Connect with us

“አጥንቴም ይከስከስ፣ ደሜም ይፍሰስላት”

“አጥንቴም ይከስከስ፣ ደሜም ይፍሰስላት”
Photo: Facebook

መዝናኛ

“አጥንቴም ይከስከስ፣ ደሜም ይፍሰስላት”

“አጥንቴም ይከስከስ፣ ደሜም ይፍሰስላት”
(በዘከሪያ መሐመድ)

በሰኔ ወር 1969 የሶማሊያ ጦር ኢትዮጵያ ላይ መጠነ ሠፊ የሆነ ወረራ ፈፀመ፡፡ ከሦስት አቅጣጫዎች የኢትዮጵያን ድንበር ሰብሮ የገባው የሶማሊያ ጦር የምሥራቅ ኢትዮጵያን ሠፊ ክፍል ከመቆጣጠር አልፎ የሐረር ከተማን ለመክበብ፣ እንዲሁም ድሬዳዋን ከተቀረው የአገሪቱ ክፍል ለመቁረጥ ተቃርቦ ነበር፡፡

የሐረር ከተማ ሕዝብ ከሶማሊያ ጦር የመድፍ ድብደባ የሚመሽግበት ጉድጓድ ለመቆፈር በተዳረገበት በዚህ የጦርነት ወቅት ለመደበኛው ጦርና በአጭር ጊዜ ሥልጠና ወደ ግንባር ለከተተው ሕዝባዊ ሠራዊት የውጊያ ወኔ በማስታጠቅ፣ እንዲሁም ሕዝቡን በተለያዩ መንገዶች የሠራዊቱ ደጀን እንዲሆን ዳር እስከ ዳር በማነቃነቅ ጥላሁን መቼም የማይረሳ ኪነ-ጥበባዊ ገድል ፈጽሟል፡፡

በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል በጦር ግንባር ከሚያካሂደው ኪነታዊ ተልዕኮ መልስ ጥላሁን ሐረር ወደሚገኘው የምሥራቅ ዕዝ ዋና መምሪያ ብቅ ይል ነበር፡፡ ከእነዚህ አጋጣሚዎች በአንዱ ዕለት የ፶ አለቃ ሙህዲን ጥላሁንን መኖሪያ ቤቱ ጋበዘው፡፡ በቆይታቸውም በተለያዩ ጊዜያት ከራዲዮ የቀዳቸውንና በሸክላ የተቀረፁ ዜማዎቹን፣ እንዲሁም በየጨዋታቸው መነሻነት ጥላሁን ለራዲዮ ጋዜጠኞች የሰጣቸውን ቃለ-ምልልሶች አስደመጠው፡፡ ጥላሁን የሚወዱትና የሚያደንቁት አያሌ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ቢያውቅም፣ ሙህዲን ለእርሱ ያለው ፍቅርና አክብሮት ለየት ያለ መሆኑን ተገነዘበ፡፡

ከዚያም ባሻገር በሙህዲን ጨዋነት እና ለባለቤቱ በሚያሳየው ፍቅርና አክብሮት ተማረከ፡፡ ቤታቸውም በጣም ተመቸው፡፡

ገዢ መሬቶችን በመቆጣጠር የሐረር ከተማን ቀለበት ውስጥ አስገብቶ የነበረው የሶማሊያ ሠራዊት በከባድ ፍልሚያና መስዋዕትነት ወደ ቆሬ ከተገፋ በኋላ፣ የማዕከላዊ ዕዝ የሙዚቃ ቡድን ሐረር መጣ፡፡ ለቡድኑ በተያዘለት መርኃ ግብር መሠረት በሐረር ዙርያ ለሚገኙ መኮንኖች፣ ለሠራዊቱ አባላትና ለቤተሰቦቻቸው በምሥራቅ ዕዝ አዳራሽ የሙዚቃ ዝግጅት ያቀርብ ነበር፡፡

