Connect with us

ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
Photo: Facebook

ባህልና ታሪክ

ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 ድንጋጌ መሠረት ከግንቦት 4 እስከ ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ የተካሄደውን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አስመልክቶ ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ፤

1. በዓለማችንና በአገራችን በኢትዮጵያ ጭምር ከቅርብ ወራት ወዲህ የተከሰተው የኮረና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ እስከአሁን በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን በመያዙና ከመቶ ሺህዎች ላላነሱ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤን በእጅጉ ያሳዘነ ሲሆን ጉባኤው፣ በቫይረሱ የተጠቁትን ምሕረት እንዲሰጠልን እስከሁን በቫይረሱ ያልተጠቁትንም እንዲጠብቅልን ተማህጽኖውን ለእግዚአብሔር አቅርቧል፡፡

2. ይኸው ተላላፊና የሰው ልጆችን በሞት እየነጠቀ ያለውን ቫይረስ እግዚአብሔር አምላክ በምሕረቱ እንዲያጠፋልን ምእመናን እንደ አንድ ልብ መካሪና እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን እንዲጸልዩ ተይዞ የነበረውን የሱባኤ ጊዜ በአግባቡ መከናወኑን ጉባኤው ተገንዝቦ ለወደፊቱም ካህናትም ሆኑ ምእመናን ወደ እግዚአብሔር የሚያደርጉትን ጸሎት በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በቤታቸው አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጉባኤው አበክሮ አሳስቧል፡፡

3. በዚሁ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ የሚሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት መቋረጡ በምእመናን ሕይወት ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑና ምእመናን ከቤተ ክርስቲያን ተለይተው መኖር ስለማይችሉ በቀጣይም የሕዝቡን ጤና መጠበቅ በሚያረጋግጥ መልኩ የሚመለከታቸው የሃይማኖት አባቶች እና የጤና ባለሙያዎች በሚሰጡት ሙያዊ ምክርና መንግሥትም በሚሰጠው መመሪያ መሠረት አሁንም የአካላዊ ርቀትና ንጽሕና አጠባበቅ ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ተሰጥቶት፣ ለዚሁ ተግባር በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ በተመደቡ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች አስተናጋጅነት ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲከናወን፣

4. አገራችን ኢትዮጵያ አገረ እግዚአብሔር፣ ሕዝቧም ሕዝበ እግዚአብሔር እየተባለ እንደሚጠራ ይታወቃል፡፡ መጠራትም ብቻ ሳይሆን ሕዝባችን በፈሪሃ እግዚአብሔር ተከባብሮ እንኳን የራሱ የሆነውን ወገኑን ቀርቶ ሌላውን እንደራሱ አድርጐ የሚወድ፣ ያለው ከሌለው ጋር የሚካፈልና በደግነቱ የሚታወቅ ሕዝብ መሆኑን ዓለም የሚመሰክረው ነው፡፡
በመሆኑም ይህ የደግነት ምሳሌነታችን በተለይም በዚህ የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ በጸናበትና ሁሉም ወገን የችግሩ ተጋላጭ ሆኖ በተገኘበት በአሁኑ ጊዜ ያለውን ለሌለው በማካፈል ይበልጥ ደግነታችን ጐልቶ እንዲታይ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ እንደምንገኝ የተገነዘበው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሁላችንም ባለን ነገር ሁሉ በመረዳዳት ይህን ፈታኝ ጊዜ እንድናልፈው ጥሪውን ያቀርባል፡፡

5. ከዚህም ጋር ዜጋው እንደ ሀገር በሁለት እግሩ ቁሞ ሕልውናው ተጠብቆ ሊኖር የሚችለውና አገራዊ ልማትም ሆነ ሕዝባዊ ዕድገት ሊመጣ የሚችለው በሁሉም ዘንድ ሰላምና አንድነት መግባባትም ጭምር ሲኖር እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ሆኖም በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል እየታየ ያለው አለመግባባትና የቃላት መወራወር በአጭሩ ካልተገታና ወደ መግባባት በመምጣት መፍትሔ ካልተበጀለት ተጨማሪ አገራዊ ቀውስ ሊያስከትል፣ ከፍተኛም ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል በመገንዘብ የሚመለከታችሁ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ለአገራዊ ሰላምና ለሕዝባዊ አንድነቱ በጋራ እንድትቆሙ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

6. አገራችን ኢትዮጵያን ለከፍተኛ ዕድገት ያበቃል ሕዝባችንን ከድህነት አረንቋ ያወጣል በሚል እምነት ከረጅም ጊዜ አንስቶ ሕዝባችን ትኩረት ሰጥቶ ምንም ሳይኖረው ጦሙን እያደረ አስተዋጽኦ በማድረግ እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሰው የህዳሴ ግድባችን አብዛኛው የግድቡ ሥራ እየተጠናቀቀና ወደ ፍጻሜውም እየደረሰ መሆኑን ስለተገለጸ ጉባኤው በከፍተኛ አድናቆት ተመልክቶታል፡፡ በቀጣይም የግድቡን ፍጻሜ ለማየት፣ የመላውን ሕዝባችን ርብርብ እንደሚጠይቅ ግንዛቤ የተወሰደ በመሆኑ እንደአባቶቻችን ለትውልድ የሚተርፍ ታሪክ ለመሥራት ሕዝባዊ አንድነቱና ተሳትፎው እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
በመጨረሻም ከግንቦት 4 እስከ ግንቦት 6 ቀን ለ3 ቀናት ያህል በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊና ማህበራዊ፣ እንዲሁም አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሲነጋገር የቆየው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጠናቅቆ በዛሬው ቀን በጸሎት ተዘግቷል፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top