Connect with us

ኸረ ኡ ኡ!… ማለቃችን ነው?!

ኸረ ኡ ኡ!... ማለቃችን ነው?!
Photo Facebook

ነፃ ሃሳብ

ኸረ ኡ ኡ!… ማለቃችን ነው?!

ኸረ ኡ ኡ!… ማለቃችን ነው?!
(ጫሊ በላይነህ)

“ያላወቁ አለቁ ነበረ ተረቱ
እያወቁ ማለቅ መጣ በሰዓቱ”

ሲል ባለቅኔው የተቀኘው ይኸ ክፉ ጊዜ ታይቶት ሳይሆን አይቀርም። አዎ!..ይኸ ሟርት አይደለም። ክፉ መመኘትም አይደለም። የኮሮና ወረርሽኝ ፈጣን ስርጭት ለመግታት ብቸኛው መንገድ እውነታውን ተረድቶ መጋፈጥ ብቻ ነው። አዎ!.. ቸልተኝነት በዝቷል። ቸልተኝነት መብዛቱንም መንግሥታችን በሚገባ ተረድቷል። በጤና ባለሙያዎች… እየተነገረን ያለውን የጥንቃቄ መንገዶች ጨርሶ እየተከተልን አለመሆኑ ኡኡ የሚያስብል ነው።

ብዙዎች ስለቁጥር ይጨነቃሉ። አንዳንዶች ደፈር ብለውም 16 ሰዎች ብቻ በኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮና ቫይረስ መያዝ ትንሽ መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህም ተነስተው መንግሥት እና የጤና ጥበቃ ሰዎች ነገሩን እያጋነኑት መሆኑን የሚናገሩ አላዋቂዎች በዝተዋል። እነዚህ ወገኖች ግን የዘነጉት እነጣልያን በቀን እስከ 800 ሰዎችን መቅበር ደረጃ የደረሱት ቁጥሩ አንድ እና ሁለት እያለ የቫይረሱ ስርጭቱ ከቁጥጥር ውጭ የመውጣቱን ጉዳይ ነው።

 

አንዳንዶች ሶሻል ዲስታንስ፣ ሌሎች ፊዚካል ዲስታንስ የሚሉትን ቢያንስ በሁለት እርምጃ መራራቅ…በኢትዮጵያ በተለይም የአፍሪካ መዲና በምትባለው የአዲስአበባ ከተማ ለመተግበር ሰሚ መጥፋቱ ያስደነግጣል። መንግሥት ት/ቤቶችን ዘግቷል። አብዛኛው ሠራተኞች ከቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ አዟል።…ይኸም ሆኖ ለታክሲ ተሰልፎ ታጭቆ መጓዝ አሁንም አልቀረም። መጠጥ ቤቶች፣ ምግብ ቤቶች፣ ሱፐርማርኬቶች፣ ሆስፒታሎች፣ ክሊኒኮች፣ መድሀኒት ቤቶች፣ የገበያ ማእከላት፣ የየሰፈሩ ጉሊቶች…አሁንም በሰዎች እንደሞሉ ናቸው። በየመንገዱ ተዛዝሎ መሄዱ፣ መተቃቀፉ፣ መሳሳሙ… በአይን የሚታይ ነው።

እናም መንግሥት መመሪያዎችን ማውጣቱ፣ ጠዋት ማታ ስለእጅ መታጠብ በመናገር ወይንም በማስተማር ብቻ ስርነቀል ለውጥ ማምጣት እንደማይችል ግልፅ ሆኗል። እናም በህገመንግስቱ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት ቢያንስ የሚያሰባስቡ መብቶችን በአስገዳጅ ሁኔታ መገደብ መቻል አለበት።

ከአንድ ቢልየን የላቀ የህዝብ ብዛት ባላት ሕንድ ህዝቡ ከቤት እንዳይወጣ የተደነገገ ሲሆን ይኸን ተላልፈው የተገኙ ዜጎች የፖሊስ ልምጭ ከመቅመስ ጀምሮ በቁጥጥር ስር እስከመዋል የሚደርስ እርምጃ መተግበር መጀመሩ እዚህ ላይ ጥሩ ተሞክሮ ይመስለኛል።

በእኛም አገር በሀይማኖት፣ በፓለቲካ ሰበቦች መሰባሰብ እንዲቆም ከንግግር ያለፈ እርምጃ ያስፈልጋል። ማህበራዊ ጉዳዮቻችን እንደሐዘን፣ ሰርግ፣ ተዝካር…ባሉ ጉዳዮች መሰባሰብ በይፋ መታገድ አለባቸው። ህዝቡ ቢያንስ ለ15 ቀናት ከቤት እንዳይወጣ በማገድ የቫይረሱን ስርጭት ባለበት ማቆም ካልተቻለ በደካማ የጤና ሥርዓታችን ከእነጣልያን የባሰ እጅግ አሳዛኝ ቀውስ ውስጥ በጣም በቅርቡ መግባታችን የማይቀርልን ሐቅ ነው።

በነገራችን ላይ መንግሥት ሰዎችን ከቤት አትውጡ ሲል እንደፈረንጆቹ በቀላሉ ይተገበራል ማለት አይደለም። ምክንያቱም የእለት ጉርስ የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በብዛት አሉንና ነው። የጎዳና ተዳዳሪዎችን ጨምሮ እነዚህ ወገኖችን ማቆያ ማእከላት በጊዜያዊነት ፈጥነን ማቋቋም ይገባናል። ህዝቡ በተለያዩ አደረጃጀቶች ድጋፉን በመስጠት ዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍል ባለበት ተረጋግቶ እንዲቆይ ድጋፉን መቀጠል አለበት።

መንግሥቴ ሆይ ፍጠን!..አልሰማ ያለውን ህዝብህን ከማስተማር ጎን ለጎን መብቱን በአስገዳጅ ሁኔታ መገደብ እየመጣብን ካለው ከባድ መቅሰፈት ለመዳን ብቸኛው መንገድ ነው!!

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top