Connect with us

የጀዋር ሲራጅ መሐመድ ምላሽ በተለይ ለምርጫ ቦርድ

የጀዋር ሲራጅ መሐመድ ምላሽ በተለይ ለምርጫ ቦርድ
Photo: Facebook

ፓለቲካ

የጀዋር ሲራጅ መሐመድ ምላሽ በተለይ ለምርጫ ቦርድ

እውነቱን ለመናገር ከዜግነት ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰዎች እያነሱት ያለውን መናኛ አጀንዳ ብዙም ልገባበት አልፈለግኩም ነበር፤ ኾኖም አሁን በግድ ወደ አጀንዳው እያስገቡን ነው፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉም በሚያስብል ደረጃ በውጪ ሀገራት የነበሩ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶችና ጋዜጠኞች የውጪ ሀገር ፖስፖርት ተጠቃሚዎች ነበሩ፡፡ ብዙዎቹ እነዚህ በውጪ ሀገራት የነበሩ ሰዎች ዛሬ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እየመሩና የጀርባ ታሪክና ዜግነትን ጭምር ማጣራትና መፈተሸን የሚጠይቁ ሚስጥራዊና ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ጭምር ውሳኔ የሚሰጡ ሰዎች ኾነዋል፡፡ የእነዚህን ሰዎችና የሥራ ድርሻቸውንም መጥቀስ ይቻላል፡፡

አስገራሚው ነገር ግን ከእነዚህ ሁሉ ሰዎች ተለይቶ የእኔ ብቻ የዜግነት ጉዳይ አጀንዳ እንዲኾን እየተደረገ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል፡- የተጥቅ ትግል እንቅስቃሴ ሲመራ የነበረው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ከዚህ ቀድም ባወጣው ዘገባ መሠረት (የተያያዘውን ምስል ይመልከቱ) የኤርትራ ፓስፖርት ነበር የነበረው፡፡ ይኼን መረጃ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰዎች በደንብ ያውቁታል፡፡ የሌሎችም በርካታ ከውጪ ተመላሽ ሰዎች የዜግነት ኹኔታ በምርጫ ቦርድ አመራር ሰዎች በደንብ ይታወቃል፡፡

(የብርሃኑ ነጋን እዚህ የጠቀስኩት ጉዳዩ በይፋ ጋዜጣ ላይም የታተመ ስለኾነ ነው) አስገራሚው ነገር የእኔ ዜግነት ላይ ብቻ ነጥለው ማትኮራቸው ነው፡፡ ለመኾኑ ፕሮፌሰር ብርሃኑንና ሌሎችንም ልክ እንደእኔ ዜግነታቸውን እንዲያረጋግጡ ጠይቀዋል? የእኔ ላይ እንዳደረጉት የብርሃኑን የዜግነት ጉዳይ ወደ ሚዲያ በማውጣት አጀንዳ አድርገውታል? አላደረጉም!

እኔን በተመለከት አንድም ቀን ቢኾን የአሜሪካ ዜግነት መውሰዴን ደብቄ አላውቅም፡፡ ለምርጫ እንደምወዳደር ከወሰንኹ በኋላ ግን የአሜሪካን ዜግነቴን መተው እንደምፈልግ በይፋ ገልጫለኹ፡፡ ለዚህም አስፈላጊውን ሂደት አከናውኛለኹ፡፡ ለአሜሪካ ኤምባሲ ፓስፖርቴን መልሻላኹ፣ የአሜሪካን ዜግነት ማጣቴንም የሚያረጋግጥ ሰርተፍኬት ተቀብያለሁ፡፡ በቀጣይነትም ይኼን ማስረጃና ሌሎች የሚጠየቁ ሰነዶችን በማሟላት ለሚመለከተው የኢትዮጵያ መንግሥት መሥሪያ ቤት አስገብቻለሁ፡፡ ይኼንን ያከናወንኩትንም ሂደት ፓርቲዬ ኦ.ፌ.ኮ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አሳውቋል፡፡ ይኼ ሁሉ ተከናውኖም የምርጫ ቦርድ ሰዎች ጉዳዩን ከማንሳት አልታቀቡም፡፡ ለምን ይኾን? ብዙዎች እንደሚጠረጥሩት ይኼን ሰበብ አድርገው በምርጫው እንዳልሳተፍ ሊያቅቡኝ ይፈልጋሉ፡፡ ምንአልባም እንደዛ አስበው ሊኾን ይችላል፡፡

