ ወርቁን መረዳት ችዬ ‹‹ሜትር ከአምሳ አልጋ የገዛሁት የወደፊት ባሌን ታሳቤ በማድረግ ነው›› የሚል ቅኔ አልጋ ልብሱ ላይ ተጽፎ አነበብኩ፡፡

ሰምና ወርቁን ፈትቼ ከጨረስኩ በኋላም… ትኩረቴን ከአልጋዋ ወደ እሷ በማዛወር ‹‹ይሄን የሚያክል አልጋ የገዛሽው ለብቻሽ ነው?›› በማለት ስጠይቃት ‹‹ጓደኛ ነበረኝ›› በማለት መለሰችልኝ፡፡

ይሄንንም ስሰማ አልጋ ወራሽ የመሆን ከፍተኛ ጉጉት እያደረብኝ ‹‹የት ሄዶ ነው ታዲያ?›› የሚል ጥያቄ ሰነዘርኩ፡፡
‹‹ከተለያየን ቆየን››
‹‹ምክንያቱን ማወቅ ይቻላል?››
‹‹ምን ምክንያት አለው ብለህ ነው? እናንተ ወንዶች ስትባሉ የምትፈልጉትን እስክታገኙ ድረስ እንጦሮጦስም ቢሆን ተከትየሽ እገባለሁ እያላችሁ ስትቀላምዱ ትከርሙና ምኞታችሁ ሲሰምር ግን ወደ እንጦሮጦስ ወርውራችሁን መመለስ ሙያችሁ ነው›› በማለት በሃዘን ስሜት ውስጥ ሆና መለሰችልኝ፡፡

በዚህን ጊዜም ‹‹ሁሉም ወንድ አንድ አይነት አይደለም! በበኩሌ ያፈቀርኳትን ሴት ተከትየ ወደ መቃብርም ሆነ ወደ እንጦሮጦስ ባልገባም… ስትታመም አብሬያት ታምሜ ወደ ኤካ ሆስፒታል ከገባሁ በኋላ አብሬያት አገግሜ እንደምመለስ አልጠራጠርም›› ስላት መከፋቷ ለቀቃትና ከት ከት ከት በማለት ዘመረች፡፡

በወሬያችን መሃከልም ‹‹ኢሳት እለታዊ›› ጀመረና… የእለቱ ትንታኔ በፈንቅል ትግል ዙሪያ የሚያጠነጥን መሆኑን ስሰማ ‹‹ህውሓት አበቃላት›› እያልኩ ፕሮግራሙን ለመከታተል ስዘገጃጅ ‹‹አቦ እነዚህን መንቻኮች ወደዚያ አጥፋልኝ›› በማለት በቡናዋ ፈንታ የኮረዳዋ ደም ይፈላ ጀመር፡፡

ይሄም ብስጭቷ የድሮ ሥርዓት ናፋቂ መሆኗን ስለገለጸልኝ ሪሞቱን አንስቼ ቻናሉን ከኢሳት ወደ DW ስቀይረው ብርቱዋ ፖለቲከኛና የሕግ ባለሙያ ወይዘሪት ብርቱካን ከአንድ ጋዜጠኛ ፊት ለፊት ተቀምጣ በመስቀለኛ ጥያቄዎች ሊያፋጥጣት አስቦ የጋበዛትን የሃርድ ቶክ አዘጋጅ መፈናፈኛ አሳጥታውና ዐይኑን የሚያሳርፍበት ቦታ ነፍጋው ዐየሁ፡፡

እኔ ደግሞ የወደድኳትን ልጅ ቁጣ ለማብረድ ስል ብቻ… ያለ ውድ በግዴ ከቻናሉ በማስከተል ሐሳቤን ቀይሬ የአሮጊቶቹ ደጋፊ በመሆን ወጣቶቹን ሳወግዛቸው ቆየሁ፡፡ ከጥቂት የደጋፊነት ቆይታ በኋላም ወደ ሙሉ አባልነት እራሴን አሳድጌ ‹‹ለመጪው የግንቦት ሃያ በዓል አንቺ ዳቦውን የምታዘጋጅ ከሆነ፣ እኔ ሻማውን ለማምጣትና አብሬሽ ለማክበር ዝግጁ ነኝ›› አልኳት፡፡

በዚህን ጊዜም ቆንጆዋ ልጅ ከቀጥተኛ ንግግሬ ላይ ያላሰብኩትን ቅኔ ማግኘቷን በሚያሳብቅ ሁኔታ በመላ ሰውነቷ እየተሸኮረመመች ‹‹ፊኛም ጨምርበት›› አለችኝ፡፡

‹‹ፊኛ ደግሞ ምን ያደርጋል?›› ብዬ በጠየቅኳት ጊዜም ‹‹ዳቦዬ ከመቆረሱና ሻማህ ከመለኮሱ በፊት የምንነፋው ነገር ያስፈልገናል›› ብላኝ አረፈች፡፡

ይሄንንም ስሰማ አንዳች የሚነዝር ስሜት እየተሰማኝ በዐይኗ ማግኔት የተጨመደዴ ዐይኔን በግድ አንቀሳቅሼ ወደ ቲቪው ከወሰድኩ በኋላ እፍረቴንና ድንጋጤየን ለማስታገስ ሳስብ ከእኔ በላይ የተደናገጠው ጋዜጠኛ ጋር ዐይን ለዐይን ተያየንና ‹‹አይዞን›› ተባባልን፡፡

ድንጋጤዬ ባለፈ ጊዜም… ከዚህ ምሽት አንስቶ እስከ በዓሉ ቀን ድረስ ያሉትን ቀናቶች በድምቀት ለማክበር የሚያስችል በቂ የሻማና የፊኛ አቅርቦት መኖሩን ገልጬ ስለ ሙጌራው ሁኔታ ስጠይቃት ‹‹ተዓምር ቢሆን ከግንቦት ሃያ በፊት ዳቦየ አይቆረስም›› በማለቷ… ልመናየን ትቼ ‹‹ግንቦት ሃያ ስንት ቀን ቀረው?›› እላት ጀመር፡፡

Continue Reading
Click to comment

More in መዝናኛ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top