ዶክተር አብይ በንጉሥ አርማህ መንገድ፤
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሶርያ ስደተኞች ያደረጉት መልካም መስተንግዶ የኢትዮጵያን የታሪክ ስም ያስጠበቀ እንደኾነ አምናለሁ፡፡ | ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ውለታዋ ያልተመለሰላት ናት፡፡ ታሪክ ካመነበት ታሪኳ የሚመጥን ስምና ክብር አልተሰጣትም፡፡ እንግዳ ተቀባይዋ ሀገር ስለ ዜጎቿ የምትሰማው ዜና ከፎቅ መጣላቸውን ነው፡፡ የዓለም ዋጋ ቢሱ ፓስፖርት የኢትዮጵያ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት ምናልባትም እንደ ቱርክ ባሉ ጥቂት ሀገራት ካልሆነ በስተቀር የተለየ ዋጋ የለውም፡፡
ቱርክ በዚህ አትታማም፤ ከነጃሺ ሀገር ነኝ የሚል ዜጋን ታከብራለች፡፡ የታላቁ ንጉሥ እንግዳ ተቀባይነት የኢትዮጵያዊያን ዘመን አይሽሬ ክብርና ማዕረግ ሆኖ ይኖራል፡፡
ሶርያውያን በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በልመና ተሰማርተዋል፡፡ የአዲስ አበቤዎች ልብ ከሀገራቸው ዜጋ በልጦ ለሶርያውያኑ ሲራራ ተመልክቻለሁ፡፡ የኢትዮጵያውያን እጅ አብልጦ ለሶርያውያን የተዘረጋው የሰው ሀገር ሰው የሚለው እውቀት የተለየ ቦታ ስለሚሰጠው ነው፡፡
ዶክተር አብይ ከሶርያ ስደተኞች ጋር አብረው አሳልፈዋል፡፡ ጋብዘዋቸዋል፡፡ እርግጠኛ መሆን ይከብደኛል፡፡ ሶርያዎች በብዙ የዓለም ሀገራት ተበትነዋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ኢስላም ወደሆኑ ሀገራትም ገብተዋል፡፡ የሰለጠኑት የአውሮፓ ሀገራትም ደርሰዋል፡፡ አንድ የሀገር መሪ አብሯቸው ማዕድ ተካፍሎ አይዞአችሁ ሲል ዶክተር አብይ ቀዳሚው ይመስሉኛል፡፡ ምናልባትም ብቸኛው፡፡
ሌላው ሀገር አይዞአችሁ ሲል በመግለጫ ነው፡፡ በወረቀት ነው፡፡ መመሪያ በማቅለል ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሄዱበት መንገድ የኢትዮጵያን የቀደመ ክብር ያስቀጠለ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ሶርያዎች ምናልባትም ነጃሺን ያገኙት እስኪመስላቸው ስለኢትዮጵያ የሚታተምባቸው እውቀት ዘመን አይሽረውም፡፡
መሪያችን በንጉሥ አርማህ ጎዳና ሄደዋል፡፡ ያ ዳና እንግዳን ማክበር ነው፡፡ ያ ዳና እንግዳን ቤታችን ቤትህ ነው ማለት ነው፡፡ ደስ ብሎኛል፡፡ ትርጉሙን አብልጦ የሚረዳው መጪው ትውልድ ነው፡፡ ሞኝነት የሚመስሉ ነገሮች በሀገራት መካከል ነገ ህያው የዝምድና ታሪክ ይሆናሉ፡፡ ትናንት ኮሪያ ስንዘምት ኮሪያ ደሃና ጦርነት ያመሳት ሀገር ነበረች፡፡ ምንም ይደረግልናል ብለን አይደለም፡፡ ሰላም ለማስከበር ሄደን አባቶቻችን ለኮርያ ነገ ተዋደቁ፡፡ ዛሬ ኮሪያ ይህንን በወቅቱ ተልዕኮ የነበረ ተግባር ዛሬ ዘመን የማይሽረው ውለታ አደረገችው፡፡
ሶርያውያን ቤት ነበራቸው፡፡ ባለ ጸጋ ሀገርም ነበረች፡፡ ትናንት የእነሱ ጎዳናዎች ያስቀኑ ነበር፡፡ ዛሬ ቤት አልባ ስደተኛ ዜጎች ሀገር ሆነች፡፡ ለእለት ጉርስ በሰው ሀገር ጎዳና ወጡ፡፡ በታላቁ ወር በአንዱ ቀን በታሪክ ወርቃማ ስም ያላት የእንግዳ ተቀባዮ ንጉሥ ሀገር መሪ በክብር ጠራቸው፤ አብረው አሳለፉ፡፡ ትርጉሙን ዘመን ያደለው ይረዳዋል፡፡ ስሜቱን ግን ተጋርተንዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከፍ ዝቅ በማይል የክብር ስም ትቀጥል ዘንድ የሚያስችል ተግባር ነውና፤