Connect with us
ፍቷቸው?!
Photo: Social media

ህግና ስርዓት

ፍቷቸው?!

ፍቷቸው?! | (ጫሊ በላይነህ በድሬቲዩብ)

የአቶ በረከት ስምኦን እና የአቶ ታደሰ ካሳ ክስ ጉዳይ ትላንት እልባት አግኝቷል። እንደሰማነው አቶ በረከት ስምኦን በስድስት ዓመት፣ አቶ ታደሰ ካሳ በስምንት ዓመት እሥራት ተቀጥተዋል።

ሰዎቹ ከአያያዛቸው እና ከቀረበባቸው የተጋነነ ክስ እና ወሬ አንፃር ስመዝነው ፍርዱ አነስተኛ ነው። ይኸም ሆኖ በፍርድ ቤት ሥራ ጣልቃ ገብቼ “ፍርድ አነሰ” የሚል ሙግት ውስጥ የመግባት ፍላጎት የለኝም።

ግን በእነአቶ በረከት ላይ ክስ ሲጀምር “በቀል ነው” ከሚሉ ወገኖች በቀጥታ ባልደመርም ሀሳባቸውን አልተቃወምኩም። አሁንም “አንዳች በቀል ተፈፅሞባቸው ይሆን” ብዬ ማሰቤን የማቋርጥበት ተጨባጭ ምክንያት አላገኘሁም።

እንደአንዳንድ የዋህ ብሎገሮች “በረከት በሙስና አይታማም” እያልኩኝ ላዝግህ አልፈልግም። በተለይ በረከት ለረጅም ጊዜያት እንደልቡ የሚያዝበት፣ ኦዲት የማይደረግ የፓርቲ ልሳናት ገንዘብ በእጁ እንደነበረ አውቃለሁ። የእነጥረትም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። ይኸ መሆኑ በራሱ ለሙስናና ብልሹ አሰራር በር ይከፍታል ብዬ ዲስኩር ባሰማህ አይመጥንህም። በረከት “የራሴ ቤት እንኳን የለኝም” ብሎ እንደሌሎቹ አስመሳይ ሹማምንት ያልቅስ እንጂ በፍርድ ቤት የቀረበበትን ክስ በበቂ ሁኔታ መከላከል ባለመቻሉ ጥፋተኛ መባሉን መካድ አይቻልም።

አሁን ጥያቄው በፍትህ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው። በፍትህ አለም አድልኦ ካለ ፍርድ ሚዛኑን ይስታል። አሁንም ጥያቄው በኢህአዴግ ወይንም በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ የተጠለሉ ሌባ አመራሮች የሉም ወይ የሚለው ነው። እነሱ ባሉበትና ባልተጠየቁበት ሁኔታ ሁለት ግለሰቦችን ነጥሎ፣ ሐጢያታቸውን ቆልሎ ከስሶ ማስቀጣት ፍትህን ያሳያል ወይ የሚለውን መመለሱ ላይ ነው።

የህግ ሰዎች የቅጣት አላማው ማስተማር ነው ይላሉ። አስተማሪ ግን የሚሆነው ሁሉም አጥፊዎች በህግ ፊት እኩል መሆን ሲችሉ ነው። “ተደምረናል” ያሉ ጮሌ ሌቦች የማርያም መንገድ የሚያገኙ ከሆነ ፍትህ አፈር መልበሷ አይቀሬ ነው። በእነበረከት ጉዳይ የሆነው ይኸው ይመስለኛል።

ህዝብ በሌብነታቸው፣ በሰብአዊ መብት ረጋጭነታቸው የሚያውቃቸው ግለሰቦች በለውጥ ሀይሉ ተጨማሪ ሹመትና አድናቆት ሲሰጣቸው በአይኑ በብረቱ ደጋግሞ አይቷል፤ ሰምቷል። ይኸን እያየም “የእነአቶ በረከት እስር ፓለቲካዊ አይደለም፤ ሙስና ነው” ብሎ እንዲቀበል መጠበቅ ህዝብን አለማወቅ፣ ሲብስም መናቅ ይሆናል።

በዘመነ ኢህአዴግ ከተራ የጉቦ መቀበል እስከከፍተኛ የመሬት ቅርምትና ንግድ ድረስ እጃቸውን ያስገቡ፣ አንዳንዶች ከገቢያቸው በላይ ሐብት አፍርተው በአደባባይ የሚፏልሉ ሹማምንት ሞልተው በተረፉበት ሁኔታ ሁለት ግለሰቦችን ነጥሎ በሙስና መክሰስ ፍትህን አያሳይም።

በግሌ መንግሥት በውስጡ የተሰገሰጉ ሌቦች ማራገፍ ባልቻለበት፣ አቅምና ተነሳሽነት ባጣበት ሁኔታ የሁለት ግለሰቦች የሙስና ክስ በፍትህ ላይ መሳለቅ ነው ባይ ነኝ።

የለውጥ ሀይሉ በሙስና ጉዳይ ሁለት አማራጭ አለው ብዬ አምናለሁ። አንዱና ዋናው ሌባ አመራሮችን ከላይ እስከታች መንጥሮ ለህግ ማቅረብ ነው። ይህ የማይቻል ከሆነ ያለፈውን የሌብነት አስነዋሪ ፋይል በይቅርታ ዘግቶ ወደፊት መራመድ ነው።

በግሌ፤ እነአቶ በረከት ተገቢውን ቅጣት በማግኘታቸው በአንፃሩ ሌሎች በህዝብ ሀብት የከበሩ ሌቦች በዝምታ የታለፉበት ሁኔታ በመኖሩ ይቅር ባይነት አስፈላጊ ነው እላለሁ። ደግሞም ስፍር ቁጥር የሌለው የመንግሥት ሌቦች፣ህገወጥ ሀብት ባፈሩበትና ያለአንዳች ጠያቂ ቆመው በሚሄዱበት አገር የሁለት የግለሰቦች “በሙስና” መታሰር ትርጉም ስለማይኖረው በይቅርታ ህጉ መሰረት ቢፈቱ እና እንዲህ አይነቱ አድሎአዊ የክስ ዶሴ በይቅርታ ቢዘጋ ስል በግሌ መፍትሔ እጠቁማለሁ። የፌደራሉም ሆነ የአማራ ክልል መንግሥት እንደሚሰሙኝ አምናለሁ።

ደህና ክረሙልኝ?!

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top