Connect with us

ነጻነትን የሚያቀዳጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

ነጻነትን የሚያቀዳጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ | አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ
Photo: Social media

ባህልና ታሪክ

ነጻነትን የሚያቀዳጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

ነጻነትን የሚያቀዳጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ | አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ክልሎች ሕዝባቸውን መሰብሰብ፣ እንቅስቃሴያቸውን መገደብ ጀምረው ነበር፡፡ በክልሎች መሃከል ይቅርና በዞኖችና በወረዳዎች መሃከል የሚደረግን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ዘግተው እንደነበር ይታወሳል፡፡

አናም ከዚያ በኋላ በፌደራል ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊታወጅ መሆኑን ሲሰማ ‹‹ቁጥጥሩ ሊጠብቅ ነው›› የሚል ግምት የነበረ ቢሆንም የወጣው አዋጅ ግን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሳይሆን የትራንስፖርት ሚኒስቴር ያወጣው የሚመስል ነበር፡፡

ይሄን ያስባለኝ አዋጁ የትራንስፖርትና የሕዝብ እንቅስቃሴን ከመገደብ ይልቅ የተሳፋሪ ቁጥርን የሚወስን ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡

እርግጥ እንደኛ ባለ ድሃ አገር ግለሰቦች በቤታቸው፣ ክልሎች በክልላቸው እንዲወሰኑ ማድረግ ከባድ ነው፡፡ በቤቱ ውስጥ የሚልሰውና የሚቀምሰው የሌለውን ሕዝብ ‹‹ከቤትህ እንዳትቀሳቀስ›› ማለት ‹‹በቫይረስ ሳይሆን የእለት ጉርስ አጥተህ ሙት›› እንደማለት ነውና…

ግን እየሆነ ያለው ይሄ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል አዲስ አበባን ብንመለከት የእለት ጉርስ ከሚፈልገው ይልቅ አስቤዛውን ከዝኖ ሲጨርስ የቤት መኪናውን ይዞ በቢዝነስ ሥም የኮሮናን ቫይረስ የሚፈልገው ይበዛል፡፡ ከተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ውጭ አብዛኛው ሕዝብ አሁንም ድረስ በበፊቱ የኑሮ ዘይቤው ቀጥሏል፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ አገልግሎት ሰጪ የመንግሥት ተቋማት አሰራራቸውን በማሻሻል ፈንታ የሰልፈኞቻቸውን ቁጥር ሲያሳድጉ ተስተውለዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በመብራትና ውሃ የክፍያ ጣቢያዎች፣ የሚታየው ሰልፍና ትርምስ እንደውም ከወትሮው የባሰ ሁኗል፡፡ (በሆስፒታሎችም ጭምር)

እርግጥ ከክፍያ ጋር ያለውን ችግር ለማቃለል የመብራትና ውሃ ክፍያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል እንዲሆን መወሰኑን ሰምተናል፡፡ ያም ሆኖ ግን መሥሪያ ቤቱ ‹‹ሰልፈኞቹን ለሌላ አሰላፊ አስተላልፏል›› እንጂ ‹‹ችግሩን ቀረፏል›› ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ልንተማመንበት ሲገባ የምንጉላላበት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጨማሪ አገልግሎቶችን ሊሰጥ ቀርቶ የእራሱንም ተግባራት በአግባቡ እየተወጣ አይደለም፡፡

ይሄን ብዬ ወደ ዋናው ሐሳቤ ስመጣ የኮሮና ቫይረስ በተገመተው ልክ ጥቃት ማድረስ ባይችልም የተጠቂዎች ቁጥር ግን ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ነው፡፡ ያውም ወደ ውጭ አገር ያልሄዱና በሽታውን ከማን እንደወሰዱ የማይታወቁ የኮሮና ተጠቂዎችን እያገኘን ነው፡፡ ይሄም ሁኔታ በሽታውን በቀላሉ ለመቆጣጠር የማያስችልና ለወረርሽኝ ተጋላጭ የሚያደርግ ቢሆንም… አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ግን የወጣበትም ሆነ እየተፈጸመበት ያለው መንገድ ከዚህ እውነታ ጋር የሚጣጣም ሳይሆን የሚቃረን ነው፡፡ የወጣው አዋጅ ክልሎችም ሆነ ዜጎች በራሳቸው ጊዜ የገደቡትን እንቅስቃሴ የበለጠ የሚያፍን ሳይሆን ዝውውርን የሚያሰፍን ሆኖ ነው ያገኘነው፡፡