ይህ ዝግጅት ሙህዲን ከነቤተሰቦቹ ጥላሁንን በመድረክ ላይ ለማየት የቻሉበትን መልካም አጋጣሚ ፈጠረ፡፡ የሙህዲን ሚስት ልጆቿን መስታወት እና ዕድላዊት ሙህዲንን ይዛ ወደ አዳራሹ ቀድማ በመግባት ከመድረኩ ፊት ለፊት በመጀመርያው ረድፍ ላይ ተቀመጡ፡፡ … ዘፋኝ መጣ፤ ዘፋኝ ሔደ፡፡ የሁሉም ታዳሚ ቀልብ ጥላሁንን ለማየት ቋምጧል፡፡ ተረኛው ድምፃዊ ዘፍኖ ሲጨርስ ታዳሚው አጨብጭቦ ይሸኘዋል፡፡ ከዚያ አዳራሹ በፉጨት ይደበላለቃል – “ጥላሁን! ጥላሁን! ጥላሁን!” የሚል ድምጽ ይስተጋባል፡፡

“አጥንቴም ይከስከስ” የተባለው የዘመኑ ወኔ ቀስቃሽ ዘፈን፣ በቀረበባቸው አዳራሾች ሁሉ ገና የመግቢያው ሙዚቃ መሰማት ሲጀምር ሥፍራው በፉጨት፣ በጩኸት እና በወኔ መናወጡ የተለመደ ትዕይንት ነበር፡፡ ጥላሁን ይህን ዘፈን ሲጫወት እንደ ጥንት አርበኛ እጀ ጠባብ ታጥቆ፣ እጅጌ አልቦ ሹራብ ደርቦ፣ ግንባሩ ላይ በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የተጠለፈ ሪባን ያስራል፡፡

በግራ እጁ ከድድር ቁርበት የተሠራ የጥንት አርበኞች ጋሻ፣ በቀኝ እጁ ደግሞ ጎራዴ ይጨብጣል፡፡ “አጥንቴም ይከስከስ፣ ደሜም ይፍሰስላት እንጂ ሀገሬን ጭራሽ፣ አይደፍራትም ጠላት፡፡”

ጥላሁን “አጥንቴም ይከስከስ” የሚለውን ሐረግ ሲያዜም ዓይኑን አፍጥጦ ጋሻውን በጎራዴው ይከተክታል፡፡ “ደሜም ይፍሰስላት” ሲል የጎራዴውን ስለት አንገቱ ላይ ያሳርፋል፡፡ ታዳሚውን ቁጭ ብድግ በሚያሰኝ አስገራሚ ትወና፣ ዓይኑን እያፈጠጠና እያጉረጠረጠ በኃያል ወኔ ነው የሚዘፍነው፡፡ የሦስት ዓመቷ ዕድላዊት ሙህዲን ከመድረኩ ፊት ለፊት የመጀመርያው ረድፍ ላይ በእናቷ ዕቅፍ ውስጥ ሆና ነበር ይህን የጥላሁን ትርዒት የምታየው፡፡ ጥላሁን ዓይኑን እያፈጠጠና እያጉረጠረጠ ሲዘፍን ዕድላዊት በፍርኃት ራደች፡፡

እናም እናቷ ጉያ ሥር ተወሽቃ ለቅሶዋን ታቀልጠው ጀመር፡፡ እናቷ ልታባብላት ሞከረች፡፡ ዕድላዊት ልትባበል አልቻለችም፡፡ እናቷ ደ’ሞ እሷን ስታባብል የጥላሁን የመድረክ ላይ ትንግርት እንዲያመልጣት አልፈለገችም፡፡ “አቦ ዝም በያ፣ ልይበት” ብላ ማባበሏን ትታ ጥላሁንን ፈዝዛ ታየው ገባች፡፡ ጥላሁን ዘፈኑን ጨርሶ ገባ፡፡ ቤቱ በጩኸትና በፉጨት ተደበላለቀ፡፡ “ቢስ! ቢስ! ቢስ!” ተባለ፡፡

