ኮሮና የአምስት ዓመቷ ልጃቸውን የነጠቃቸው ወላጆች መልእክት.. .
(ታምሩ ገዳ)
በአሜሪካ ፣ሚቺጋን ግዛት ዲዬትሬት ከተማ ውስጥ የሚኖሩት ሁለቱ የጸረ ኮሮና ዘማቾች የሆኑት የእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኛው ኢቢይ ሀርበርት እና የፖሊስ ባልደረባዋ ባለቤታቸው ላቮንድሪያ ሀርበርት ባለፈው እሁድ የአምስት ዓመት ሴት ልጃቸው ስካይልር በዘመኑ የኮሮና ወረርሺኝ ሳቢያ ቢነጠቁም ለሁለም ሰዎች እጭር መልክት አላቸው ።እርሱም “የኮሮና ቫይረስ ማንኛውንም ጾታ፣ዘር እና ሀይማኖት ስለማይለይ አንዘናጋ ” የሚል ነው።
እንደ ወላጅ እናቷ ገለጻ በአስቸኳይ አዋጁ ምክንያት ለቀናት ከቤቷ ወጥታ የማታውቀው እና የቫይረሱ ምልክት በቤተሰቦቿ ላይ ያልተከሰተው ጨቅላዋ ስካይለር ገና ህመም ሲጀማምራት ጉሮሮዋን ከመከርከር ውጪ ለሁለት ቀናት እንደማንኛውም ጊዜ ትበላለች፣ትጠጣለች፣ትጫወታለች ።
” ከዚህ የተነሳ የኮሮና ወረርሺኝ የሚለው ቃል በአይምሮዬ ውስጥ አልመጣም ነበር” የሚሉት ወላጅ እናቷ ከአራት ቀናት በሁዋላ ጨቅላዋ ልጃቸው “ልቆጣጠረው የማልችለው የራስ ምታት እና ትኩሳት አስቸገረኝ ” ማለቷን ተከትሎ ለምርመራ ወደ ሆስፒታል ስትወሰድ፣የመተንፈስ ችሎታው ጤናማ እንደ ነበር፣ምንም አይነት የወረርሽኙ ምልክት ባይታይባትም በጣም ያልተለመደ ፣ነገር ግን ከኮሮና ጋር ተዛማጅነት ያለው የማጅራት ገትር/መንጃይት በሽታ ምልክት እየታየባትም የመተንፈስ እንቅስቃሴው በመልካም ሀኔታ ላይ ነበር።
በኃላ ባለፈው ሚያዚያ/አፕሪል 3/2020 እኤአ የመተንሻ መሳሪያ ቢገጠምላትም ፣ በተፈጥሮዋ ፍቅርን ሰጥታ ፍቅርን የምትቀበል፣ፍርሃት የሚባል ነገር የምታውቀው ልጃቸውን በኮሮና መነጠቃቸውን የፖሊስ አባል የሆኑት እናቷ በሀዘኔታ ያስታውሳሉ።
ከሀኪሞች የቅርብ እገዛ አግኝታ የነበረችው ሕፃን ስካይነር በሚቺጋን ግዛት ውስጥ የመጀመሪያዋ በእድሜዋ አነስተኛ የኮሮና ቫይረስ ሰለባ ስትሆን ፣ስታድግ ዳንሰኛ፣እና የህጻናት የጥርስ ሀኪም መሆን ህልም የነበራት ታዳጊዋ አሟሟቷ ወላጆቿን ብቻ ሳይሆን ህይወቷን ሊታደጉ ብርቱ ጥረት ያደረጉት የህክምና ባለሙያዎችን ጭምር ልባቸውን ሰብሯል። ሁሌም ጠዋት ከእንቅልፍ ስትነሳ እናቷን በመሳም “እወድሻለሁ” በሚል የምትናገረው የፍቅር ቃል ከአእምሯቸው እንደማይጠፋ ወላጅ እናቷ ለ ኤን ቢ ሲ ቴሌቭዥን ተናግረዋል።
ወላጅ አባቷም እንዲሁ”እንደ ኮሮና የመሰለ መጥፎ ወረርሽኝ ጋር ስንዋጋ ብዙ ነገር ተምረናል ፣እርሱም ኮሮና ስለ ቀለም፣ ስለብሔር፣ ስለ ፖለቲካ፣ስለ ጾታ፣ ስለ ሀይማኖት ፣ስለ እድሜ ግድ የለውም ።ይሄ ጨካኝ አውሬ ከፊቱ ያገኘው ሁሉ ለማጥፋት ያሴረ ነው።በልጄ ላይ የደረስው ስቃይን ፣በቤተሰቤ ላይ እንዲህ የወደቀው የልብ ስብራትን ለጠላቴም ብሆን አልመኘውም፣ነገር ግን በዚህ መጥፎ ወረርሽኝ ዙሪያ ያለን ግንዛቤን እናጠናክረው”በማለት በወረርሽኙ ዙሪያ የተዘናጉ ፣አይነካንም እና አይመለከተንም ያለ ወገኖችን አስጠንቅቀዋል።
ወረርሽኙ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአለም ላይ ሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ሽህ በላይ ስዎችን አጥቅቷል፣ አንድ መቶ ሰባ ሰባት ሽህ በላይ ገድሏል፣ ስድስት መቶ ሰማኒያ ሺህ በላይ ከቫይረሱ አገግመዋል። በምድረ አሜሪካ እንዲሁ ስምንት መቶ ሀያ አራት ሽህ በላይ አጥቅቶ ከአርባ አምስት ሺህ በላይ ህይወት መቅጠፉን መረጃዎች ይገልጻሉ።