ኢዜማ – በአንድ ዓመት አንድ ትልቅ ግብ ያሳካ ፓርቲ!
(የሺዋስ አሰፋ)
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፖርቲ:-
-በዜግነት ላይ የተመሰረተ፣
-ከምርጫ ወረዳ ጀምሮ የተደራጀ፣
-መንግስት እና ፓርቲን በአደርጃጀት የለየ፣
-ቀደም ሲል የነበሩ ፓርቲዎችን አክስሞ ያዋሃደ፣
-በሀገራችችን ማህበራዊ ፍትህን ለማስፈን ያለመ፣
ህዝባችን በመረጠው መተዳደር እንዲችልና ሀገራችን እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲኖራት አራት ትልልቅ ስትራተጂክ ግቦችን አፅድቆ የተነሳና እነሱን ለማሳካት ትኩረቱ ሁሉ ሥራ ላይ ብቻ የሆነ ከልቡ ፓርቲ ነው።
ግቦቹም:-
ግብ ፩: ዘመናዊና ዘመን ተሻጋሪ የፓርቲ አደረጃጀት፣
ግብ ፪: አገር ለመምራት ብቁ የሆነ መንግስታዊ መዋቅር፣
ግብ፫: መንግስት ለመመስረት የሚያስችል የፓርላማ ወንበር በምርጫ ማሸነፍ እና
ግብ፬: ከሁሉ አስቀድሞ እና በሁሉም ደረጃ ለአገር ሰላም እና ለህዝብ መረጋጋት መስራት ሲሆኑ፣ በተረጋጋ፣ በሰከነና ኃላፊነት በሚሰማው ሁኔታ ከምስረታው ጀምሮ ለአገር ስላምና ለእውነተኛ ሽግግር እየሰራ ነው፣ ወደፊትም ለአገራዊ እርቅ የሚረዱ ተዓምራዊ ተግባራትን ግለሰቦችም ይሁን ከስብስቦች ጋር በግንባር ቀደም ተነሳሽነት ይሰራል።
አገር መምራት የሚያስችል ብቁ መንግስታዊ መዋቅር በማዋቀርና የፖሊሲ ሰንዶችን በማዘጋጀት ረገድ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል፣ ከዚህ በኋላ ገዢዎች ከኛ ውጭ ሌላ ብቃት ያለው ፓርቲ የለም ሊሉ አይችሉም – ኢዜማ ትልቅ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ተጠባባቂ መንግስትም ነው። በምርጫ ማሸነፍም ከላይ ያሉትን ግቦች ካሳካንና በተለይም የአገር ሰላም መሆን ከተረጋገጠ በኋላ የምንደርስበት ግብ ነው።
ኢዜማ ዘመናዊና ዘመን ተሻጋሪ የፓርቲ አደረጃጀት መመስረት የሚለውን ግቡን ሙሉ በሙሉ ያሳካ መሆኑን በልበሙሉነት መናገር እችላለሁ። ኢዜማ ግልፅ ደንብና መመሪያዎች፣ ፕሮግራምና ፖሊሲዎች ያሉት፣ በአገር ውስጥ ባሉ የምርጫ ወረዳዎችና በውጭ አገራት ከተሞች መዋቅር ያለው፣ በርካታ ጽ/ቤቶች ያሉትና ለዜጎች ቅርብ የሆነ፣ በሃሳብ፣ በሃብት፣ በሰው ኃይልና በመዋቅር የደረጀ ግዙፍ ፓርቲ ሆኗልና የኢዜማ አባል በመሆኔ እኮራለሁ።
ከምስረታ በፊት፣ በምስረታ ወቅት ብዙ የደከማችሁ የኢዜማ መስራች አባላት ጥረታችሁ ሰምሯል፣ ልፋታችሁ ግቡን መቷል፣ ኢዜማ የኢትዮጵያ ህዝብ ተስፋ ሆኗልና እንኳን ደስ አላችሁ። እንኳን ለኢዜማ ፩ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አደረሳችሁ።
ለእኔ ደግሞ ከነዳንኤል ሺበሺ ጋር ከቃሊቲ እስር ቤት የተፈታንበት ቀን ስለሆን በዓሉ እጥፍ ድርብ ነው።
በዓላችንን ያለንበት ሁኔታ ከግምት በማስገባት እናክብረው። በያላችሁበት ራሳችሁንና ህዝባችሁን ከኮሮና ወረርሽኝ ጠብቁ። ሰላም!