የሙዚቃ ባንዱ አባላት ትንሽ ትንፋሽ ለመሰብሰብ ያቆሙ እንደሁ እንጂ ይህ ዘፈን ቢያንስ አንዴ፣ እልፍ ሲልም ሁለቴና ሦስቴ “ይደገም!” እንደሚባል ያውቃሉ፡፡ … እናም የመንደርደርያው ሙዚቃ ዳግም መሰማት ይጀምራል፡፡ አዳራሽ በፉጨት ይቀልጣል፡፡ የጥበብ አርበኛው ጥላሁን ዝሎ ሳይሆን ይበልጥ ግሎ ዳግም ወደ መድረኩ ብቅ ይላል፡፡ ዘፈኑን በድጋሚ ሲጫወት ከመድረክ ወርዶ ወደ ተመልካች ይሄዳል፡፡ ከመጀመርያው ይበልጥ በሞቀና በጋለ ስሜት ይጫወተዋል፡፡ … ጎራዴው ይበልጥ ይሰላል፤ ጋሻው ይከሸከሻል፡፡ … ዓይኑ ይበልጥ ይፈጣል፤ … ይበልጥ ይጉረጠረጣል፡፡ የሦስት ዓመቷ ዕድላዊት ከመጀመርያውም ይልቅ አሁን በጣም ተሸበረች፡፡ ጥላሁን ከመድረክ ወርዶ ጭራሽ ወዳለችበት መጣ፡፡ እርሷን እያየ ዓይኑን አፈጠጠ፤ እርሷም ከቀድሞው ይበልጥ ለቅሶዋን አቀለጠችው፡፡ … የሳቀ እንጂ አንድም ያባበላት ሰው አልነበረም፡፡

በማግሥቱ ከምሳ በኋላ ጥላሁን በመደበኛ ልብሱ ሙህዲን ቤት በእንግድነት መጣ፡፡ ሽርጥ ተሰጠውና በወጉ አገልድሞ ከሙህዲን ጋር ፍራሽ ላይ ተቀመጡ፡፡ የሙህዲን ሚስት ትናንትና እዚያ አዳራሽ ውስጥ ስለተፈጠረው ሁኔታ እያጫወተችው ነበር፡፡

በዚያው ቅጽበት ግን ጥላሁን አንዲት ሕፃን ልጅ ከበራፉ ደፍ ሥር ተቀምጣ በሚኮላተፍ ቃና ስታንጎራጉር ሰማና፣ “እሽሽ … እስቲ ቆይ! እስቲ ቆይ! አንዴ ዝም በሉ!” አለ፡፡ ሁሉም ፀጥ አሉና የሕፃኗ ልጅ ድምጽ ብቻ ይሰማ ጀመር፡፡ “አጥንቴም ይከስከስ”ን ለእርሷ እንደተሰማት በጣፋጭ የሕፃን አፏ እያዜመች ነበር፡፡

ቤቱ ውስጥ ያሉት ሁሉ በፀጥታና በአድናቆት እያዳመጧት ሳሉ ድንገት ወደዉስጥ ዞረች – ዕድላዊት፡፡ ወዲያውም ጥላሁን፣ “እንደዚያ ነው እንዴ ዘፈኑ?! እንደዚያ’ኮ አይደለም፡፡ ነይ እንዴት እንደሆነ ላሳይሽ” አለና ወደእርሱ እንድትቀርብ ጋበዛት፡፡ ሕፃኗ ዕድላዊት ግራ ተጋብታ ከተቀመጠችበት በመነሳት ወደ እናቷ ሄዳ የእናቷን ቀሚስ ጨምድዳ ያዘች፡፡ እናቷ ግን፣ “ሂጂ ወደሱ፣ ያሳይሽ፣ ሂጂ አትፍሪ” ብላ አደፋፈረቻት፡፡ ዕድላዊት ፈራ ተባ እያለች ጥቂት እርምጃ

