መንግስት የሀገርንና የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ ሲል ህገ መንግስቱን የሚጥሱ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ላይ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚገደድ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በዛሬው እለት ባስተላለፉት መልእክት፥ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ጎልተው ከወጡ የህዝብ ፍላጎቶች አንዱ ህዝብ የሚሳተፍበትና የሚሰማበት የአስተዳደር ወይም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመገንባት ፍላጎት ነው ብለዋል።
ይህ ፍላጎትም እያደገ ዛሬ ላይ መድረሱንና በዚህ ትውልድም ይህንን የበለጠ ለማጎልበት የሚረዳ ኩነት ቀጣዩ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ መሆኑንም አንስተዋል።
ለዚህም በርካቶች ምርጫውን በጉጉት ሲጠብቁት ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ አንዳንድ ፓርቲዎችና ልሂቃን ምርጫው መደረግ የለበትም የሚል አቋም በያዙበት ጊዜ መንግስት ግን ሀገራዊ ፋይዳውን በመረዳት ምርጫው በጊዜው መካሄድ እንዳለበት አምኖ ሲዘጋጅ ነበር ብለዋል።
ሆኖም በኮሮናቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝ ሳቢያ ምርጫውን ቀድሞ በተያዘለት ሰሌዳ ማካሄድ እንደማይችል በህግ ብቸኛ ስልጣን የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 22 ቀን 2012 ማስታወቁንም አስታውሰዋል።
በዚህም ምክንያት ምርጫውን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ የግድ መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የምርጫ መተላለፍ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የዓለም ሀገራትም ምርጫን ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ ስፖርታዊ ሁነቶች መሰረዝ ማስከተሉንም በምሳሌነት እንስተው አብራርተዋል።
ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ማካሄድ እንደማይችል ከገለፀበት ጊዜ ጀምሮም መንግስት የተለያዩ አማራጮችን በህግ ባለሙያዎች ሲያስጠና መቆየቱን በመግለፅ፥ የህግ ባለሙያዎችም ምርጫው መተላለፍ የሚችልበትን የህግ አማራጮችን ማቅረባቸውንና በዚህም ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል ብለዋል።
ይህንን ተከትሎም የፌደራሉ መንግስት ከፍተኛ የስልጣን አካል የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በጉዳዮ ላይ ህገ መንግስታዊ ትርጓሜ እንዲሰጥበት ለህገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ መምራቱንም ገልፀዋል።
የቀረቡትን አማራጮች ተከትሎ በርካቶች የተለያየ ሀሳብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ ገንቢ ሀሳብ ለሚያቀርቡት ምስጋና አቅርበው፤ ሆኖም ግን አማራጮቹ ተቀባይነት የላቸውም፣ ህገ መንግስቱ የሚተረጎም አንቀጽ የለውም በሚል የሽግግር መንግስት ሀሳብ ያቀረቡ መኖራቸውንም አንስተዋል።
ህገ መንግስቱ የሚተረጎም አንቀጽ የለውም የሚለው ክርክር አውቆ ላለማወቅ ከወሰነ አካል ወይም ጥልቅ የሆነ አላዋቂነት ውስጥ ከተዘፈቀ ሰው የሚቀርብ ሀሳብ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አክለውም አሁን ያለው መንግስት ህግ የሚያወጣ፣ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችን የሚፈርም፣ በጀትና እቅድ የሚያፀድቅ ህጋዊ መንግስት መሆኑን በመጥቀስ፤ ብልፅግና ፓርቲም በመላ ሀገሪቱ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም መዋቅር ያለው፣ ሀገራዊ ለውጡን በመምራት የበርካቶችን ድጋፍ ያገኘ ግዙፍ ፓርቲ ነውም ብለዋል።
ህጋዊ በሆነ አግባብ የኮቪድ-19 ስጋት እስኪቀረፍ እና ቀጣዩ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ደግሞ ሀገር የማስተዳደር ኃላፊነት ያለው ፓርቲ መሆኑንም ገልፀዋል።
ያለ ምርጫ እንዲሁ ተጠራርቶ ስልጣን የመከፋፈል ህጋዊም ሆነ ህገ መንግስታዊ አግባብ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስልጣን ይገባኛል የሚለው ፈሊጥ ዴሞክራሲያዊም ህገ መንግስታዊም አይደለም ብለዋል።
ህገ መንግስቱ ከደነገገው ውጪ በህገወጥ ምርጫ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ እንቅስቃሴ ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በመግለፅ፤ እንዲህ አይነቱ እንቅሰቃሴ የኢፌዴሪ ህገ መንግስትን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሀገሪቱንና ዓለም አቀፍ ህጎችን የሚጥስ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በአንቀፅ 50 የፌደራል መንግስት ስልጣንና ተግባር ሲዘረዝር ቁጥር አንድ አድርጎ ያስቀመጠው ህገ መንግስቱን የመጠበቅና የመከላከል ኃላፊነት ነው፤ ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነን ሲሉም ገልፀዋል።
በህገ መንግስቱና በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ ካልሆነ በስተቀር የጨረባ ምርጫ ለማድረግ መነሳት ሀገርንና ህዝብን ለከፋ አደጋ የሚዳርግ በመሆኑ፤ መንግስት ሀገርንና የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳልም ብለዋል።
ስልጣን የሚፈልጉ የፖለቲካ ሀይሎች የሀሳብ ክርክሮቻቸው ወጣቱንና እናቶችን በማይጎዳ መልኩ እንዲያደርጉት ይመከራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስር ዶክተር ዐቢይ፥ ፖለቲከኞች ስልጣን እንዲይዙ ወጣቶች ማለቅ፣ እናቶች ማልቀስ፣ ቤቶች መፍረስና ህዝቦች መፈናቀል የለባቸውም ብለዋል።
የከሮናቫይረስ ስጋት ተጋርጦብን፤ የሀገር ሉአላዊነትና ደህንነት ለአደጋ ተጋልጦ ባለበት ጊዜ ስልጣንን ያለ ምርጫ እና ከህግ አግባብ ውጪ በሁከትና በብጥብጥ ካልሰጣችሁኝ ሀገር አተራምሳለው የሚል ማንኛውንም ሀይል መንግስት እንደማይታገስ በማሳሰብ ፤ ለዚህም በሁሉም ረገድ ዝግጁ ነን ሲሉም ገልፀዋል።(ፋና)