የሳንባ ቆልፍ(ኮሮና ቫይረስ) ወጥቶልን ይሆን? | (ቅዱስ መሀሉ)
በችካጎ ሮዝላንድ የማህበረሰብ ሆስፒታል በቀን ከሚመረመሩ ከ400 እስከ 600 በሚደርሱ ሰዎች ላይ በአማካይ ግማሽ ያህሉ ሰዉነታቸው ኮሮና ቫይረስን መዋጋት የሚችል ተፈጥሯዊ መከላከያ(አንቲቦዲ) አበጅቶ ተገኝቷል። ይህ የሚያሳየው ሰዎች በቤት ውስጥ እንዲገቡ እና እጅ ታጠቡ የሚለው ውሳኔ ከማለፉ በፊት የሳንባ ቆልፍ(ኮሮና ቫይረስ) በማህበረሰቡ ውስጥ ይበልጥ መሰራጨቱን እና አንዳንዶቹ የህመሙን ምልክቶች ልብ ሳይሏቸው በራሳቸው ማገገማቸው እና ድጋሚም እንዳያዙ የተፈጥሮ መከላከያ ሰውነታቸው ገንብቶ መገኘቱን ከየዕለቱ ምርመራ መረዳት ይቻላል።
ባለሙያዋ ከምንመረምራቸው 600 ያህል ሰዎች ውስጥ በአማካይ በቀን ከ10 እስከ 20በመቶ ብቻ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል ብለዋል። ቫይረሱ ኖሮባቸው በራሳቸው የተፈጥሮ የሰውነት መከላከያ የዳኑት ሰዎች ካለባቸው ሰዎች የበለጠ ይበዛሉ። ይህ ማለት ብዙ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ሳያውቁት ስላገገሙ ቫይረሱ ለነዚያ ሰዎች ወጥቶላቸዋል (ኢሚዩን ናቸው)። እነዚህ ሰዎች በተወሰነ ማህበራዊ ርቀታቸውን ጠብቀው ወደ ቀደመ ስራቸው እና ኑሯቸው በተለመደው መልኩ ሊመለሱ ይችላሉ። ምክንያቱም ለማንም ስጋት አይደሉምና!
በጀርመን ቦን ውስጥ በምትገኝ የሄንስበርግ ወረዳ በተካሄደ ጥናት 15 በመቶ ነዋሪው ኮሮና ቫይረስ እንደያዛቸው ምንም ምልክት ሳያሳዩ እና ሳያውቁ የሳንባ ቆልፍ(ኮሮና ቫይረስ) እንደነበረባቸው የታወቀ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ በኮሮና ቫይረስ ለሞት የተዳረጉት 0.37በመቶ ብቻ ናቸው። የተቀሩት በበሽታው መያዛቸውን ሳያውቁ ተቋቁመው አልፈውታል።
እና ምን ለማለት ነው ኢትዮጵያ ውስጥም አብዛኛው ሰው ምናልባት የሳንባ ቆልፍ (ኮሮና ቫይረስ) ይዞት ሳያውቀው የወጣለት ሊሆን ይችላል? ማን ያውቃል!?
ለምሳሌ በአሜሪካ ከኒውዮርክ በላይ ብዙ ሰዎች ሊሞቱበት ይችላል ተብሎ ተሰግቶ የነበረው በካሊፎርኒያ ግዛት ነበር። ይሁን እንጅ አንዳንድ ጥናቶች ያ ያልሆነበት ምክንያት ምናልባት ኮሮና ቫይረስ በይፋ በአሜሪካ ከተነገረበት ግዜ ቀደም ብሎ በግዛቱ ተከስቶ የነበረው ለየት ያለ ሃይለኛ ጉንፋን/ኢንፍሉዌንዛ ምናልባትም ራሱ ኮሮና ቫይረስ ሊሆን እንደሚችልና እና ነዋሪዎቹ መከላከያ አንቲቦዲ ስላዳበሩ ይሆናል የሚል መላ ምት አለ። በወቅቱ የሞቱ ሰዎች ቢኖሩም ለሞታቸው ምክንያት ሆኖ የተመዘገበው ግን ያኔ ያልታወቀው ኮሮና ቫይረስ ሳይሆን ከጥቅምት ወር ወዲህ በኢንፍሉዌንዛ ከሞቱት ከ50ሽ በላይ አሜሪካዊያን ውስጥ ነው።
የአሜሪካ ብሄራዊ የአለርጅ እና ተዛማች በሽታዎች ተቋም በአሜሪካ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ይሞታሉ ብሎ ቀድሞ ካስቀመጠው ቁጥር ላይ 40 በመቶውን ቀንሷል። ይህ ምናልባት በብዙዎቹ ግዛቶች በሚመረመሩ ሰዎች ላይ አብዛኛው ህዝብ በሽታውን ለመከላከል የሚያስችለው አንቲቦዲ ሳያውቀው ገንብቶ የመገኘቱ ነጸብራቅ ሊሆን ይችላል።
ሁላችንም ልንረዳ የሚገባው ነገር አሁንም ቢሆን ከ80በመቶ በላይ አብዛኛው በሳንባ ቆልፍ(ኮሮና ቫይረስ) የሚያዙ ሰዎች የሚድኑት ያለምንም ተጨማሪ ህክምና በቤታቸው ውስጥ ነው። ሁላችንም ልብ ልንለው የሚገባው ቫይረሱ የሚበረታው አረጋዊያን እና በማንኛውም እድሜ ላይ የሚገኙ የተለያየ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ላይ ነው!!
ጉንፋን እንኳ ደጋግሞ የሚያጠቃቸው እና ለተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭ የሆኑት ህጻናትን እንኳ የአዋቂዎቹን ያህል አለመታመማቸው ብቻ ሳይሆን አንዳንዶቹ መያዛቸውን ሳያውቁ ቶሎ መዳናቸው፣ ህመሙ በነሱ ላይ አለመጽናቱ እና አለማሰቃየቱ ለስነ ቫይረስ ሳይንቲስቶች እንቆቅልሽ እና አግራሞት ብቻ ሳይሆን በአንድ ሳይንቲስት አገላለጽ “በዚህ የወረርሽኝ ወጀብ የሚያስደስተው ብቸኛ ነገር ቢኖር ቫይረሱ በህጻናቱ ላይ አለመጨከኑ ብቻ ነው።”
እስካሁን ከመላው ዓለም በተመዘገበው መረጃ ህጻናት በበሽታው ብዙ አልተጎዱም ማለት አልተያዙም ማለት አይደለም። ጥቂት ህጻናት ተይዘዋል። ከነሱ ውስጥም የሞቱት 10 አይሆኑም። የሳንባ ቆልፍ ህጻናትን የእኛን ያህል ባይጎዳቸውም ህጻናቱ በሽታውን የበለጠ ሊጎዱ ወደ ሚችሉ ሰዎች የማስተላለፍ እድላቸው ሰፊ ነው። ስለዚህ ለራሳችን እየተጠነቀቅን የምንወዳቸው እናትና አባቶቻችንን እንዲሁም ህጻናትን ጨምሮ በየትኛውም እድሜ ላይ የሚገኙ ሌላ ህመም ያለባቸውን ሰዎች(የስኳር፣ የልብ፣ ደም ግፊት፣ ካንሰር፣ ቲቢ፣ አስም፣ ኤችአይቪ ወዘተ) እንጠብቃቸው።
የቺካጎው ዜናው ሙሉ ዘገባ ይሄው፡