ደም መለገስ ከኮሮናቫይረስ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለዉም – የቤቶች ድራማ ተዋናዮች
ደም መለገስ ከኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ19) ጋር ምንም ዓነይት ግንኙነት እንደሌለውና ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ደም እንዲለግሱ አርቲስቶች ጥሪ አቀረቡ።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በተፈጠረው መደናገጥ የበጎ ፈቃድ ደም ለጋሾች ቁጥር መቀነሱ እንዳሳሰበው ብሄራዊ የደም ባንክ አገልግሎት ማስታወቁ ይታወሳል።
በተለይ በስፋት የደም ልገሳ የሚከናወንባቸው ዩኒቨርሲቲዎች፣ ትላልቅ ፋብሪካዎች እና የመንግስት ተቋማት ናቸው፡፡
እነዚህ ተቋማት ደግሞ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በተላለፈው መመሪያ ምክንያት እንቅስቃሴያቸው ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በመገደቡ የደም ለጋሾች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።
ይህንን ተከትሎ የጤና ሚኒስቴርና ብሄራዊ የደም ባንክ አገልግሎት በጎ ፈቃደኞች ደም እንዲለግሱ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።
ጥሪውን የተቀበሉት የቤቶች ድራማ ተዋናዮች ዛሬ በኢትዮጵያ የደም ባንክ አገልግሎት ተገኝተዉ ደም ለግሰዋል።
ተዋናዮቹ የአገሪቱ መሪዎች በፈቃደኝነት ደም በመለገስ ያሳዩትን አረአያነት መከተል ከህዝቡ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
የደም አሰጣጥ ሂደቱም ንጽህናውን የጠበቀና ለኮሮናቫይረስ የማያጋልጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የኮሮናቫይረስ ተጋላጭነት ሳይኖር ደም ለሚያስፈልጋቸው ደም መለገስ ተገቢነት ያለው መሆኑን አስገንዝበዋል።
ከኮሮና በሽታ መከሰት በኋላ የደም ሰጪዎች ቁጥር እንደቀነሰና ደም መስጠት ከበሽታው ጋር ምንም ዓይነት ተዛምዶ እንደሌለውም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ደም በመለገስ የሰው ሕይወት ማትረፍ የዜግነት ግዴታቸው እንደሆነና ለህሊናም እርካታ እንደሚሰጥ ተዋናዮቹ ገልፀዋል።
”የሚተካውን ደም በመለገስ የማይተካውን ህይወት” እናድን ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መሥፈርት መሠረት 100 ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርባት ኢትዮጵያ በዓመት አንድ ሚሊዮን ከረጢት ደም ያስፈልጋል፡፡
ይሁንና በአገሪቱ ደም የመለገስ ባህሉ ገና ባለመዳበሩ በዓመት የሚሰበሰበው የዚህን አንድ አራተኛ የሚሆን አይደለም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድና ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸዉ የሕዝቡን ተነሳሽነት ለማሳደግ በቅርቡ ደም መለገሳቸዉ የሚታወስ ነዉ።
ምንጭ:- ኢዜአ