Connect with us

የአዲስአበባ ሆቴሎች ኮሮና አከሰረን አሉ

የአዲስአበባ ሆቴሎች ኮሮና አከሰረን አሉ
Photo: Facebook

ኢኮኖሚ

የአዲስአበባ ሆቴሎች ኮሮና አከሰረን አሉ

በአዲስ አበባ ያሉ ሆቴሎች በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በተሰረዙት ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስብሰባዎች ምክንያት ለኪሳራ መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

የወጪ ጫናቸውን ለመቀነስም ሠራተኞች የዓመት ዕረፍት እንዲወጡ እያደረጉመሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢዜአ ባደረገው ቅኝት ለስብሰባና ለጉብኝት በሚመጡ እንግዶች የሚጨናነቁት ሆቴሎች አሁን ጥቂት ተገልጋዮችን እያስተናገዱ ነው።

በዓለም የጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ተብሎ የተሰየመው ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) በኢኮኖሚው ላይ እያሳደረ ያለው ጫና ከባድ መሆኑ እየተገለጸ ነው።

በተለይ የወጪ ንግድና የኮንፈረንስ ቱሪዝም መቀዛቀዝ የሸቀጦች ዋጋ ላይ እጥረትና ንረት በመፍጠር ጫናውን አክብዶታል።

የቫይረሱ ስርጭት እየተስፋፋ የንግድ፣ የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እየተዳከመ መምጣቱና የበረራዎች መቋረጥም ዓለም አቀፍ ግንኙነትን እየገታ መሄዱን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መግባቱን ተከትሎ መንግስት የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ትላልቅ ስብሰባዎች ለሁለት ሳምንት እንዲዘጉ መወሰኑ ይታወቃል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የሆቴል ኃላፊዎች ስብሰባዎች መቅረታቸውን ተከትሎ ለኪሳራ መዳረጋቸውን ይናገራሉ።

የጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል የሰው ሃብት ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ጥበቡ በዚህ ወቅት በርካታ አለም ትላልቅ ስብሰባዎች የሚካሄዱበት ወቅት መሆኑን ጠቅሰው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት እነዚህ ስብሰባዎች አለመካሄዳቸው ሥራ በቆመበት ቋሚ የሆነ ክፍያዎችን ለመክፈል ስለሚገደዱ የኢኮኖሚ ጫና እንደሚያስከትል ነው የገለጹት።

የኢሊሊ ሆቴል ምክትል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ድሪባ ዋቅጅራ በበኩላቸው በአዲስ አበባ ውስጥ ያሉት ሆቴሎች ቢዝነስ ከቱሪዝም ይልቅ ከኮንፍራንስ ጋር የሚያያዝ በመሆኑ በበሽታው ምክንያት ብዙ ስብሰባዎች ላልታወቀ ግዜ በመራዘባቸው ከሆቴሉ የሚያገኙትን ገቢ በ80 በመቶ እንደሚቀንሰው ተናግረዋል።

የሃርመኒ ሆቴል ስራ አስኪያጅ አቶ ዜናዊ መስፍን ቡክ የተደረጉ ከ300 እስከ 500 የሚሆኑ አለም ዓቀፍ ስብሰባዎች እንደነበሩ ጠቅሰው ስብሰባዎቹ በመሰረዛቸው ገቢያቸው ላይ ጫና እንዳሰደረ ነው የተናገሩት።

ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ረገድ የሚታወቀው የሆቴል አገልግሎት ዘርፍ ተጨማሪ የስራ ዕድል መፍጠር መቆሙን የገለጹት የሆቴል ሃላፊዎቹ፤ አሁን የተፈጠረው መቀዛቀዝ የተቀጠሩ የሆቴል ሰራተኞች የተጠራቀመ እረፍታቸውን እንዲወስዱ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን በተከሰተው ወቅታዊ ችግር ምክንያት ሰራተኞችን የመቀነስ ሀሳብ እንደሌላቸውም አመልክተዋል።

የኢሊሊ ሆቴል ምክትል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ድሪባ ዋቅጅራ “ያለንን ወጪ ለመቀነስ በተለይ የተጠራቀመ የዓመት ዕረፍት ያላቸው ሰራተኞቻችንን ይህን ጊዜ እስኪያልፍ ቤታቸው ሆነው የሚፈልጉትን ስራ እየሰሩ ይሄን ዕረፍትም እንዲጠቀሙ እያደረግን ነው። ከዚያም ውጪ ደግሞ በደንበኛ ምክንያት መስራት ያልቻልናቸውን ስራዎች አሁን ላይ የጥገናም ይሁን ሌሎች ስራዎች እየሰራን እያሳለፍን እንገኛለን ’’ብለዋል።

የሃርመኒ ሆቴል ስራ አስኪያጅ አቶ ዜናዊ መስፍን እንዳሉት ደግሞ “የተከማቸ ዕረፍት ያላቸውን መውሰድ ከፈለጉ እሱንም በግዴታ አይደለም ፍቃደኝነት ጠይቀን ሰራተኞቻችንን ጠይቀን ነው እንጂ፤ እንዲሁ አሁን ቢዝነስ የለምና ውጣ የሚለው አስተሳሰብ የለንም።’’

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ደንበኞች ወደ ሆቴል ከመግባታቸው በፊትና ከገቡም በኋላ የንጽህና መጠበቂያ መሳሪያዎችንና የሙቀት መለኪያ መሣሪያ በመጠቀም ጥንቃቄ እያደረጉ መሆኑን ኢዜአ ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሶስት ተጨማሪ ሰዎች በመገኘታቸው በበሽታው የተያዙትን ቁጥር ዘጠኝ እንዳደረሰው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው በተጨማሪ ከተገኙት ሶስት ሰዎች መካከል ከውጭ አገር የተመለሱ አንዲት የ85 ዓመት ኢትዮጵያዊ ይገኙበታል።(ኢዜአ)

Click to comment

More in ኢኮኖሚ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top