Connect with us

ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው ግድቡን ማጠናቀቅ ሲቻል መሆኑ ተጠቆመ

ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው ግድቡን ማጠናቀቅ ሲቻል መሆኑ ተጠቆመ
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው ግድቡን ማጠናቀቅ ሲቻል መሆኑ ተጠቆመ

የኢትዮጵያ በአባይ ውሃ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቷ የሚረጋገጠው ከማንም ምንም ሳትጠብቅ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተባበረ ክንድ ስታጠናቅቅ ነው ሲሉ ኢንጅነር ተፈራ በየነ ተናገሩ።

በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ውሃዎች ዙሪያ በአማካሪነት የሚሰሩት ኢንጂነር ተፈራ በየነ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ከዓባይ ወንዝ 86 በመቶ በላይ የሚሆነውን ውሃ ከጉያዋ የምታመነጨው ኢትዮጵያ ብትሆንም፤ ምንም ያህል የውሃ ድርሻ የማያበረክቱ የተፋሰሱ የታችኛው አገሮች ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዳትሆን ሲሰሩ ኖረዋል።

ስለዚህ በአባይ ውሃ ላይ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቷ የሚረጋገጠው ከማንም ምንም ሳትጠብቅ ታላቁ ህዳሴ ግድብን እንደ ጀመረችው በተባበረ ክንድ ስታጠናቅቅ ነው።

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ የዓለም አቀፉ የድንበር ዘለል ወንዞች ማዕቀፍ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው፤ አንድ ድንበር ዘለል ወንዝ የተፋሰሱ አገራት የጋራ ሀብት ስለሆነ በፍትሃዊነት ሊጠቀሙት እንደሚገባ ይደነግጋል።

በመሆኑም አገሮች በፍትሃዊነትና በምክንያታዊነት እንዲሁም በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ ከተጠቀሙት ምንም ጉዳት እንደማያመጣ የተለያዩ አገሮች ተሞክሮ ያሳያል።

ካናዳና አሜሪካ፣ ሌሴቶና ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም አሜሪካና ሜክሲኮ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም ውሃውን ለልማታቸው በማዋል በልጽገዋል።

እነዚህ አገሮች በወንዞቹ ላይ አንዱ አገር ልማት ሲያለማ ሌላኛው የልማቱ ደጋፊ በመሆን በጋራ የሚያለሙበት ሁኔታ እንዳለ ኢንጅነር ተፈራ አመልክተዋል።

በአባይ ወንዝ ተፋሰስ ላይ ያለው ፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነት ሲታይ ኢትዮጵያ ከጉያዋ በሚፈልቀው ውሃ ለዘመናት የበይ ተመልካች ሆና በድህነት ጎዳና ውስጥ እንደምትገኝ ገልጸው፤ አሁን ላይ በፍትሃዊነት ወንዙን ልንጠቀመው ይገባል የሚል ጥያቄ ስታነሳ የተፋሰሱ ግርጌ አገራት ውሃውን አትንኩት፣ አትቅመሱት፣ አታሽቱት የሚል ጫና እያሳደሩ እንደሚገኙ ኢንጅነር ተፈራ ተናግረዋል።

ኢንጅነር ተፈራ የተፋሰሱ የታችኛው አገሮች ምንም ያህል የውሃ ድርሻ ለአባይ ወንዝ ሳያበረክቱ የላይኛው የወንዙን ተፋሰስ አገሮች ፍትሃዊ ተጠቃሚ አትሆኑም የሚለው የትኛውም ዓለም ላይ የሌለ መሆኑን ገልጸው፤ ባለፉት 15ና 20 ዓመታት አገሪቷ ከአባይ ወንዝ ገባር ከሆኑ እንደ ተከዜና ጣና በለስ ወንዞች ትንሽም ቢሆን የተለያዩ ልማቶችን ማልማት የቻለችው ከማንም ምንም ሳትጠብቅ በራሷ ገንዘብና እውቀት ማልማት በመቻሏ ነው ብለዋል።

ኢንጅነር ተፈራ ከዚህ ተሞክሮ በመነሳት ኢትዮጵያ የአባይ ውሃ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቷን የምታረጋግጠው የተጀመረውን ግድብ ለፍጻሜ በማብቃት ነው ፤ ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንሁን ብለው መጠየቅ የሚገባቸው የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ሆነው እያለ የተፈጥሮ ሀብቱ ባለቤት ኢትዮጵያ ፍትሃዊ ተጠቃሚ ልሁን ብትልም ተጠቃሚ እንዳትሆን ሌት ተቀን እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ሃብቱ እጅ ላይ እያለ ፍትሃዊ ተጠቃሚ ልሁን ብሎ ወደ ልመና የሚኬድ ከሆነ መቼም ቢሆን የኢትዮጵያ ተጠቃሚነት ስለማይረጋገጥ፤ እነዚህ አገሮች መፍትሔ ፈልገው ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንሁን ብለው ለድርድር የሚመጡትና ኢትዮጵያ ለዘመናት የታገለችለትን ፍትሃዊ ተጠቃሚነቷን የምታረጋግጠው መንግሥትና ህዝብ ጠንክረው ህዳሴ ግድቡን እንደጀ መሩት ሲያገባድዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢንጅነር ተፈራ ወንዙን ከሌሎች የተፋሰሱ አገራት ጋር በፍትሃዊነት ለመጠቀም ኢትዮጵያ ያላትን ጽኑ አቋም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሰፊው ማስረዳትና ማሳወቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ በተጓዳኝ የግድቡ መሰረተ ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ ስታደርገው እንደነበረው ድርድርና ምክክሩን መቀጠል እንደሚገባም ጠቁመዋል።

አዲስ ዘመን መጋቢት 9/2012
በሶሎሞን በየነ

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top