የኮሮና አስከፊ ጉዳት በሰኔ እና ሐምሌ ወራት ሊታይ ይችላል
በኢትዮጵያ ከፍተኛ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዋች ቁጥር እና የከፋ ጉዳት ሊደርስ የሚችለው ሰኔ መጨረሻና ሐምሌ መጀመርያ ቀናት ላይ መሆኑን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።
መንግስት የኮሮና መከላከያ እርምጃዎችን ባይወስድ ኖሮ ከ27 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በኮሮና ቫይረስ ይጠቁ እንደነበርም ተገልጿል። ጤና ሚኒስቴር ወረርሽኙ ሊያደርስ የሚችለው የከፋ ውጤት ገና አላለፍነውም፤ እንደ ኮሮና ወረርሽኝ አንድ ሀገር ገብቶ የሚብስበት ጊዜ ገና የሚመጣ ነውና መዘናጋት አደገኛ ነው ብሏል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የጤና ነክ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ያዕቆብ ሰማን እንደተናገሩት ፤ አንድ ወረርሽኝ የስርጭት ጣርያው ላይ ለመድርስ በአማካይ አስር ሳምንት ወይንም 3 ወር ይፈልጋል፤ እኛ አንድ ወር ከ ሁለት ሳምንታችን ስለሆነ አስከፊው ነገር ገና ከፊታችን ነው ብለዋል ፡፡
ጥናታችን እንደሚያሳየው በሀገር አቀፍ ደረጃ አሁን የምናደርገውን ጥንቃቄ ባናደርግ ከ 27 ሚሊዬን በላይ ህዝብ ኮሮና ያጠቃብን ነበር የሚሉት ዶ/ር ያዕቆብ በደንብ ከተጠነቀቅን ደግሞ የዚህን ቁጥር 60 በመቶ ወይንም 13 ሚሊዮን መቀነስ ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ያዕቆብ ኮሮና ቫይረስ በሀገራችን ሊያደርስ የሚችለው ከፍተኛውን ጉዳት የሚያደርስበት ወቅት ሰኔ መጨረሻና ሀምሌ መጀመርያ ላይ ነው፡፡
በታሪክ የተከሰቱ ወረርሽኞችም ለምሳሌ የህዳር በሽታ የዝናብና የብርድ ወቅት መውጣትን ተከትሎ ነው የስርጭታቸው ከፍታ ላይ የደረሱት ያሉ ሲሆን ከቅርብ አመታት ወዲህ ዝናብ ቀደም ብሎ ሚያዚያ፣ግንቦት ላይ እየጀመረ ስለሆነ የሰኔ የመጨረሻ ሳምንትና የሀምሌ የመጀመርያ ሳምንት ሊከፋ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ኮሮና ሀገራችን ገባ ሲባል ድንጋጤው ህዝቡም ላይ ብቻ ሳይሆን ፌደራል መንግስትም ክልል መንግስታትም ላይ እንደነበር የምታውቀው የተወሰዱት እርምጃዎችን ስታስታውስ ነው የሚሉት ዶ/ር ያዕቆብ አሁን በኮሮና የሚያዘው ቁጥር ሲያድግ ህዝቡ ብቻ ሳይሆን መንግስትም በቁጥጥር ላላ እያለ እንደሆነ ነው የምታስተውለው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አንዳንድ መፍትሄዎች ቀድመህ በማድረግህ ብቻ ላይሰሩልህ ይችላሉ፤ የወረርሽኙ የከፍታ ወቅት ላይ (እንደ ግምታችን ሰኔ መጨረሻና ሀምሌ መጀርመያ ላይ) ፤ ህዝቡ በጣም እንዲጠነቀቅ ብትፈልግ፤ ሊዳከምና ሊሰላችብህ ይችላል፣ ስለሆነም መቼ በምን ያህል መጠን ነው እንቅስቃሴ የምገድበው፣ እርምጃዎቼን የማጠብቀው የሚለውን ሲወስን መንግስት ባለሙያዎችን ሁሌም ማማከር አለበት ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
(ኢትዮ ኤፍ ኤም)