Connect with us

ቀጭዎችን ፍለጋ በሱማሌዎቹ ቀዬ …

ቀጭዎችን ፍለጋ በሱማሌዎቹ ቀዬ

መዝናኛ

ቀጭዎችን ፍለጋ በሱማሌዎቹ ቀዬ …

ቀጭዎችን ፍለጋ በሱማሌዎቹ ቀዬ
ገራሌ ብሔራዊ ፓርክን ፍለጋ
****
ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በኢትዮጵያ ጠረፍ የሚገኘውን የገራሌ ብሔራዊ ፓርክ ፍለጋ ተጉዟል፡፡ በገራሌ ቆይታው በሱማሌዎቹ ቀዬ ቀጭኔዎቹን ፍለጋ ላይ ነኝ ሲል ቆይታውን እንዲህ ያካፍለናል፡፡ | ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

ከሙባረክ ወረዳ ተነስተናል፡፡ ሙባረክ ኢትዮጵያ ውስጥ ናት ግን ደግሞ የኬኒያ ሽልንግ እንደ ሞያሌ ነፍስ ዘርቶ ይገዛባታል፡፡ ኑሮ ውድ ነው፡፡ ያም ኾኖ እንጀራ አለ፡፡ ሩዝ ዋናው ምግብ ሲሆን ብዙው ሰው በስጋ ይበላዋል፡፡ ስለምትሞቅ ቀዝቃዛ መጠጦች ሰፊ ገበያ አላቸው፡፡

በተለይም ውሃና ለስላሳ፤ ሙባረክ አርፈን የመጨረሻውን ምሳ በልተናል፡፡ ከዚህ በኋላ ሕይወት የሚቀጥለው ዱር ውስጥ ነው፡፡ ወደ ጠረፋማዋ ቀበሌ አመራን፡፡ መሐመድ ማሌዲ ሚኒሺያ ነው፡፡ መንገድ ይመራናል፡፡ ቀጭኔ ሊያሳየን የተመረጠ አዋቂ ነው፡፡ ከዚያ ሲያልፍ ዱሩን እንደ ቤቱ የሚያውቅ ነውና ለብዙ ነገር ይጠቅማል፡፡

መቤ ፋይዳ የለውም እያለ ፋይዳ ያጡ ጉዳዮችን አንስቶ ይጥላል፡፡ ጨዋታዎቹ አይጠገቡም፡፡ የብሔራዊ ፓርኩ ስካውቶች የቀጠና አስተባባሪ ነው፡፡ አሎ ብርቲ ቀበሌ ደረሰን፡፡ የመጨረሻዋ የብሔራዊ ፓርኩ ወደብ ናት፡፡ ተጨማሪ ሚሊሺያዎች ተቀላቀሉን፡፡ ጥቂት እንደተጓዝን ብሔራዊ ፓርኩ ገላ ገባን፡፡

ገራሌ ተደብቆ የኖረ ፓርክ ነው፡፡ ስሙ በአካባቢው ከሚኖረው ገሪ የተባለ ግዙፍ የሱማሌ ጎሳ የመጣ እንደሆነ መቤ አጫውቶኛል፡፡ እንዲህ እንሰሳ እንደልብ የሚታይበት ብሔራዊ ፓርክ በእኔ ሀገር ጥቂት ነው፡፡ አንዱጋ መጥቻለሁ፡፡

የሜዳ ፍየሉ ብዙ ነው፡፡ ገረኖው ቁጥር የለውም፡፡ አጋዘኑ ግራና ቀኝ ይሮጣል፡፡ ሳላዎቹ ያልደረቀው ሳር ሸሽጓቸውም ይታያሉ፡፡ ሰጎኖች ሜዳው ተመችቷቸዋል፡፡ ሳልቆም የማየውን ሳስብ ቆሜ በፍለጋ ያጠኋቸው የዱር እንስሳትን መኖሪያዎች አሰብኩ፡፡

ገራሌ የወፍ ሀገር ነው፡፡ የሚሰማው ሁሉ የወፍ ድምጽ ነው፡፡ እዚህም እዚያም ዓይነተ ብዙ ወፍ ይታያል፡፡ ደግሞም ይሰማል፡፡ የሚታየው የሚደመጥበት ልዩ ፓርክ፡፡

ፓርኩን የወረረ የመሬት ቀበኛ አላየሁም፡፡ ከብቶች ዝር ያላሉበት የሀገሬ የተፈጥሮ ሀብት ውስጥ መግባቴን አመንኩ፡፡ ወዲህ አርብቶ አደር ምድር ብሆንም የጎሳው ጠንካራ ህግ ገራሌን ታድጎታል፡፡

የኢንሹ ሀገር ነው፡፡ ኢንሹን እንዲህ ከጥንድነት ወደ ቤተሳባዊ ጉድኝት አድጋ ያየሁበትን ስፍራ ማስታወስ አልቻልኩም፡፡ ኢንሹ ትንሽና ጥንድ ሆና የምትኖር ባለ ትዳር እንሰሳ ናት፡፡ እዚህ ቁጥሯ ቁጥር የለውም፡፡

ውሃ ኩሬ ጋር ደረስን፡፡ ውሃ ኩሬውን ለማየት መኪናችንን አቁመን ወርደን ወደ ዳርቻው ተጠጋን፡፡ መንገድ መሪው መሬቱን እቃ እንደ ጣለ ሰው አቀርቅሮ አሰሰው፤ ወደ ውሃው ስንጠጋ ኮቴ አየን፡፡ የቀጭኔዎች ነበር፡፡ የሄዱበትን ዳና ተከተልነው፡፡ ግን መሽቷል፡፡

አንዱ ጥላ ስር ድንኳኖቻችን መጣል ጀመርን፡፡ ጀንበርን ተሻማናት፤ ሲነጋ ቀጭኔዎቹ በሄዱበት እንሄዳለን፡፡ ታሪኩ የብሔራዊ ፓርኩ ዋርደን ነው፡፡ ቀጭኔዎቹን እንድናይለት ጓጉቷል፡፡ ሁነኛ ምስክር የሚፈልገውን ብሔራዊ ፓርክ ዓይኖቻችን ይታደጉት ይሆናል፤ ማን ያውቃል?

Click to comment

More in መዝናኛ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top