Connect with us

ለጌታቸው ረዳ ፓርቲ ምርጫ ማለት የአላዲን የመቶ ሜትር ሩጫ ነው

ለጌታቸው ረዳ ፓርቲ ምርጫ ማለት የአላዲን የመቶ ሜትር ሩጫ ነው
Photo: Social media

መዝናኛ

ለጌታቸው ረዳ ፓርቲ ምርጫ ማለት የአላዲን የመቶ ሜትር ሩጫ ነው

ለጌታቸው ረዳ ፓርቲ ምርጫ ማለት የአላዲን የመቶ ሜትር ሩጫ ነው
(አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ)

እስካሁን ያደረግናቸውን አገራዊ ምርጫዎች ሳስባቸው ‹‹The Dictator›› የሚለው አስቂኝ ፊልም ላይ የዋዲያን መሪ የሆነው አላዲን (Supreme Leader) ከመቶ ሜትር ሯጮች ጋር ትራክ ውስጥ ሆኖ ይታየኛል፡፡ አላዲን ታዲያ ትራኩ ውስጥ ማሊያ ለብሶ የተገኘው ከሩጫውም ተሳታፊነት ባለፈ የሩጫው አስጀማሪም ጭምር በመሆን ነበር፡፡ እናም ተወዳዳሪ አትሌቶቹ በቦታቸው ሆነው ተኩስ ሲጠባበቁ አላዲን ተስፈንጠረሮ ሩጫውን ከጀመረ በኋላ ሽጉጡን ላጥ አድርጎ ይተኩሳል፡፡ ተኩሱን የሰሙት አትሌቶችም ሩጫውን በመጀመር ሊደርሱበት ሲሉ ጉልበት ጉልበታቸው በሽጉጥ እየሰበረ ያስቀራቸዋል፡፡

የሚያስገርመው ታዲያ እንዲህም አድርጎ አላዲን የሮጠው አምሳ ሜትር አካባቢ ብቻ ሲሆን ቀሪውን ርቀት መጨረስና የዓለም ሪከርድን መስበር የቻለው… በሩጫው ፍጻሜ ላይ አንደኛ የሚወጣው አትሌት የሚበጥሰውን ገመድ ይዘው የቆሙት ሁለት ሰዎች ወደ እሱ እየሮጡ እንዲመጡ በማድረግ ነበር፡፡

ይሄንን የመቶ ሜትር ሩጫም ወደ አገራችን ምርጫ ስናመጣው… ኢሕአዴግ- በአላዲን፣ በጥይት የሚመቱት አትሌቶች- ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ የሚበጠሰውን ገመድ ይዘው ወደ አላዲን የሚሮጡት ዳኞች ደግሞ ምርጫ ቦርድን ወክለው እናገኛቸዋለን፡፡ አላዲን ሪከርድ ሰብሮ የገባበት ሰዓት ደግሞ የኢሕአዴግን መቶ ፐርሰንት የምርጫ ውጤት ያስታውሰናል፡፡

በመሆኑም በአንጻራዊነት በ1997 ዓ.ም ካደረግነው ምርጫ ውጭ የነበሩት ምርጫዎች መንግሥት ‹‹መቶ ፐርሰንት ተወዳጅ ነኝ›› ብሎ በእኛ አሻራ እራሱን የመረጠባቸው ነበሩ፡፡ የ1997ቱም ቢሆን ሒደቱ ጥሩ ቢሆንም ውጤቱ ግን ቤተ-መንግሥት ይገቡ ዘንድ የመረጥናቸውን የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ወህኒ-ቤት በማስገባት የተጠናቀቀ እንደነበር የሚረሳ አይደለም፡፡

ያለፉትን የምርጫ ዙሮች ትተን አሁን ወዳለንበት ስንመጣ…. ሥልጣን ላይ ያለው ‹‹የብልጽግና ፓርቲ›› ለቤተ-መንግሥቱ ያደረገው እድሳት ከሚሰናበት ሳይሆን ከሚሰነብት መንግሥት የሚጠበቅ ቢሆንም… ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን የምርጫ ቦርድ አድርጎ መሾሙ፣ ለተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሆነ ለዜጎች የፈጠረው ስነ ምህዳር የሚያፍን አለመሆኑ፣ እና የመሳሰሉት ነገሮች የተሻለ ምርጫ ይኖራል ብለን እንዲናስብ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ፍጻሜውን ካላበላሸው በቀር ጅማሬው መልካም የሚባል ነው፡፡

