የኢትዮጵያዊቷ እናት የምህረት ጥሪ ~ ከአሜሪካ
(ታምሩ ገዳ/ህብር ራዲዮ)
የባህር ማዶ ኑሯቸውን ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ለማድረግ እ.ኤ.አ 2013 ወደ አሜሪካው የሚኒሶታ ግዛት የተጓዙት ወ/ሮ አማሪያ ሺፋ ብዙዎች የምቾት እና የብልጽግና አገር የሚሏት አሜሪካ እጆቿን ዘርግታ አልተቀበለቻቸውም።
ወ/ሮ አማሪያ የአሜሪካን ግዛትን በረገጡ ከአንድ አመት ቆይታ በሁዋላ ከባለቤታቸው ከአቶ ሀቢቢ ተሰማ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ወ/ሮዋ ባለቤታቸው በመግደል ወንጀል ተከሰው አምስት አመት ተፈርዶባቸው እስራታቸውን ባለፈው አመት አጠናቀዋል።የሚኒሶታ ግዛት የኢሚግሬሽን ተቋም ግን ወደ አገራቸው ኢትዮጵያ እንደሚመልሳቸው በመወሰኑ ዛሬም ቁርጡ ባለየለት ሁናቴ በእስር ቤት ይማቅቃሉ። ወ/ሮ አማሪያ ግንሪች ፊልድ በተባለው ስፍራ በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ ባለቤታቸው “በቤት ውስጥ አስሮ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲፈጽምብኝ በመቆየቱ እራሴን ለመከላከል በወሰድኩት እርምጃ ገደልኩት፣ ባደረኩት ወንጀል በእጅጉ ተጸጽቻለሁ፣ያንን ድርጊት ባልፈጽመው በወደድኩ ነበር ። ወደ አገሬ ከተመለስኩኝ በባለቤቴ ቤተሰቦች የበቀል እርምጃ ሊወሰድብኝ ይችላል፣ህይወቴ አደጋ ላይ ነው የሚወድቀው ” ሲሉ ይሞግታሉ።
የልጆቻቸው አባትን ” እራስን በመከላከል ሳይሆን ከመጠን ባለፈ ወደ ሰላሳ ጊዜያት በመደብደብ ገድለዋል ” የሚለው ከሳሽ አቃቢ ህግ ወ/ሮ አማሪያ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በሚለው አቋሙ ጸንቷል። የሟች ወንድም የሆኑት አቶ አህመድ በበኩላቸው “ወንድሜን የገደለችው በቅናት ተነሳስታ ነው” በማለት ቀደም ሲል እንባ የተቀላቀለ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ባለፈው አመት ከታሰሩበት እስር ቤት በስልክ አማካኝነት የሚኒሶታ የይቅርታ ሰሚ ቦርድ ተማጽኖ ያቀረቡ ሲሆን ቦርዱ በወቅቱ ውሳኔውን በይደር ቢያቆየውም የሚኒሶታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፍትህ ሹም የሆኑት ሎሪይ ግልዲይ በበኩላቸው ወ/ሮ አማሪያን ይቅርታ እንደማይፈቅዱላቸው ቀደም ሲል ገልጸዋል ። ቦርዱ የምህረት ጥያቄውን ለመጀመሪያ ጊዜ ለማየት የፊታችን ግንቦት /ሜይ 22 ቀን 2020 እኤአ የጊዜ ቀጠሮ የቆረጠ ሲሆን ምህረት ለማግኘት ወ/ሮ አማሪያ የቦርዱ አባላት ሙሉ በሙሉ ይሁንታ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል። በፍትህ ሹም ውሳኔ ቅር የተሰኙት እና ወደ ኢትዮጵያ ለመጠረዝ በአፋፍ ላይ የሚገኙት ወ/ሮ አማሪያ ባለፈው ሀሙስ የሚኒሶታ አገረ ገዢ እና ከሶስቱ የቦርዱ አባላት አንዱ የሆኑት ቲም ዋዝ በጉዳዩ ጣልቃ አንዲገቡበት የተማጽኖ አቤቱታ አቅርበዋል።
ለህግ ታራሚዎች ምህረት ማድረግ በአሜሪካ ግዛቶች በብዙ የተለመደ ባይሆንም በአመት ከአንድ መቶ በላይ ታራሚዎችን በይቅርታ ከሚለቀው የአላባማ ግዛት እና በግምት ከሃያ ለማይበልጡ በቀላል ወንጀል ለተከሰሱ ታራሚዎቾች ይቅርታ ከሚያደርገው ሚኒሶታ ጋር ሲነጻጸር የወ/ሮ አማሪያ የምህረት ጥያቄ ምን ያህል ውጣ ውረድ አንደሚኖረው መገመት አያዳግትም።
በሚኒሶታው ዪኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና የህግ ፕሮፌሰር የሆኑት ዴቪድ ሻልቴዝ ወ/ሮ አማሪያ ለሀገረ ገዢው ያቀረቡት የጣልቃገብነት ጥያቄ ብዙም አውንታዊ ምላሽ ሊያመጣ እንደማይችል ከሚገምቱት ባለሙያዎች መካከል አንዱ ሲሆኑ ” ይህንን መብት ለአገረ ገዢው የሚሰጥ እና የአቤት ባይዋን ጥያቄ እውን የሚያደርግ ህገመንግስታዊ አንቀጽ በግልጽ ያለ አይመስለኝም”ብለዋል።
የቀድሞው የግዛቲቱ አቃቢ ህግ የነበሩት ማይክ ሃትቺ እንዲሁ “ወ/ሮ አማሪያ ከባድ ፈተናዎችን አልፈዋል ፣አሁንም ቢሆን ይሄው ችግርን ነው የሚጋፈጡት በማለት በእርሳቸው ዘመን ይቅርታ የተደረገላቸው ሰዎች ከአደንዛዥ እጽ ጋር በተያያዘ የተፈረደባቸው እንጂ አመጻ (ቫዮለስን) አለማካተቱን በማውሳት የምህረት ጥያቄው አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚገባ ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል።