ኢትዮጵያውያን ከተረፋቸው ሳይሆን ከሌላቸው ላይ ቆጥበው እየገነቡ ያሉት እና ወደ ፍፃሜ እየተቃረበ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁንም አጨቃጫቂ እንደሆነ ቀጥሏል። ይሁን እንጂ ግድቡ የኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብት እንደመሆኑ ግንባታውን ከማፋጠን የገደበው የለም። የተፈለገውን መስዋዕትነት ሁሉ በመክፈል የግድቡን ግንባታ ዳር ማድረስ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ግዴታ መሆኑንም ጭምር ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ሲናገሩ ይደመጣል።
“ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እየተገነባ ያለው በህዝብ ገንዘብና ላብ ከመሆኑም በላይ አባይ የኢትዮጵያውያን የተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም ደም ስር ነው” የሚሉት አቶ ያሲን ኑሩ፤ አሁንም ቢሆን ግድቡን ለማጠናቀቅ የሚፈለግብንን መስዋትዕነት ሁሉ በመክፈል ማጠናቀቅ ከኢትዮጵያውያን ይጠበቃል። የህዳሴ ግድብን ከኢትዮጵያውያን እጅ ነጥቆ ሊያወጣ የሚችል ኃይል የለም። ምክንያቱም የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ደም ስር ነው ይላሉ።
ግብፅና ሱዳን እያደረጉ ያሉት እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ እንድትራብና እነሱ ብቻ ከአባይ ወንዝ ተጠቃሚ ሆነው መልማት ስለፈለጉ ነው እንጂ፤ ኢትዮጵያ ብቻዬን ልጠቀም አላለችም። ይህ ይታወቃል። ነገር ግን ግብፅ በአሁኑ ወቅት ኃይል በመጠቀም ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷ በሆነው የአባይ ወንዝ ላይ ተጠቃሚ እንዳትሆን ብዙ ጥረት እያደረገች ትገኛለች። ከእሷም አልፎ ሱዳንን በመጠምዝዝ እንዳትስማማ አድርጋለች ብለዋል።
ነገር ግን ሱዳን ከዚህ በፊት ልማቱ እንዲቀጥል ፍቃደኛ ነበረች። ስለዚሀ ሱዳንንም ከግብፅ ለይተን ማየት የለብንም የሚሉት አቶ ያሲን፤ የህዳሴ ግድብ ግንባታው ሲያልቅ ከግድቡ በሚገኘው ልማት ኢትዮጵያ ማደግና መበልፀግ የምትችል በመሆኑና ህዝቦቿም ከድህነት ጎዳና የሚወጡበት በመሆኑ በሚፈለገው ሁሉ እሳተፋለሁ። አቅማችን በፈቀደው ልክ እስካሁንም በገንዘብ ስንረዳ ነበር አሁን በእኔ በኩል የሚፈለግብኝን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ብለዋል።
አያይዘውም በአሁኑ ወቅት የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መንግስትና የጤና ባለሙያዎች አድርጉ የሚሉትን ጥንቃቄዎች በማድረግ መዋጋት እንደሚቻል አስታውሰው፤ በተለይም በህዳሴው ግድብ አካባቢ የሚሰሩ መሀንዲሶችና አጠቃላይ ባለሙያዎች ኮሮና ቫይረስ የግድቡን ግንባታ ወደ ኋላ እንዳይመልሰው በከፍተኛ ጥንቃቄ ሥራቸውን መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ አሚና ዓሊ፤ “ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማለት የልጆቻችን የነገ ትልቅ ሀብት ነው” በማለት ሃሳባቸውን ሲገልፁ፤ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እየደገፉ መሆኑን እና አሁንም ወደፊትም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ይገልጻሉ። ግድቡ የእያንዳንዳችን ሀብት በመሆኑ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ባለው አቅም ሁሉ መደገፍ እንዳለበትም ይናገራሉ ። ገንዘብ ያለው ገንዘቡን፤ ዕውቀት ያለውም ዕውቀቱን በማካፈል የግድቡን ግንባታ ተጠናቆ ለማየት መጓጓት እንዳለበት ይመክራሉ።
የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ ለእኛ ኢትዮጵያውያን ያለው ፋይዳ በእጅጉ የጎላ ነው። በመሆኑ የግብፅን ረብሻና ጫጫታ ሳናዳምጥ እኛ ሥራችንን ዝም ብለን መስራት አለብን። መንግስትም ሁሉንም ነገር በግልፅ ሳይሆን፤ በሚስጥር በመያዝ የሚሰራቸውን ሥራዎች በፀጥታ መስራት አለበት ያሉት ወይዘሮ አሚና፤ ኢትዮጵያ አሁን ያላትን የውጭ ግንኙነቶች በመጠኑ በማድረግ የሀገሪቷን ዳር ድንበር መጠበቅም እንዳለባት ጠቁመዋል።
ግብፅ አሁንም ድረስ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ እያነሳች ያለውን ውዝግብ አስመልክቶ መንግስት አሁንም ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ እና በውይይት ለመፍታት እያደረገ ያለው ጥረት ሊበረታታ የሚገባው ነው ያሉት ወይዘሮ አሚና፤ ነገር ግን ግብፆች፤ በሰላማዊ መንገድ አይሆንም ብለው ጦርነት የሚያውጁብን ከሆነ ወደ ኋላ ማለት የለም በጦርነትም ቢሆን የህዳሴ ግድቡን ማጠናቀቅ ለኢትዮጵያውያን የግድ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ኤርጳ ዳበሳ የትራፊክ ፖሊስ ናቸው። የህዳሴ ግድብ ጉዳይ የሁላችንም ጉዳይ ነው ይላሉ ፤ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ምንም አይነት ድርድር አያስፈልገውም ተገድቦ ማለቅ አለበት። መንግስት እንደ መንግስት ሥራውን መስራት አለበት። ህብረተሰቡም ከመንግስት ጎን በመቆም እንደጀመርነው መጨረስ ይጠበቅብናል ይላሉ ።
በአባይ ጉዳይ ግብፅም ሆነች ሱዳን የሚያራምዱትን ሃሳብ ለመቋቋምና የህዳሴ ግድቡን ለማጠናቀቅ ህዝቡ አንድ መሆን አለበት። የብሔር፣ የፖለቲካና የተለያዩ ልዩነቶቻችንን በመተው አንድ ሆነን የተፈለገውን መስዋዕትነት ሁሉ በመክፈል ግድቡን መጠናቀቅ እንዳለበትም ይመክራሉ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2012