Connect with us

የምዕራባውያን አሻራ ዓይናቸውን ያንሸዋረራቸው ሚዲያዎች ወደ መንፈሳዊ እሴቶች

የምዕራባውያን አሻራ ዓይናቸውን ያንሸዋረራቸው ሚዲያዎች ወደ መንፈሳዊ እሴቶች
Photo Facebook

ባህልና ታሪክ

የምዕራባውያን አሻራ ዓይናቸውን ያንሸዋረራቸው ሚዲያዎች ወደ መንፈሳዊ እሴቶች

የምዕራባውያን አሻራ ዓይናቸውን ያንሸዋረራቸው ሚዲያዎች ወደ መንፈሳዊ እሴቶች ፊታቸውን ሲያዞሩ ሞገሳቸው ጨምሯል፡፡  | ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

የኢትዮጵያ ሚዲያ መንፈሳዊነትን ሲሸሽ ህዝባዊ እሴትን ሲርቅ የኖረው ዓይኑ ተንሸዋሮ ነው፡፡ ከምዕራባዊው የሚዲያ ጥበብ ጥራትና ተአማኒነትን ሳይሆን እምነትና ባህል ጠልነትን ወርሷል፡፡ መሰልጠን መጮህ የሚመስላቸው አዳዲስ ሚዲያዎችም በዚሁ በምዕራባውያኑ የስካር ዓለም ጉዞ አብረው መጓዝን የመረጡ ናቸው፡፡

በህዝባቸው ኑሮ ላይ ድርሻቸውን ማጤን አይፈልጉም፤ ከዚያ ይልቅ በእንግሊዝ ጠባብ ሜዳ ወሬ የሰፊዋን ዓለም ጣጣ የደረሱበት መስሏቸው ሲዳክሩ ኖረዋል፡፡ ትውልዳቸው እጅ ባለ መታጠብ ሞት ሲመጣበት እጅህን ታጠብ ያሉት እንደ ጲላጦስ የሃጢአት እጃቸውን ሳይታጠቡ ነው፡፡

አሁን ብዙዎቹ ሚዲያዎቻችን ወደ እኛ ተመስለዋል፡፡ የምንፈልገውን ያሳዩናል፤ የሚገባን የሚነገርበት ሚዲያ ኾነዋል፡፡ አስቀድሞም ሚዲያነት እንደ ምዕራባውያኑ ኦስካርና ፕሪሚየር ሊግ መስሏቸው በምዕራቡ ዓለም ባህል ሰክረው ነበር፡፡ ይኼ ስካር ግን ክፉ ቀን ሲመጣ ተጋለጠ፡፡

አሁን ቴሌቨዥንን መክፈት መልካም ነው፡፡ ዑላማ እናደምጥበታለን፤ ጳጳስ እንሰማበታለን፤ ፓስተር እናይበታለን፤ እንዲህ ያሉ ፍሬ ያላቸው ጉዳዮች በራቁበት መስኮት ደጋግ ምክሮችን እንሰማበታለን፡፡ ባይኖረንስ ባልነው ሀብት እንኳን ኖረን ያልንበት እድል ተፈጥሯል፡፡

የቴሌቨዥኖችና የሬዲዮኖቻችን ሞገስ ጨምሯል፡፡ ምክንያቱ እሴቶቻችንን ስላሳዩን ነው፤ ለእኛ ስለቀረቡ ነው፡፡ የሚታመን ሀሳብ ይዘው ስለመጡ ነው፡፡ ደግ መሆንና መልካም መስራት ዜና ስለሆነባቸው ነው፡፡ ከአድርባይነትና ከቆርጦ መቀጠል አረፍ ስላሉ ነው፡፡

እርግጥ ነው በሌላው ግዜ ቴሌቨዥኖችና ሬዲዮኖች እንዲህ የእምነት ቤት የስብከት መገናኛዎች ይሁኑ አልልም፤ ግን ሴኩላሪዝም ከህዝብ መራቅ አይደለም፡፡ ሴኩላሪዝም የሌላው ዓለምን ትራፊ ጉዳይ አምጥቶ ማቡካት አይደለም፡፡ ዛሬ ሚዲያዎቻችን እንደ ቻይና እንግሊዝና አሜሪካ ክትባት ፈጠርን የሚሉ ባለሙያዎችን መስማት ናፍቀዋል፤ እንዲህ ያለ ብርቱ እንዲፈጠር ምን ሰርተው ነበር፡፡ የበቀቀን ህይወትን ከመኖር ተላቀው የባህል እውቀቶች እንዲበለጽጉ ድርሻቸው የቱ ድረስ ነበር? ዛሬ ግን የባህል ሀኪሙን ውጤት ናፍቀውታል፡፡ ምዕራባውያኑ የናፈቁትን ያገኙት ማግኘት የሚፈልጉት ጋር ለመድረስ ለፍተው ነው፡፡ እኛ አፍሪቃ ዋንጫን መብላት ፈልገን በሚዲያዎቻችን የምንደክመው ግን ማንትስ የተባለው ክለብ የእንግሊዝን ዋንጫ እንዲበላ ነው፡፡

ይሄንን ጨለማ እናልፈዋለን፤ ዳግም ጨለማ ትውልድ ሲገጥም ድል ያደርግ ዘንድ ሚዲያዎቻችን በብርሃን ሊኖሩ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሚዲያ ብርሃኑ ኢትዮጵያውያንን መምሰል፣ ለኢትዮጵያ መኖር፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ማየት ነው፡፡ አሁን የተመለሰው የሚዲያዎቻችን ሞገስ ባለበት ይቀጥል ዘንድ ነገም እንዲህ ወደ ኢትዮጵያውያን የተጠጋን ሀሳብ እውቀት ጉዳይና ነገር እሴትና ባህል ጉዳይ አድርጎ መስራቱ አጠያያቂ አይደለም፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top