Connect with us

በግብጾች ከተወረርን እኮ ቆየን!!

በግብጾች ከተወረርን እኮ ቆየን!!
Photo: Reuters

ፓለቲካ

በግብጾች ከተወረርን እኮ ቆየን!!

በግብጾች ከተወረርን እኮ ቆየን!! | (ጫሊ በላይነህ)

የሰሞኑ የእነትራምፕ ማስጠንቀቂያ ከገባንበት ድባቴ እያነቃን መሆኑ እሰየው ነው፡፡ በዚህ ላይ ከውጫሌ ውል ጋር ተያይዞ ተገደን ወደጦርነት የገባንበት የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ጋር ነገሩ መገጣጠሙ ውስጣችን ተዳፍኖ ያለውን የአትኩኝ ባይነት ወኔ እንዲቀጣጠል ምክንያት ሆኗል፡፡ እነትራምፕ የግድባችሁን ውሃ ሙሌት ካለእኛ ስምምነት እንዳትሞክሩት ማለታቸው የፖለቲካ ሹኩቻችንን አቆይተን በአንድ እንድንቆም በር እንዲከፈት አድርጓልና ሚስተር ዶናልድ ትራምፕን ከዚህ አንጻር አለማመስገን ንፉግነት ይሆናል፡፡

ሰሞኑን ይህንኑ ወቅታዊ ጉዳይ ተከትሎ በአንዳንድ ወገኖች በኩል ግብጽ ልትወረን ትችላለች የሚሉ ሥጋቶች ተደጋግመው እየተሰሙ ነው፡፡፡ በእርግጥም የግብጽ ባለሥልጣናት የተለመደ ፋከራና ሽለላ ደምቆ እየታየ መሆኑ እውነት ነው፡፡ እኔ ግን እላለሁ፤ ግብጽን ከወረረችን እኮ ቆየች፡፡

እስቲ ልብ ብለህ ተመልከት?!.. ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት በአመዛኙ ብሔር እና ሃይማኖት ተኮር ግጭቶች እዚህም እዚያም ሲፈነዱ የታዩት በአጋጣሚ መስሎህ ከሆነ ተሳስተሃል፡፡ የአገሬ ሰው እስላሙም ክርስቲያኑም ቀና ብሎ የማያያቸውን የእምነት ተቋማት እንደችቦ የነደዱት ለምን ይመስለሃል?

ታቦት አላስገባ፣ አላስወጣ ብሎ፣ የሃይማኖት ነጻነትን ለመገዳደር እምቡር እምቡር ያለው መንጋ፣ መስጊድን ለማፈራረስና ለማቃጠል እጁ የፈረጠመው መንጋ የተፈጠረው በገጠመኝ እንዳልሆነ ለአንተ መንገር ለቀባሪ ማርዳት ይሆናል፡፡

ለመሆኑ ይህ ሁሉ ክፋት ከየት የመጣ ኢትዮጵያዊነት ይመስልሃል? መልሱ ቀላል ነው፡፡ ግጭቶቹ እንደክብሪት እንዲቀጣጠሉ የተጫሩ እሳቶች ነበሩ፡፡ እርስ በርስ በጎሳና በሃይማኖት ተቧድነን እንድንባላ የታቀዱ ፕሮጀክቶች ነበሩ፡፡ በፈጣሪ ብርታት ባይከስሙ ኖሮ የግብጾች ሕልም ይሳካ ነበር፡፡

አዎ! ከተወረረርን ቆይተናል፡፡ ትላንት ወንድም በወንድሙ ላይ፣ ጎረቤት በጎረቤቱ ላይ፣ መንደርተኛው በሌላው መንደርተኛ ላይ ወደሶዶ ማሳደድ የገባው እነዚሁ ተከፋይ ፖለቲከኞች በቆሰቆሱት እሳት፣ በረጩት ገንዘብ ምክንያት ነው፡፡

አዎ! በግብጾች ከተወረርን ቆይተናል፡፡ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው ግጭት የሚያቀጣጥሉ ሰዎች ተፈጥረው የተመለከትነው ተከፋይ ሕሊናቢሶች፣ ከሃዲዎች በመብዛታቸው ነው፡፡

ከዛሬ 124 ዓመት በፊት ለወራሪው ጣሊያን ያደረ አገሬ “ባንዳ” ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ ባንዳው ዘመዱ ሆዱና ሆዱ ብቻ ነው፡፡ የወገንን መረጃ ለጠላት አሳልፎ ይሰጣል፤ ያስጠቃል፡፡ ጠቁሞ፣ መርቶ ያሳስራል፤ ያስገድላል፡፡ ለጠላት ክፉ ሴራ ይተባበራል፡፡ ከጠላት ጎን ተሰልፎ ጥቃት ያደርሳል፣ ንብረት ያቃጥላል፤ ያወድማል፡፡

የዘመኑ ባንዳዎች እንዲሁ በተመሳሳይ መልኩ አገርን እየሸጡ ነው፡፡ አገርና ሕዝብ ሠላም እንዳይኖረው ቆመው የሚያድሩ ክፉ ጋኔሎች ናቸው፡፡ በሰው ክንድ የዘንዶን ጉድጓድ ለመለካት ሲባዝኑ የሚውሉ አረመኔዎች ናቸው፡፡

እናም የሚያሰጋን ግብጾች ቀጥተኛ ወረራ አይደለም፡፡ የሚያሰጋን የግብጽ ወታደርና መሳሪያ ብዛትም አይደለም፡፡ እሱንማ እንዴት እንደምንመክት ከአባቶቻችን ከተማርን ቆየን፡፡ ይልቅስ መፍራትስ አንተና እኔን መስሎ፣ እንደቀበሮ ባህታዊ መሃላችን ተሸጉጦ ለግብጾች የሚሰራውን፣ ለጠላት ያደረውን ባንዳ ነው፡፡ ለግብጾች አድሮ ሠላምን እየነሳን ያለውን ክፉ ጋኔል ከመሃላችን ካላስወገድን መቼም ሠላም አይኖረንም፡፡ በአጭሩ የተነሳብንን የውክልና ጦርነት ማስቆሙ ላይ በርትተን እንስራ፡፡ በላባችን፣ በደማችን የሚሸቅጡ ብልጣብልጥ ነጋዴ ፖለቲከኞችን በቃ የምንላቸውም በዚሁ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ባንዳ ፖለቲኞቻችን ሆይ በቃችሁ!!

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top