1. መጀመሪያ በዚህ ቁርጡ ባልለየለት የፖለቲካ ኹኔታ የአሜሪካ ዜግነቴን በራሴ የምተው አልመሰላቸውም ነበር፡፡ ላጭበረብር እንዳሰብኩ ገምተውም ነበር፡፡ ምንም አይደል፤ ለዚህ አጉል ጥርጣሬያቸው ይቅር ብያቸዋለሁ፡፡ ለሕዝባችን መሻት ስንል እንኳን ፓስፖርታችንን አስፈላጊ ከኾነም ሕይወታችንን ለመስጠት ቁርጠኛና ዝግጁ እንደኾንን አልተረዱም፡፡

2. ዜግነት የመመለስ ሂደቱን እንደጀመርኩ ሲረዱ ደግሞ፣ ዜግነት የመመለሱ ሂደት ረዝሞ ምርጫው ሊያመልጠኝ እንደሚችል ተስፋ አደረጉ፡፡ ነገር ግን ሂደቱ ከገመቱት ውጪ በፍጥነት ተጠናቀቀና የአሜሪካን ዜግነት ማጣቴን የሚያረጋግጥ ሰርተፍኬት ተቀበልኩ፡፡

3. አሁን ከእኔ የሚጠበቁ ሕጋዊ ሂደቶችን ሁሉ ፈጽሜም እንኳ የምርጫ ቦርድ ሰዎች የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ላይ ጫና በመፍጠር ሂደቱን ለማወሳሰብ እየሞከሩ ነው፡፡ ኾኖም ይኼን ለማድረግ ምንም የሕግ ድጋፍ የላቸውም፡፡ በእኔ በኩል የሚጠበቁ ሦስት ሂደቶችን በአግባቡ ፈጽሚያለኹ፡፡ የዜግነት ሰነድ መልሻለኹ፣ የቀድሞ ዜግነቴን ጥያለኹ፣ ማመልከቻዬንና ሰነዶቼን ለሚመለከተው የመንግሥት ቢሮ አስገብቻለሁ፡፡

ጉዳዩ ለሚያሳስባቸው ወገኖች የምለው ነገር፡- በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የምናደርገው ነጻ፣ ገለልተኛና ፉክክር የተመላበት ምርጫ ላይ ሙሉ ትኩረታችንን እንድናደርግ ነው፡፡ ይኼንን ታሪካዊ አጋጣሚ በአግባቡ እንዳንጠቀም ከሚያደርጉ መናኛ አጀንዳዎች ራሳችንን እናርቅ፡፡ በእኛ በኩል የጨዋታውን ሕግ እናውቀዋለን፣ ለሕጉም ተገዢዎች እንኾናለን፡፡ ሕጉን በምንም መልኩ የመጣስ ፍላጎት የለንም፡፡ በምርጫው ሰላማዊና ሕጋዊ ኾነን በሙሉ ልባቸውን ነው የምንሳተፈው፡፡ በዚህ ሂደት ከማንም አካል ውለታ አንጠይቅም፤ ከማንም በተለየ መድልኦ እንዲደረግብንም አንሻም፡፡ ብዙ የለፋነውና መስዋእትነትም የከፈልነው ለዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ለመብቃት ነው፡፡ ሂደቱ ፍሬ እንዲያፈራም በቃላችን ታምነን እንቆያለን፡፡

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top