Connect with us

ምሥላቸው በተማሪዎች ደብተርና መጽሐፍ ላይ፣ ሥማቸው በጎዳናዎቻችን ላይ …

ምሥላቸው በተማሪዎች ደብተርና መጽሐፍ ላይ፣ ሥማቸው በጎዳናዎቻችን ላይ

ባህልና ታሪክ

ምሥላቸው በተማሪዎች ደብተርና መጽሐፍ ላይ፣ ሥማቸው በጎዳናዎቻችን ላይ …

ምሥላቸው በተማሪዎች ደብተርና መጽሐፍ ላይ፣ ሥማቸው በጎዳናዎቻችን ላይ ሊታተምና ሊሰየም የሚገባቸው አባት
አሳዬ ደርቤ በድሬ ቲዩብ

ባሁኑ ጊዜ በሃይማኖታችንም ሆነ በፖለቲካችን ውስጥ ጥሩ ሥም ለማፍራትና ተቀባይነት ለማግኘት የእራስን እምነት ማስተማር ወይንም ደግሞ ለራስ ማንነት መቆርቆር አይበቃም፡፡

ይልቅስ አንድ የፖለቲካ መሪ ወደ መድረኩ ሲመጣ ከሚወክለው ሕዝብ ጋር የሚጠላውን ሕዝብ ለይቶ መሆን አለበት፡፡ እወደዋለሁ ከሚለው ብሔር ባለፈ እጠላዋለሁ የሚለው አካል ያስፈልገዋል፡፡

ይህ ነገር ታዲያ ወደ ሃይማኖታችንም ተላልፎ በየቤተ-እምነቶቻችን ጥሩ ሥም ያላቸውን ዲያቆኖች፣ ኡስታዞች፣ ፓስተሮች… ብንመለከት ልዩነትን በመፍጠር የተካኑ ናቸው፡፡

የሚከተሉት ሃይማኖት ውስጥ ያለውን እውነት ከመስበክ ይልቅ ሌላው ዘንድ ‹‹አለ›› ብለው የሚያምኑትን ስህተት የሚያስተምሩ፣ ጥቃቅን የሃይማኖት ግጭቶች ሲፈጠሩ ከመረጋጋት ይልቅ ማባባስ የሚቀናቸው በርካቶች ናቸው፡፡

ከሚያፋቅሩን ይልቅ የሚያቃቅሩ ታሪኮችን እየቆፈሩ እንደ ፖለቲካ መሪ በአማኙ ሕዝብ ልብ ውስጥ ጥላቻን እና ቂምን የሚዘሩ የሃይማኖት መሪዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡

ተቀዳሚ ሙፍቱ ሃጂ ኡመር ኢድሪስ ግን እንደ እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ሳይሆኑ ምግባራቸውን የሚገልጽ ተክለሰውነትና ሸጋ አንደበት የተሰጣቸው ታላቅ የሃይማኖት አባት ናቸው፡፡ አባትነታቸው ደግሞ ለአንድ ሃይማኖት ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያኖች ጭምር ነው፡፡

ለምሳሌ ያህል እኔ የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ብሆንም የእምነት አባቶች በቴሌቪዥን ቀርበው በሚናገሩበት ጊዜ ከእራሴው ሃይማኖት መሪዎች ይልቅ የእኒህን አባት ቴምር ቴምር የሚል ንግግር ማድመጥን እመርጣለሁ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከአንደበታቸው የሚወጡት ቃላቶች ሁሉ ከእምነቱ ተከታዮች ባለፈ ለመላው የሰው ልጆች የሚጥሙ መሆናቸው ነው፡፡ ከእምነት ጎን በጎን ሰብዓዊነትን፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነት፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን የሚሰብኩ መሆናቸው ነው፡፡

ምንም እንኳን ይሄ አባታዊ ምግባራቸው በዘመኑ የሃይማኖት መሪዎች ዘንድ የማይፈለግ ሆኖ አጣብቂኝ ውስጥ እየከተታቸው ቢመጣም እሳቸው ግን ታላላቅ ሸሆች ከተኸለቁበትና፣ ሃይማኖት ፍቅርን ከማይበልጥበት ምድር የበቀሉ በመሆናቸው አብሯቸው ያደገውን ሊጥሉት አይቻላቸውም፡፡ ወንበራቸው የሚፈልገውን ዓይነት መሪ ከመሆን ይልቅ አምላካቸው የሚወደውን አይነት ሰው ሆነው ማለፍ የሚመርጡ ናቸው፡፡ በዚህም ባሕሪያቸው የሁላችንም አባት ከመሆንም አልፈው ‹‹የሃይማኖት አባት›› የሚል ሐረግ ስንሰማ ቀድመው ትዝ የሚሉን እሳቸው ሆነዋል፡፡

አንዳንድ ጊዜ እኮ በእኛ በተከታዮቻቸው ዘንድ የሃይማኖት አባቶችን መተቸት አምላክን እንደ መተቸት የሚቆጠር ስለሆነ እንጂ የጨፈንነውን ዐይናችንን ገልጠን የቤተ-እምነቶቻችንን መድረክ ብንመለከት የበግ ለምድ በለበሱ ተኩላዎች፣ በአምላክ ሥም በሚያምታቱ ነጋዴዎች፣ ለገነት ቀርቶ ለመሬት በማይመጥኑ ሰዎች መወረሩን እንረዳ ነበር፡፡

ታዲያ ንግዱና ማጭበርበሩም ቢሆን ከግጭት ይልቅ መስማማትን፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን፣ ጥላቻን ሳይሆን ፍቅርን በመዝራት ላይ የተመሰረተ ቢሆን ባልከፋ ነበር፡፡ እነሱ ግን የራሳቸውን ሕይወት የሚያለመልሙት የአማኙን ሕይወት በማጨለም ነው፡፡ ምድራዊ ቤታቸውን የሚያፈኩት ጨለማን እየዘሩ ነው፡፡

በመሆኑም ተኩላነት በነገሰበት በዚህ የነጋዴዎች ዘመን እንደ ተቀዳሚ ሐጂ ኡመር እንድሪስ ዓይነት ‹‹ሰው ሁኑ›› በሚል አምድ ስር ‹‹ከሃይማኖት ሰውነት መቅደሙን፣ ወንጀልና ስህተት በደም አለመተላለፉን›› የሚያስተምሩ አባት ማግኘታችንን ትልቅ ጸጋና በረከት ነው፡፡

እናም እኛ ኢትዮጵያውያን ታላላቅ ስብዕናዎቻችንን በሕይወት ሳሉ ከማወደስና ከመዘከር ይልቅ ይህችን ምድር ከለቀቁ በኋላ ማስታወስና ማንገስ የምንወድ ስለሆንን እንጂ እንደ እሳቸው ያሉ የአገር አድባሮቻችንን ሳናጣቸው በፊት ምሥላቸውን በተማሪዎች ደብተርና መጽሐፍ ላይ አትመን፣ መልካም አስተምህሯቸውን ጽፈን፣ ሥማቸውን በጎዳናዎቻችንና በአደባዮቻችንን ላይ ሰይመን አክብሮታችንን ልንገልጽላቸው ይገባን ነበር›› እያልኩ ‹‹ለመልካም አባታችንና ለመላው የእሥልምና ተከታይ ለሆኑ ወገኖቻችንን እንኳን ለ1441ኛው የኢድ አል-ፈጥር በዓል አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top