Connect with us

የትግራይ ሕዝብ ለነጻነት እና እኩልነት የሚያደርገውን ትግል …

የትግራይ ሕዝብ ለነጻነት እና እኩልነት የሚያደርገውን ትግል

ፓለቲካ

የትግራይ ሕዝብ ለነጻነት እና እኩልነት የሚያደርገውን ትግል …

የትግራይ ሕዝብ ለነጻነት እና እኩልነት የሚያደርገውን ትግል
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ይደግፋል!
**
የትግራይና የአማራ ሕዝብ ለሽህ ዓመታት የዘለቀ ቤተሰባዊ ትስስር እና አንድነት ያላቸው ሕዝቦች መሆናቸው ታወቃል። በረጅሙ ታሪካችን ውስጥ ይሄ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የሕዝብ ግጭት ኖሮን የማያውቅ ቢሆንም ፋሽስት ጣሊያን አገራችን ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የቀረጸውን ፖሊሲ የፖለቲካ ፕሮግራሙ አድርጎ የተቀበለው እና የአማራን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆ ከደደቢት በርሃ እስከ ታላቁ ቤተመንግስት የዘለቀው ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር(ትሕነግ) ብሎ የሚጠራው ቡድን በአማራ ሕዝብ ላይ ባደረሰው ጥፋት እና ስርዓት ሰራሽ ጥቃት ምክንያት ግንኙነታችን ፈተና ላይ ወድቆ ቆይቷል። ሕወኃት በአገር ወዳድ ኃይሎችና በመላዉ የኢትዬጵያ ሕዝብ ትግል ከተሸነፈ በኋላ በትግራይ ሕዝብ መካከል መሽጎ የጥፋት እና የሴራ መረቡን በመዘርጋት በርካታ ጥቃቶችን እና ዉድመቶችን አስከትሏል። ይህ ቡድን በመላ አገራችን ላይ አንሰራፍቶት የነበረዉን የአፈና ስርዓት ጠቅልሎ በትግራይ ሕዝብ ላይ አስፍኖበት ይገኛል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ከአንድ ዓመት በፊት ባወጣው መግለጫና ለመንግሥት ባደረገው ጥሪ ሕወኃት በአጠቃላይ በአገራችን በልዩ ሁኔታ ደግሞ በአማራ ሕዝብ ላይ በጥላቻ ተመስርቶ ሥራ ላይ ባዋለው ሕገ መንግሥትና ልዩ ልዩ ፖሊሲዎች የአገራችንን አንድነት እና ሉአላዊነት አደጋ ላይ የጣለ፣ መላዉ የአገራችን ሕዝብ በተለይም የአማራ ሕዝብ ማኅበራዊ ረፍት እንዳያገኝ አገር የማተራመስ ፖሊሲ የሚያራምድ ፅንፈኛ የፖለቲካ ኃይል እንዲሁም በቀጣይ በአገራችን ዉስጥ ሊኖር የሚገባዉን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ለማስተጓጎል በቋሚነት የተሰለፈ ጎታች ኃይል መሆኑን በመግለፅ ሕወኃት “አሸባሪ” ድርጅት ተብሎ እንዲሰየምና ከሰላማዊ የፖለቲካ ፖርቲዎች ምዝገባ እንዲሰረዝ ጥሪ ማስተላለፉ ይታወቃል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በትግራይ ሕዝብ እና በአሸባሪው ትሕነግ ቡድን መካከል ያለውን ልዩነት ጠንቅቆ ያውቃል፤ ትሕነግ የአማራን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆ ትግል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በስልጣን ላይ በቆየባቸው አመታት ሁሉ በአማራ ሕዝብ ላይ ላደረሳቸው ህልቆ መሳፍርት በደሎች እና ስርዓት ሰራሽ ጥቃቶች ኃላፊነቱ የአሸባሪው ድርጅት እንጅ የጨዋው እና የተከበረው የትግራይ ሕዝብ አለመሆኑን አብን፣ የአማራ ሕዝብ እና አገር ወዳድ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ለአፍታም ቢሆን አንስተውም።

የትግራይ ሕዝብ ራሱን በመንደር እና በጎጥ አደራጅቶ እያጠቃው ካለው የትሕነግ አገዛዝ ጋር የሚያደርገውን ትግል አብን፣ የአማራ ሕዝብ እና መላው አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በትኩረት እየተከታተልን መሆኑን አውቆ እና የወደቀው ሕውኃት-ትሕነግ መንኮታኮት የጊዜ ጉዳይ ብቻ መሆኑን ተረድቶ አገዛዙን ለመገርሰስ የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያችንን እያስተላለፍን የትግራይ ሕዝብ በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ግንኙነት መካከል ደንቃራ የሆነውን የተደራጀ የወንጀለኞች ቡድን፤ የትሕነግ የአገዛዝ ስርዓት ከራሱ ላይ አሽቀንጥሮ በመጣል ከሌሎች ኢትዮጵያውያን እህት ወንድሞቹ ጋር በአንድነት ለመቆም፤ ለፍትኅ፣ ለእኩልነትና ለነጻነት በሚያደርገው ትግል አብን ከጎኑ እንደሚቆም ያስታውቃል።

በተለይ ከሕወኃት መወገድ በኋላ የሚኖረዉ ዘመን የአማራ እና የትግራይ ሕዝብ የቀደመውን ቤተሰባዊ ትስስራቸውን ወደ ነበረበት የሚመልሱበት፣ ሕዝባዊ አንድነታቸውን የሚያረጋግጡበት እንደሚሆንና በሰለጠነ ዉይይት እና ድርድር ዉስጥ ከሌሎቹ የአገራችን ወንድም ሕዝቦች ጋር በመተባበር የሚገቡበትን ምዕራፍ ከፋች እንደሆነ፤ አገራችንንም በጋራ ወደ ዘላቂ የእኩልነት፣ የነፃነት፣ የሰላም እና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማስገባት የምንችልበት እንደሚሆን በምክንያታዊ ርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

የአማራ ሕዝብ እና መላዉ የኢትዬጵያ ሕዝብ በዚህ ፈታኝ ወቅት ወገናችን የትግራይ ሕዝብ ከሕወኃት ዘረኛ፣ ጠባብ፣ ጎጠኛ እና አፋኝ ስርዓት ነፃ ለመዉጣት የሚያደርገዉን ትግል አግዛችሁ እንድትቆሙ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ይሄን ታሪካዊ ጥሪ ያስተላልፋል።

አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!

አዲስ አበባ፤ ሸዋ፤ ኢትዮጵያ
ግንቦት 18 ቀን 2012 ዓ.ም

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top