ወደ ጥላሁን ቀረበች፡፡ ጥላሁን ቀጥሎ ያደረገው የ፶ አለቃ ሙህዲንም ሆነ ባለቤቱ፣ እንዲሁም ልጃቸው መስታወት ፈጽሞ ያልጠበቁትን ነበር፡፡ … እንደተቀመጠ ቀና አለና ልክ መድረክ ላይ የሚያወጣውን ያህል ኃያል ድምጽ በማውጣት “አጥንቴም ይከስከስ”ን ያዥጎደጉደው ጀመር፡፡ በአንድና በሁለት ስንኝ አላቆመም፡፡

የሀገሬ ጀግኖች ሴት ወንዱ ታጠቁ
ከእንግዲህ ለጠላት አንተኛም ንቁ፣…
ጀግንነት እንደሆን የአባቶቻችን ነው
ሕብረታችን ፀንቷል ድል መምታት የእኛ ነው
ስለዚህ አንራራም፣ ግዴለንም እኛ
ታጥቀን ተነስተናል፣ ለኔን ትተን ለኛ፡፡ …

የጥላሁን ድምጽ ከቤት አልፎ ውጪ ድረስ ይሰማ ስለነበር የጎረቤት ሰዎች ተንጋግተው በመምጣት ሙህዲን በር ላይ ተኮለኮሉ፡፡ ጥላሁን ዓይኖቹን ዕድላዊት ላይ ተክሎ መዝፈኑን ቀጠለ፡፡… አክትሟል አበቃ፣ የናንት ምዕራፋችሁ የማይሆን ቅዠት ነው፣ ከንቱ ነው ህልማችሁ፡፡ ብትቅበዘበዙ፣ አልፋችሁ ከልኩ
ባንድነት ብለናል፣ ሀገሬን አትንኩ …

“አጥንቴም ይከስከስ፣ ደሜም ይፍሰስላት
እንጂ ሀገሬን ጭራሽ አይደፍራትም ጠላት፡፡ …

“ዐየሽ እንደዚህ ነው የሚዘፈነው፣ አሁን ገባሽ?” አላት፡፡ ዕድላዊት ትናንት እዚያ አዳራሽ ውስጥ እንዲያ ዐይኑን እያፈጠጠ ሲያስለቅሳት የነበረው፣ ይሄ እቤታቸው ፍራሽ ላይ የተቀመጠው ሰውዬ መሆኑን አወቀች፡፡ … ዛሬ ግን እንደ ትናንቱ አላለቀሰችም፡፡

ይልቁንም እናቷንና አባቷን እያየች ሳቋን ለቀቀችው፡፡ ጥላሁንም ጣፋጭ ሳቋን እየተጋራ ‹ነይልኝ› ብሎ አቅፎ ሳማት፡፡ ከዚያም ጉልበቱ ላይ አስቀምጦ ከሙህዲን እና ከባለቤቱ ጋር ጨዋታውን ቀጠለ – ዕድላዊት ዓይን ዓይኑን እያየችው፡፡ … በር ላይ የተኮለኮሉት ጎረቤቶች “ቢስ!…” ለማለት ስላልደፈሩ ያቺን ጣፋጭ አጋጣሚ ተጋርተው … ከሞቀ ፈገግታ ጋር ወደየመጡበት ተመለሱ፡፡

የሙህዲን የመጀመርያ ልጅ፣ መስታወት ሙህዲን ከ32 ዓመታት በፊት ምሥራቅ ዕዝ ግቢ ውስጥ ይገኝ በነበረው ቤታቸው የሆነውን የዚያን ዕለት ትዕይንት ከነሙሉ ድባብ እና ለዛው፣ ዛሬ ቀላድ አምባ በሚባለው ሠፈር ከሚገኝ መኖሪያ ቤቷ በእንግድነት ጎራ ላለው ለዚህ ደራሲ ስትተርክለት፣ … እንግዳው ዕድላዊት ያፈላችለትን ‘ጥዑም’ ቡና ፉት እያለ ነበር ያደመጣት፡፡

ምንጭ – “ጥላሁን ገሠሠ፣ የሕይወቱ ታሪክና ምሥጢር”፣ ገጽ 253-255

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in መዝናኛ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top