Connect with us

የጠ/ሚኒስትሩን ክብር የሚነካ ምስል ለቋል የተባለው የፕረስ ጋዜጠኛ የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀበት

ፍርድ ቤቱ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን በመግደል ለተከሰሱ አራት ግለሰቦች የመንግስት ተከላካይ ጠበቃ እንዲቆምላቸው አዘዘ
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

የጠ/ሚኒስትሩን ክብር የሚነካ ምስል ለቋል የተባለው የፕረስ ጋዜጠኛ የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ተጠየቀበት

በኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት ይፋዊ ድረገጽ ላይ የጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድን እና ባለቤታቸውን ክብር የሚነካ በፎቶሾፕ የተቀናበረ ምስል በማውጣት የተጠረጠረው የድርጅቱ ባልደረባ ጋዜጠኛ ድልነሳው ምንውዬለት ፖሊስ ፍ/ቤት አቅርቦት የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ መውሰዱ ተሰማ፡፡

ጋዜጠኛው መጋቢት 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጠ/ሚኒስትሩን አዋራጅ ነው የተባለለትን ምስል በድርጅቱ የፌስቡክ ገጽ ላይ ከለቀቀ በኃላ በዕለቱ በድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፊርማ ከሥራና ከደመወዝ ከመታገዱ በተጨማሪ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ የሚታወቅ ነው፡፡

ፖሊስ ተጠርጣሪውን የፌዴራል የመጀመሪ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በማቅረብ ለተጨማሪ ምርመራ የ14 ቀናት ቀጠሮ መቀበሉን ድሬቲዩብ አረጋግጧል፡፡

ጋዜጠኛ ድልነሳው ቀደምሲል በመንግሥት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ይሰራ እንደነበር የጠቀሱት ምንጮቻችንን ትንሽ የመቸኮል ባህርይ ከማሳየት በስተቀር የተለየ መጥፎ ባህርይ አልነበረውም ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት በኦንላይ ሚዲያ ላይ ተመድቦ ከመስራት በተጨማሪ በጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ተመድቦ ሲሰራ መቆየቱን ምንጮች ጨምረው ጠቅሰዋል፡፡

የተለቀቀው በፎቶሾፕ የተቀናበረ ምስል ጋዜጠኛው ከሌሎች ደረገጾች ያገኘው ይሁን ወይንም በራሱ የተዘጋጀ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም፡፡

በተያያዘ ዜና በዛሬው ዕለት መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ለቦርድ አባል ምርጫ በተመራጭ ላይ ሁለት ጊዜ ቆጠራ አካሂዶ ሹመቱን በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል ፡፡

ለኢትዮጵያ የፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባል ሆነው ከቀረቡ ዘጠኝ ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ላይ ቅሬታ ያቀረቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እንዳሉት ከሆነ ግለሰቡ የሀይማኖት እኩልነት ላይ የማያምኑ፣ በዜጎች መካከል ክፍፍል እንዲፈጠር የሚሰሩ፣ በማለት በሕዝብ የሚነሱባቸው ቅሬታ ወደ ጎን በመተው መቅረብ አልነበረባቸውም በሚል አባልነታቸውን ተቃውመዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባል ሆነው ከቀረቡት አባላት መካከል ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ላይ ቅሬታ በመቅረቡ ለብቻው ጉዳያቸው ታይቶ ድምጽ እንዲሰጥ የተደረገ ሲሆን በዚህን ሰዓት ድምጽ ያልሰጡ፣ድምጽ የሰጡ እንዲሁም የተቃውሞ ድምጽ ተጠቃልሎ ውጤቱ ይፋ ተደረገ፡፡ ነገር ግን በዚህን ጊዜ ከአንድ የፓርላማ አባል ….ቆጠራው ትክክል አይደለም… የሚል አስተያየት ተሰነዘረ፡፡

ምክርቤቱ የቀረበለት ቅሬታ ተመልክቶ ቀድሞ ያሳወቀው ውጤት ዳግመኛ ቆጠራ በማካሄድ የምርጫው ውጤት አሳውቋል ፡፡ በዚህም ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በ148 ድጋፍ በ126 ተቃውሞ እና 24 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ የቦርድ አባልነት ፀድቋል።

ዲያቆን ዳንኤል በአብላጫ ድምጽ ከተመረጡ በኋላ በምክር ቤቱ ቀርበው ቃለ መሀላ ከፈፀሙ የቦርድ አባላት መካከል ግን አልተገኙም ነበር።

በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ድምጽ ተሰጥቶበት ውጤት ከተነገረ በኋላ በድጋሚ ቆጠራ በማድረግ ውሳኔ የተሰጠበት የመጀመርያ አወዛጋቢ ያልተለመደ የምክርቤት ውሎ እንደነበር ለመታዘብ ችለናል፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top