በተለያየ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ገብተው በሕገወጥ መንገድ በሚኖሩ የውጭ አገር ዜጎች ላይ እርምጃ ሊወሰድ መሆኑን የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጅብ ጀማል በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በተለያየ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ገብተው ሕጋዊ ሳይሆኑ በሕገወጥ መንገድ በአገሪቱ የሚኖሩ የውጭ አገር ዜጎች ወደ ኤጀንሲው መጥተው ሕጋዊ መስመር የማይይዙ ከሆነ ለአገርና ለህዝብ ደህንነት ሲባል እርምጃ ይወሰዳል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ በተለያዩ ምክንያት በቪዛ ወደ አገር ውስጥ ከገቡ የውጭ አገር ዜጎች መካከል አንዳንዶቹ የቆይታ ጊዜያቸውን ያሳለፉ ሲሆን፤ አንድ የውጭ ዜጋ የቆይታ ጊዜው አልፎ ከሕግ ውጭ ከተቀመጠ ድርጊቱ በሕግ የሚያስቀጣ በመሆኑ በሕገወጥ መንገድ የሚኖሩ የውጭ አገር ዜጎችን ወደ ሕግ ሥርዓት ለማስገባት ከሰኔ 2011 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 15 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ወደ ኤጀንሲው በመምጣት እንዲመዘገቡ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ማስታወቂያ ሲያስተላልፍ ቆይቷል።
ኤጀንሲው በወጣው ማስታወቂያ አማካኝነት 303 የተለያዩ የውጭ አገር ዜጎች ሕጋዊ ለመሆን የተመዘገቡ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 170 የሚጠጉ ሰዎች ያለባቸውን ውዝፍ ቅጣት በመክፈል፤ የመክፈል አቅም የለንም ላሉ ደግሞ ኤጀንሲው ትብብር በማድረግ ግማሽ ቅጣት እንዲከፍሉ በማድረግ እንዲሁም ለመክፈል ምንም አቅም የሌላቸውን የመውጫ ቪዛና የትራንስፖርት ወጪያቸውን ተሸፍኖ ከአገር እንዲወጡ ውሳኔ አግኝተው ከአገር እንዲወጡ መደረጉን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
በአራት ወራት ውስጥ ሕጋዊ ለመሆን በኤጀንሲው ከተመዘገቡት 303 የውጭ አገር ዜጎች ውስጥ 170 የሚጠጉት ሕጋዊ ሆነው ከአገር ሲወጡ፤ የተወሰኑት እዚሁ ስደተኛ ሆነን እንቀመጣለን በማለታቸው ወደ ስደተኞች ካምፕ የገቡ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
በተለያየ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ገብተው ህጋዊ ሳይሆኑ ብዙ የውጭ አገር ዜጎች በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች እንደሚኖሩ ዳይሬክተሩ ጠቁመው፤ እነዚህ በሕገወጥ መንገድ የሚኖሩ የውጭ አገር ዜጎች ህጋዊ እንዲሆኑ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ማስታወቂያ ቢተላለፈም አሁንም በሕገወጥ መንገድ እንደሚኖሩ፤ ለአገርና ለህዝብ ደህንነት ሲባል ኤጀንሲው ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሕገወጥ የውጭ አገር ዜጎች ህጋዊ እንዲሆኑና ህጋዊ በማይሆኑት ላይ ደግሞ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።
የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ከስደተኞች ኤጀንሲ፣ ከጠቅላይ ዓቃቢ ሕግ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ ደህንነትና መረጃ፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከክልል መስተዳድር የፀጥታ ቢሮ የተውጣጡ አባላት ያለው ኮሚቴ መቋቋሙን ዳይሬክተሩ ጠቁመው፤ ኮሚቴው ሁለት ዙር ተገናኝቶ በመወያየት ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስቸለውን ዕቅድ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ኮሚቴው በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገባ ሲሆን፤ በቅድሚያ ስደተኞች ወደ ኤጀንሲው መጥተው እንዲመዘገቡ የማሳወቅ ሥራ እንደሚሠራ፣ ህጋዊ ሆነው ወደ ስደተኛ ጣቢያ መግባት የሚፈልጉ ስደተኞች ወደ ስደተኛ ጣቢያ እንዲገቡ፣ ከአገር መውጣት የሚፈልጉ ደግሞ ቅጣቱን ከፍለው ወደ መጡበት እንደሚመለሱ እንደሚያደርግ፤ ወደ ኤጀንሲው ቀርበው ሕጋዊ በማይሆኑት ላይ ግን ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።
(አዲስ ዘመን የካቲት 4/2012)