ሆኖም ግን አገሪቱ ላይ ካለው አለመረጋጋትና ከበሽታ ክስተት ጋር ተያይዞ ምርጫው የሚደረግበት ጊዜ እንዲራዘም ቢደረግም ህውሓቶች ግን አገራዊ ምርጫው በተያዘለት ጊዜ የማይካሄድ ከሆነ እንደ ድርጅት በክልላቸው ምርጫውን እንደሚያስኬዱ እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ የሚገርመው ነገር ታዲያ ህውሓቶች ስለ ምርጫ የሚያወሩን በዚያው የአላዲን አስተሳሰባቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ላይ ሲተገብሩት የኖሩትንና ምርጫ የሚል ሥም የሰጡትን ‹‹የእቃቃ ጨዋታ›› ትግራይ ላይ ለመድገም፣ ብሎም ከምርጫ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ይከሰታል ብለው የሚያስቡትን አስፈሪ ድባብ በማለም ነው፡፡

ትናንት ከአጋር ድርጅቶች ጋር ተባብረው ‹‹አማራጭ የለሽ ምርጫ›› በማዘጋጀት የኢትዮጵያን ሕዝብ መቶ ፐርሰንት የምርጫ ውጤት ሲግቱት እንደኖሩት ሁሉ… ያችኑ የህጻናት ጨዋታቸውንና 100% ውጤታቸውን ክልላቸው ላይ ለመተግበር ነው ይህ ሁሉ ጥድፊያ፡፡

እንጂማ ይህ አስተሳሰባቸው ለዲሞክራሲያዊ ምርጫና ለሕገ-መንግሥቱ መከበር ካላቸው ቀና አመለካከት የመነጨ ቢሆን ኖሮ… ስለ ምርጫው ከማውራት በፊት የፖለቲካ ስነ-ምህዳሩን ማስፋት ብሎም የምርጫ ቅድመ-ሁኔታውን ማመቻቸት ያስፈልግ ነበር፡፡

ህውሓት ግን ልክ እንደ አየለ ጫሚሶ አይነት ሰዎችን በማሰባሰብ በተቃዋሚ ፓርቲነት ካላደራጃቸው በቀር በራሳቸው ጊዜ ፓርቲ የመሰረቱት ድርጅቶች’ማ እንዲያሸንፉ ቀርቶ እንዲሳተፉም ፍላጎት የለውም፡፡

አሥር ጊዜ ‹‹ምርጫ ምርጫ›› የሚሉን ሕዝቡ በድምጹ መሪውን መምረጥ አለበት›› ብሎ ከማሰብ ሳይሆን የክልላቸውን ምርጫ መቶ ከመቶ ደፍነው በርካታ ተቃዋሚዎችን በውስጧ የያዘችው ኢትዮጵያ ግን በምርጫ ማግስት ስትታመስ ለማየት ካላቸው ጉጉት ነው፡፡

ምክንያቱም ሕዝቡ ለመረጠው ፓርቲ ቢሮውንና ሥልጣኑን የሚያስረክብ ድርጅት የአረና ፓርቲ አመራሮች መቀሌ ውስጥ የተከራዩትን ቤት እንዲለቁ አያደርግም፡፡ ‹‹ለእነ አብርሓ ደስታና አምዶም ገብረ-ሥላሴ ቤት እንዳታከራዩ›› እያለ አከራዮችን አያስፈራራም፡፡

ስለሆነም ህውሓት በምርጫ ስልጣንን ስለመልቀቅ ከማውራቱ በፊት ተቃዋሚዎችን ከተከራዩት ቤት ማስለቀቁን መተው አለበት፡፡ ዶክተር አረጋዊ እንደ ፓርቲ አመራርነቱ የዶክተር ደብረ ጽዮንን ቦታ እንዲመኝ ከማድረግ አስቀድሞ… እንደ ልቡ የሚንቀሳቀስበትና በፈለገው ጊዜ ገብቶ የሚወጣበት የሰላም አየር መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

‹‹መንገድም እውነትም እኔ ነኝ›› ከሚል ደረቅ አቋም መራቅ፣ ‹‹ምርጫ ማለት በተቃዋሚ ፓርቲዎች ተሳታፊነት ገዥው ፓርቲ የሚያሸንፍበት መድረክ ነው›› ከሚል የአላዲን አስተሳሰብ መላቀቅ ግድ ይላል፡፡ ከሒደቱና ከውጤቱ በፊት የምርጫ ቅድመ-ሁኔታውን ምቹ በማድረግ የህዝብ ድምጽ የሚከበርበት፣ ፓርቲዎች እውነተኛ ተፎካካሪዎች ሆነው የሚሳተፉበት የውድድር ሜዳ መፍጠርን ይጠይቃል፡፡

ከዚህ ውጭ ያለው የጌታቸው ረዳ የምርጫ ወሬ ግን ከአላዲን የመቶ ሜትር ሩጫ ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡

Click to comment

More in መዝናኛ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top