እንግሊዝና የኮሮና ቫይረስ ፍልሚያ
(አለማየሁ ገበየሁ ~ እንግሊዝ)
እንግሊዝ ከአውሮፓ ብትገነጠልም አውሮፓ ከእንግሊዝ አልተገነጠለም የሚያሰኝ ተግባር ዛሬ ጠዋት ተፈፅሟል፡፡ ምን ሆነ መሰላችሁ? በአውሮፓ በሚገኙ 180 የሬዲዮ ጣቢያዎች << YOU WILL NEVER WALK ALONE >> የተሰኘውን የሊቨርፑል እግር ኳስ ክለብ መለያ መዝሙር አስተላልፈዋል ፡፡ በርግጥም አለም አንድነትን የናፈቀችበት ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን በወቅታዊው የአለም ስጋት ላይ ጠንካራ ርምጃ አልወሰዱም እየተባሉ ሲወቀሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬ ታላቋ ብሪታንያ ኮሮና ቫይረስን ለመመከት ወደ ሃይለኛው ጦርነት ገብታለች፡፡
ከሰሜን አየርላንድ በስተቀር ሁሉም ት/ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ በጡረታ የተገለሉ 65 ሺህ የሚደርሱ ዶክተሮችና ነርሶች ወደ ጤና ተቋማቱ / NHS / እንዲቀላቀሉ ለእያንዳንዳቸው አስቸኳይ ደብዳቤ ተፅፎላቸዋል፡፡ የመጨረሻ አመት የህክምና ተማሪዋችም የፍልሚያው አካል እንዲሆኑ ተጠይቋል፡፡ ጦር ሰራዊቱ በሚቀጥለው ወር ላይ ለሚሰጠው ከፍተኛ ግዳጅ እንዲዘጋጅ ተነግሮታል፡፡
እንግሊዝ ከቀጣዩ ሳምንት በኋላ እንደሌሎቹ የአውሮፓ ሀገራት ፀጥ ረጭ ማለቷ ይጠበቃል፡፡ ይሁን እንጂ በፀጥታው መሃል ሃያ አራት ሰአታት ወዲህና ወዲያ የሚካለቡ ሰራተኞችና የስራ ክፍሎች መኖር ግዴታቸው መሆኑንን መንግስት አሳስቧል፡፡
እነዚህ ሰራተኞችም ቁልፍ ሙያተኞች የሚል ስያሜ አግኝተዋል፡፡ ቁልፍ ሰራተኞቹ ዶክተርና ነርሶች ፣ የተወሰኑ መምህራንና ማህበራዊ ሰራተኞች፣ የፍትህ ተቋማት፣ የሃይማኖት አካላትና ጋዜጠኞች … የምግብ ዝግጅት ሽያጭና ክፍፍል የሚያደርጉ ሰራተኞች … የህዝቡን ፀጥታና ደህንነት የሚጠብቁ ፖሊሶች ፣ የጦር ሰራዊት አባላት ፣ እሳት አደጋና የማረሚያ ቤት ሰራተኞች … ውሃ፣ መንገድና ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የሚሰሩ አባላት … የገንዘብ ተቋማት፣ ፖስተኞችና የፅዳት ሰራተኞች ይገኙበታል፡፡
ከላይ በተጠቀሱት ቁልፍ ስራ ውስጥ የሚሳተፉ አባወራና አማዎራዋች ልጆቻችንን የት እናደርጋቸው የሚል ስጋት ውስጥ እንዳይወድቁ በማሰብ ይህን ስራ የሚሰሩ መምህራን ተመድበውላቸዋል፡፡
አብዛኛው ህዝብ በበሽታው ምክንያት ላልታወቀ ግዜ ቤቱን በላዩ ላይ ይዘጋል፡፡ የQuarantine ህግ ተፈፃሚ ይሆናል ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ራስን ከአደገኛ በሽታ ወይም ወረርሽኝ ነጥሎ ማቆየት በመሆኑ በተለይ ኢትዮጵያዊያን ማህበራዊ ግንኙነታቸውን / ቤተክርስትያን መታደም ፣ የልጆች ልደትን ሰብሰብ ብሎ ማክበር ፣ አንድ ላይ ተሰባስቦ ቡናም ሆነ ቢራን መጠጣት ፣ የተለያዩ ድግሶችን ማዘጋጀት ወዘተ / ለግዜውም ቢሆን መግታት ይጠበቅባቸዋል _ ያለምንም ይሉኝታ ፡፡
ቤት መዘጋቱ እስከመቼ ይቀጥላል? ምናልባት ለሁለት ወራት ወይም ለሁለት አመታት? ማንም አያውቀውም ፡፡ ደግነቱ የእንግሊዝ ህዝብ ለግዜውም ቢሆን የቻለውን ያህል ተሻምቶ የሚላስ የሚቀመሰውን ሰብስቧል ፡፡ ጥሪቱ ግን ማለቁ አይቀርም ፡፡ በሽታው ካልተወገደ በስተቀር ወጥቶ መስራት አይቻልም ፡፡ ለነገሩ በጥቂት ወራት ውስጥ አያሌ የስራ ተቋማት ስለሚክስሩ መዘጋታቸው ግድ ይሆናል ፡፡ ዞሮ ዞሮ ካልሰራ ገንዘብ አያገኝም ፡፡ እህል መግዣ፣ ቤት ኪራይ መክፈያ ፣ ውሃ መብራትና ጋዝ መሙያ አያገኝም ፡፡ የስልክ ፣ የመኪናም ሆነ የካውንስል ታክስ እዳን ምን እንደሚያደርጋቸው ገና አላወቀም ፡፡ በአዳዲስ ርምጃዎቹ ውስጥ የተወጠረው የቦሪስ ጆንሰን መንግስት የበርካታ ሚሊኒዮችን ህይወት ለመታደግ የሚረዳ እቅድ እያዘጋጀሁ ነው የሚል ፍንጭ በመስጠቱ የወቅቱ ተመላኪ < አምላክ > እየሆነ ነው ፡፡
ሁሉም ነገር ጥያቄ በሆነበት በዚህ ወቅት የምላሽ ርቀት አይታወቅም ፡፡ መወሰድ የጀመሩት የመንግስት ጠንካራ ርምጃዋች የህዝቡን ፍርሃትና ስጋት ያለዝበው እንደሆነ ለማውቅም ግዜ ያስፈልጋል ፡፡ ይኸው የአምላክነትን ሚና በመጫወት ላይ የሚገኘው መንግስት ግን የኮሮና ቫይረስን ማእበል በ12 ሳምንታት ውስጥ አቆማለሁ ብሎ ፎክሯል ፡፡ ይሳካለት ይሆን ? የኢትዮጵያ አምላክ ይርዳው ፡፡