ይገርመኛል!…የህወሓት ቱማታ፤ የእነዐብይ ዝምታ!!
(ጫሊ በላይነህ)
ነገሬን በጥቂት ማሳሰቢያ ልጀምር። ከዚህ ቀደም ባቀረብኳቸው ሐተታዎች ላይ ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድን አንተ እያልኩኝ በመጥራቴ ቅር የተሰኛችሁ ወገኖች መኖራችሁን ሰማኹ። በእናንተ ቤት “አንቱ” ማለት አክብሮት፣ “አንተ” ማለት ደግሞ ንቀት ማድረጋችሁ ነው። ለማንኛውም እኔ ፈጣሪዬን ኢየሱስ ክርስቶስን እና ወላጅ አባቴን አንተ እያልኩኝ የምጠራው ስለምንቃቸው ሳይሆን ስለማከብራቸው፣ ስለምወዳቸው መሆኑን ካስታወስኩኝ ይበቃል፡፡
የነገሬ መነሻ የሰሞኑ የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ነው። የህወሓት ግትር አመራር አስቀድሞ የወሰነውን የአልዋሀድም ውሳኔ ጠቅላላ ጉባኤው ተቀብሎ መሀተም አሳርፎበታል። ጉባኤው ጥርስ ቢኖረው ኖሮ ሌላው ቢቀር “በኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ የተላለፈበት የውህደት ሀሳብ ለምን ልንቃወም ቻልን፣ ለምን ወደክህደት ተሸጋገርን?” ብሎ ወጥሮ ይጠይቅ ነበር። ግን አልጠየቀም። መድረኩ የተያዘው በሥጋ ዝምድና፣ በአምቻ ጋብቻ፣ በጎጥ በተሳሰሩ… የህወሓት ቁንጮዎች ነውና እንዲጠይቅም አይጠበቅም። የሆነው የሚጠበቀው ነገር ነው።
የህወሓት ማፈንገጥ በቅሎ ገመዷን ብትበጥስ ለራሷ አሳጠረች የሚለውን ተረት የሚያስታውስ ነው። በገዛ ውሣኔዋ በኮታ እና በጫና ካግበሰበሰችው የፌደራል መንግሥት ሥልጣን ጠቅልላ በቅርብ የመሰናበቷ ነገር የተበላ ዕቁብ ነው፡፡
ምናልባት የእነጠ/ሚ ዐብይ ሆድ ካልራራላቸው በስተቀር የአንዳንድ የህወሓት አባላትና ጀሌዎች ተባብረው የዘረፉት፣ ከገቢያቸው በላይ ያፈሩት ሐብት እየተለቀመ ወደሕግ መስመር መግባቱም በቅርብ የምናየው ነው፡፡ ሌላው ቢቀር እኛ ሰፈር የሚገኘው ቆሞ ቀሩ ባለቤት አልባ ሕንጻ ባለቤቱ ተፈልጎ ሒሳቡን እንዲያወራርድ መደረጉ አይቀሬ ነው፡፡ ከእያንዳንዱ አክስዮን፣ አትራፊ ቢዝነስ እና አትራፊ ውንብድና ጀርባ ያሉ አንዳንድ በሙስናና ብልሹ አሠራር የሚጠረጠሩ የህወሓት ባለሥልጣናትን የፌደራል መንግሥቱ ማሰር፣ ማሳደድ ሳያስፈልገው ማንነታቸውንና ሐጢያታቸውን ብቻ ለሕዝብ ይፋ ያደረገ ዕለት ህወሓትን ምስጥ እንደበላው እንጨት ባዶዋን ያስቀራታል፡፡
የሚገርመው፤ አንዳንድ የህወሓት ሰዎችንም በቁማቸው እያሸና ያለው የእነጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ ዝምታ ነው፡፡ መቼ ጠጠር ላበደረ ወርቅ ምላሽ እንደማይጠበቀው ሁሉ ህወሓቶችም ብዙ ለፍልፈው፣ ብዙ ስም አጥፍተው፣ ብዙ ዝተው… እቅፍ አበባ ከዐብይ ወገን እንደማይጠብቁ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይህም ሆኖ እነዐብይ ለዚህ ሁሉ የህወሓቶች ቱማታ መልሳቸው ዝምታ መሆኑ በራሱ ያማል፡፡ በህወሓት ጫማ ገብቶ ሲታሰብማ ያስፈራል፡፡ እናም መጪው ጊዜ ህወሓት በመንግሥት በጀት የፌዴራሊስት ሀይሎች..ገለመሌ እያለች የከሰሩ ፖለቲከኞችን በገንዘብና ጥቅማ ጥቅም የምትገዛበት፣ የፌስቡክ ሠራዊት ብላ ሁከት ቀስቃሾችን የምትቀልብበት ነባራዊ ሁኔታ መቀጠሉ የሚታሰብ አይደለም፡፡
ደግሞ ህወሓት ሆዬ ከፌዴራል ሓይሎች ጋር አብረን እንሰራለን በማለት የምትጎርረው ነገር አሪፍ ኮሜዲ ነው፡፡ ላለፉት ዓመታት በተለይ የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝቦች መራራ ትግል መልሶ ሕወሓትን መልሶ ለማንገስ አለመሆኑን ገና የገባት አልመሰለኝም፡፡ እንደጺላጦስ ራስዋን ከደሙ ንጹህ አድርጋ ስለሕግ የበላይነት፣ስለሕገመንግስት መከበር፣ ስለፌዴራሊዝም፣ ስለሕዝቦች ነጻነት፣ እኩልነት፣…ስትደሰኩር እንደመስማት የሚያዝናናኝ ነገር የለም፡፡
በመጨረሻው ሰዓት ህወሓት ትክክለኛ ቦታዋን መርጣ ይዛለች፡፡ ከገዥ ፓርቲነት ወደተቃዋሚነት በፍጥነት ወርዳለች፡፡ የእኔ ምኞት በሥልጣን ዘመኗ ስትናፍቀው የኖረችውን የታማኝ ተቃዋሚ ሚና በአግባቡ በመወጣት ለአገር ሠላምና መረጋጋት እንዲሁም ልማትና ብልጽግና የራሷን አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንድታበረክት ነው፡፡ ሌላው ሰይጣዊ መንገድ ለሁሉም የሚበጅ አይደለምና!
(የአዘጋጁ ማስታወሻ፡- ይህ ጹሑፍ የጸሐፊውን እንጂ የድሬቲዩብን ኤዲቶሪያል አቋም አያሳይም፡፡)