Connect with us

“የናይል ስጦታዋ” ግብፅ ያልተነኩ ሌሎች የውሃ አማራጮች

"የናይል ስጦታዋ" ግብፅ ያልተነኩ ሌሎች የውሃ አማራጮች

ማህበራዊ

“የናይል ስጦታዋ” ግብፅ ያልተነኩ ሌሎች የውሃ አማራጮች

“የናይል ስጦታዋ” ግብፅ ያልተነኩ ሌሎች የውሃ አማራጮች ።
——–
“የናይል ስጦታ” በመባል የምትታወቀው ግብፅ 90% የውሃ ፍላጎቷን የምታሟላው ከዚሁ አንድ ለናቱ ከሆነው ወንዝ በመሆኑ *እስካሁን ባለው ሁኔታ* ናይል/አባይ ህልውናዋ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም ። ነገር ግን ፥ የግብፅ “የናይል ስጦታነት” በጊዜ ሂደት ”የወንዙ ብቸኛ ባለቤት ነኝ” ወደሚል ተቀይሮ የላይኞቹን ተፋሰስ ሀገራት ጠብታ ውሃ እንኳን ያላስቀረ ሴራ በቅኝ ወራሪዋ እንግሊዝ ፊታውራሪነት መፈፀሙ በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል ።

((እዚህ ጋ የ1929ን አንግሎ-ሱዳን እና የ1959ን የግብፅ-ሱዳን ስምምነቶችን ማየት ይቻላል ። በ1959ኙ የሁለትዮሽ ስምምነት መሠረት ከአጠቃላዩ 84 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር (ቢ.ኪ.ሜ.) ዓመታዊ የውሃ ፍሰት መጠን ፥ ግብፅ 55.5 ቢ.ኪ.ሜ ፣ ሱዳን 18.5 ቢ.ኪ.ሜ ፣ ቀሪው በትነት የሚባክን ሲሆን ፤ የወንዙን 85% የምታመነጨው ኢትዮጵያ ግን ድርሻዋ ዜሮ መሆኑን ልብ ይሏል))

ከላይ የተገለጸው የተዛባ አመለካከት እንዳለ ሆኖ ፥ ግብፅ ሌሎች የውሃ አማራጮች እንዳሉዋት ማየት ይቻላል ።
በአፍሪካ ግዙፍ የሚባል የከርሰ-ምድር ውሃ ክምችት በሰሜን አፍሪካ ውስጥ (ማለትም በግብፅ ፣ ሱዳን ፣ ቻድ እና ሊቢያ) እንደሚገኝ ጥናቶች አረጋግጠዋል [1] ። ይህ የኑቢያ አኩፈር (aquifer) በመባል የሚታወቀው 2.6 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎሜትር ስፋት የሚሸፍን ሲሆን 150,000 ኪዩቢክ ኪሎሜትር ያህል የከርሰ-ምድር ውሃ ይይዛል ተብሎ ይገመታል [4]።

የዚህ የኑቢያ አኪዩፈር አብዛኛው ክፍል ግብፅ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ፥ ግብፅ አሁን በምታገኘው ዓመታዊ የውሀ መጠን ቢሰላ እንኳን ለ500 ዓመታት ሊያስኬድ የሚችል የውሃ ሀብት መሆኑን ባለሞያዎች ያስረዳሉ ። (የግብፅ የከርሰ-ምድር ውሃ ሀብት ከኢትዮጵያ ጋር ሲነጻጸር በብዙ እጥፍ ይበልጣል [2,3]) ። ሆኖም ግን ፥ ይህንን ግዙፍ የውሃ ሀብት ግብፅ እስካሁን ድረስ እምብዛም አገልግሎት ላይ አላዋለችውም (8% ያህል ብቻ ጥቅም ላይ ውሏል [2]) ።

ከከርሰ-ምድር ውሃ ሀብቷ በተጨማሪ ሌላ አማራጭ የውሃ አቅርቦት ከቀይ ባህር እና ከሜዲትራንያን ባህር ማግኘት ትችላለች ። ጎረቤቷ እስራኤል የሜድትራንያንን ባህር ውሃ ጨዋማነቱን በማስወገድ ለመስኖና ለተለያየ ፍጆታ እንደምታውል ይታወቃል ።
እንዲህ ያሉ አማራጮች እያሉዋት በአንድ ወንዝ ላይ ብቻ ተንጠልጥላ “ዋ! ውሃዬን ትነኪና…” ስትል ለዘመናት የኖረችው የግብፅ መሠረታዊ ጥያቄ የውሃ ድርሻ ጥያቄ ሳይሆን “ኢትዮጵያ ግድብ ሰርታ ልትቆጣጠረን ነው” ወይ “ደለል አፈሩ ይቀርብኛል” ወይም ሌላ እንድምታ ያለው ይመስላል ። (* ግብፅ የናይልን ወንዝ ለራሷ ከመጠቀምም አልፋ በሲናይ በረሃ በኩል አሻግራ ለሌሎች ሀገራት እንደምትሸጥ ይታወቃል)

ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ 112 ሚሊየን ገደማ ደርሷል ፤ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረም ነው ፤ በህዝብ ብዛት ከዓለም ሀገራት 12ኛ ነን ። ለዚህ ህዝብ ውሃ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ እና የውሃ ፍላጎቱ ከሚገመተው በላይ እየጨመረ እንደሚሄድ ግልጽ ነው ። ምንም እንኳን ሀገራት ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ለግብፅ ወግነው ግልፅ የሆነ አድልኦ ቢያረጉብንም ፥ ተደራዳሪዎቻችን ኢትዮጵያ በሀብቷ የመጠቀም መብቷን አስከብረው ታሪካዊ ኃላፊነታቸው ይወጣሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ።
—–
ያዕቆብ አለማየሁ
(ቅዳሜ ፤ የካቲት 28/ 2012 ዓ.ም)
—–
ዋቢ ጽሁፎች/ካርታዎች
[1] British geological survey. Digital groundwater map of Africa
[2] https:// water.fanack.com/egypt/water-resources/
[3] Berhanu B., Seleshi Y., Melesse A. (2014) Surface Water and Groundwater Resources of Ethiopia. In: Melesse A., Abtew W., Setegn S. (eds) Nile River Basin. Springer
[4] International groundwater assessment center. Nubian Aquifer. https://groundwaterportal.net/project/nubian-aquifer

Click to comment

More in ማህበራዊ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top