Connect with us

አንቺ የሀገር እናት ነሽ …

አንቺ የሀገር እናት ነሽ

ባህልና ታሪክ

አንቺ የሀገር እናት ነሽ …

አንቺ የሀገር እናት ነሽ፡፡ የወለዱትን ማሳደግ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ እናት ለሌለው ሁሉ እናት መኾንና መከራን አይቶ ማሳደግ ግን ጸጋ ነው፡፡

አንቺ ኢትዮጵያዊ ጸሐይ እንኳን አደረሰሽ፡፡
******
ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

እናት ናትና እድሜዋን ቆጥሬ አንቱ አልላትም፡፡ እሷ ብርቱ ሰው ናት፡፡ እሷ የኢትዮጵያዊት ደግ እናት ታላቅ ምሳሌ ናት፡፡ ልቧን ለሀገር ሰጥታለች፡፡ የሀገር እናት ኾናለች፡፡ ስሟ የደግነት ቅጥያ ነው፡፡ አበበች ጎበና የሚለው ቃል በሀገሬ ደግ እናት የሚለውን የሚወክል ያኽል ልዩ ስፍራ ይዟል፡፡

ዛሬ በመላው ዓለም የሚገኙ እናቶች ቀናቸው ነው፡፡ እናቶቻችንን እያመሰገንን ነው፡፡ የየራሳችንን እናት አስታውሰናል፡፡ ሁላችንም የምናስታውሳት የጋራ እናታችን ደግሞ አንቺ ነሽ፡፡ ብዙ ትውልድ ስምሽን ከምግባርሽ ጋር አቆራኝቶ መታደልሽን ሲያወድሰው ይኖራል፡፡

እናትነት ስጦታ ነው፡፡ ለወለደችው የምትንሰፈሰፍ እናት እንዲህ የሚያደርጋት ምስጢር የተፈጥሮ ነገር ነው፡፡ ለወለዱት መኾን በብዙ ከተፈጥሮ ይቆራኛል፡፡ የእናት ወጉም እንዲህ ነው፡፡ ላልወለዱት መኖር ግን ጸጋ ነው፡፡ እናት ላጣ እናት ኾኖ የእናትን ክብር በኢትዮጵያዊ ፍቅር አድምቆ መጻፍ መሰጠት ነው፡፡

አንቺ የሀገር እናት ነሽ፡፡ ሀገር የጣለውን አንስተሻል፡፡ ወገን ፊት የነሳውን ስቀሽ የተቀበልሽ ደግ ነሽ፡፡ መልካምነትን በእናትነት ጉልበት ያሳየሽ ነሽ፡፡ እንኳን ለእናቶች ቀን አደረሰሽ፡፡

የእናቶች ቀን ሲኾን ይኽ ቀን አብልጦ ያንቺ ይመስለኛል፡፡ ደግ ልብ፣ ሩህሩህ መንፈስ ለሰው ተሰቃይቶ ሰው ለሀገር ማብቃት ላንቺ የተሰጡ ግዙፍ ጸጋዎች ናቸው፡፡ ልጇን ከጣለች እናት ላይ ልጇን እንስተሽ በማሳደግ የጥቂት ጨካኝ እናቶችን ሐጢአት በደግነት ድል አድርገሽ ፍቀሽዋል፡፡

አንቺን መሳይ የሀገር እናቶች ሃምሳም መቶም ኾነው እጥፍ እንዲኾኑልን እንመኛለን፡፡ ተስፋ ለቆረጡ እንቡጦች ተስፋን የሰነቀ ለሌላው ተጠብሶ የመኖርን ግዙፍ መልካምነት አሳይተሻል፡፡ አንቺ ኢትዮጵያዊት እናት፤ አንቺ መልካም የማድረግ ምሳሌ፤ አንቺ ኢትዮጵያዊ ጸሐይ እንኳን አደረሰሽ፡፡

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top