ከዚህ ባለፈም ባሉበት ቦታ በዓሉን ለማክበር ያሰቡ ዜጎችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲያከብሩ የፈቀደ፣ አዲስ አበባ የነበሩ የቀን ሰራተኞችና የጎዳና ተዳዳሪዎች በባስ ተጠቅጥቀው ወደ ክልላቸው ወስዶ የዘረገፈ፣ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት የነበረውን ጭምትነት አጥፍቶ ነጻነትን ያጎናጸፈ፣ በአዲስ አበባ የነበረውን ቸልተኝነት ከትግራይ ውጭ ላሉት ክልሎች ያስተላለፈ ነው፡፡ አዋጁ እንቅስቃሴን መገደብ ሲገባው የተሳፋሪዎች ቁጥርን እና የትራንስፖርት ታሪፍን ብቻ ነው ማሻሻል የቻለው፡፡

ምንም እንኳን የኮሮና ምርመራ ያላደረገ አንድ ግለሰብ ለበዓል ወደ ቤተሰቦቹ ጋር በአውቶብስ ሄዶ ከሚያገኘው ጥቅም ይልቅ የሚያስተላልፈው ሕመም ከባድ ቢሆንም፣ የቀን ሠራተኞችንና የጎዳና ተዳዳሪዎችን ወደ ክልላቸው ስንመልስ ቫይረሱንም አብረን የምናደርስ ቢሆንም፣ ከመሰተራችን በላይ መንቀሳቀሳችን እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ አገር የሚያመጣው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑ ቢታወቅም፣ ከጤናው ይልቅ ሥራውን ያስቀደመ ዜጋ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በዚህ በሽታ ሥራውንም ጤናውንም አጥቶ አልጋ ላይ መዋሉ አይቀሬ ቢሆንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጠበቅ ማለት ሲገባው ለቀቅ አድርጎናል፡፡

በሌላ መልኩ ግን ሕዝቡ በየጎዳናው እና በየገባያው ላይ ተሰጥቶ ቢውልም የመንግስታችንም ሆነ የሚዲያዎቻችን ትኩረት ቤተ-እምነቶች ላይ መሆኑ ግርታን ይፈጥራል፡፡ ቤተ-እምነቶች ከሁሉም አስቀድመው አማኞቻቸውን በመበተን ቅጽሮቻቸውን የዘጉ ቢሆንም ቁጥጥሩ ግን ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› ወይንም ደግሞ ‹‹ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ›› ነው፡፡

ያም ሆኖ ታዲያ የኔ ቅሬታ በሌሎች ስፍራዎች ላይ ያለው ቁጥጥር መላላቱን እንጂ ቤተ-እምነቶች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር መጥበቁን የሚቃረን አይደለም፡፡ ሐሳቤ ከቤተ-እምነቶች ጎን በጎን በንግድ ድርጅቶችና በገባያ ስፍራዎች፣ በአገልግሎት ሰጪ ተቋሟትና በጎዳናዎች ላይ ያለው እንቅስቃሴ መጥበቅ ይገባዋል የሚል ነው፡፡

እምነትን በተመለከተ ደግሞ ባሁኑ ሰዓት ‹‹ኢትዮጵያን የሚጠብቃት አምላክ አላት›› የሚለው እምነት እየተንጸባረቀ ያለው በመንግስት በኩል ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም የምርምራውንም ሆነ የቁጥጥሩ መዳከም በመድሃኒቱ ወይንም ደግሞ በእምነቱ ከተማመነ መንግሥት የሚጠበቅ ነውና….

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top