Connect with us

የታዬ ደንደአ ሁለት ሚሊየን ብር መዘረፍ ያስነሳው አቧራ

የታዬ ደንደአ ሁለት ሚሊየን ብር መዘረፍ ያስነሳው አቧራ
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

የታዬ ደንደአ ሁለት ሚሊየን ብር መዘረፍ ያስነሳው አቧራ

የታዬ ደንደአ ሁለት ሚሊየን ብር መዘረፍ ያስነሳው አቧራ | (ጫሊ በላይነህ)

የኦሮሚያ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ታዬ ደንደአ ሁለት ሚሊዮን ብር ተዘረፍኩኝ በሚል ለቢቢሲ መናገራቸው ማወያየቱን ቀጥሏል፡፡ እንደእሳቸው አባባል ዘረፋው የተፈጸመው ለሥራ ጉዳይ ወደ ቢሾፍቱ በሄዱበት ወቅት ነው፡፡ በዘረፋውም መኪና ውስጥ የነበረ ሁለት ሚሊዮን ብር እና ሌሎች ንብረቶች ተወስዶባቸዋል፡፡

ዝርፊያው የተፈፀመበት ሁኔታም ሲያስረዱም፤ ቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ቢን ኢንተርናሽናል በተባለ ሆቴል ምሳ ለመመገብ መኪናቸውን አቁመው በገቡበት ጊዜ “የመኪናቸው በር በማስተር ቁልፍ ተከፍቶ” የተጠቀሰው ገንዘብና የተለያዩ ንብረቶች እንደተዘረፈባቸው ተናግረዋል።

ይህ ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ በመኪናቸው ይዘው የነበረው በቢሾፍቱ ከተማ ሥልጠና እየተከታተሉ ለነበሩ ለሰልጣኞች የሚከፈል አበል እንደነበር ጨምረው አስረድተዋል።

ከገንዘቡ በተጨማሪ ላብቶፕ ኮምፒውተር እና ሁለት የሥራና የግል ጉዳዮችን የሚጽፉባቸው ማስታወሻ ደብተሮች እንደተሰረቁባቸው ተናግረዋል።

ጨምረውም ስርቆቱ ከተፈፀመ በኋላ “የታዬ ማስታወሻ ደብተር እጄ ገብቷል” ብሎ የፌስቡክ ገፁ ላይ የጻፈ ግለሰብ መኖሩንና ጉዳዩን ወደ ሕግ መውሰዳቸውንም ያስረዳሉ።

የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ ስለጉዳዩ ተጠይቆ ምርመራ እየተካሄደ ስለሆነ ተጣርቶ ሲያልቅ ይፋ እንደሚደረግ የከተማው ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ደረጀ ሙለታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአቶ ታዬ ደንደአ የማስታወሻ ደብተር መሰረቁን ፌስቡክ ገፁ ላይ ጻፈ ያሉት ግለሰብ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሃሳብ በመስጠት የሚታወቀው ደረጀ ቤጊ የተባለ ግለሰብ ነው።

በጉዳዩ ላይ ቢቢሲ ያነጋገራቸው አቶ ደረጀ “እንደማንኛውም ጊዜ በፌስቡክ የመልዕክት ሳጥኔ እንደተላከልኝ አስታውቄ ነው ማስታወሻዎቹ መሰረቃቸውን የፃፍኩት” ብለዋል።

“በውስጥ መስመር ነው የተላከልኝ፤ የለጠፍኩትም [ኢንቦክስ] ብዬ ነው። ታዬ መዘረፉንም ሆነ ስለ እርሱ ምንም የማውቅው ነገር የለኝም” ብለዋል።

አቶ ታዬ መዘረፋቸውን በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል የተባለው ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ የተሰማ ቢሆንም ለማረጋገጥ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

አቶ ታዬ ደንደአ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ሲሆኑ በመገናኛ ብዙህን እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የፓርቲያቸውንና የራሳቸውን አቋም በመግለጽ ይታወቃሉ።

አቶ ታዬ ደንደአ በተለይም በቅርቡ ኦፌኮን የተቀላቀለው በብዙዎች ዘንድ አይነኬ ተደርጎ የተሳለውን የአቶ ጀዋር ሲራጅ መሐመድን መስመር የሳቱ ቅስቀሳዎችን፣ የጥላቻ ንግግሮችን ደፍረው በማጋለጥ፣ በመተቸት ይታወቃሉ፡፡

በአዳማ ሲካሄድ የሰነበተው የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ሥልጠና በዛሬው ዕለት ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ በተገኙበት የመዝጊያ ሥነሥርዓቱ ተከናውኗል፡፡

የአቶ ታዬ ደንደአ ለአበል ክፍያ የያዙት ገንዘብ መዘረፉ ከተሰማ በኋላ በሶሻል ሚዲያው ብልጽግና ፓርቲ በመንግሥት ገንዘብ ስብሰባ አካሂዷል የሚሉ ክሶችን የሚያዥጎጉዱ ሰዎች ታይተዋል፡፡ ይኸ ክስ አንድ ነገር አስታውሶኛል፡፡ በምርጫ 97 ኢህአዴግ ከፓርቲዎች ጋር ምርጫ ቦርድ ለስብሰባ በተቀመጠበት ወቅት አሁን ለጊዜው ከዘነጋሁት አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ (ባልሳሳት ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ይመስሉኛል) ጥያቄ አዘል ትችት ይነሳል፡፡ ትችቱ የኢህአዴግ ጎምቱ ሰው አቶ በረከት ስምኦንን የሚመለከት ነበር፡፡

የቀረበው ትችት በአጭሩ “አቶ በረከት በመንግሥት መኪና ጭምር እየተጠቀመ የፓርቲ ሥራ ያከናውናል፣ እዚህ ስብሰባ እንኳን የመጣው የመንግሥት መኪና ይዞ ነው” የሚል ነበር፡፡ አቶ በረከት ሆዬ ከምሳ በኋላ ወደስብሰባ አዳራሽ ሲመጡ በጠዋቱ ክፍለጊዜ የተተቹበትን አራት ቁጥር መኪናቸውን በሌላ ሁለት ቁጥር መኪና ቀይረው መምጣታቸው መሳቂያ፣ መሳለቂያ አድርጓቸው እንደነበር አስታውሳለኹ፡፡

እናም በብልጽግና ላይ የተሰነዘረው ሥጋት ምንም ቁምነገር የሌለው አድርጎ መውሰድ አይቻልም፡፡፡ ለምን ቢባል ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ባለፉት ዓመታት የመንግስት ገንዘብ፣ ተሽከርካሪ፣ ጊዜ እንዲሁም የፓርቲውን መዋቅር ጭምር እየተጠቀመ መቶ በመቶ አሸንፌያለሁ ወደሚል ኩምኩና መሸጋገሩ ላስታወሰ ክሱ ውሃ እንደሚያነሳ ይገነዘባል፡፡ ይኸም ሆኖ ግን ብልጽግና የሐብታሙ ኢህአዴግ ወራሽ በመሆኑ ለአበል ክፍያ የሚሆን ገንዘብን ያጣል ብሎ ማሰብ ግን አንድም ኢህአዴግን አለማወቅ አሊያም የዋህነት ይሆናል፡፡

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top