Connect with us

ህወሓት ራሱን ችሎ ከኢህአዴግ ጋር የጀመረውን እንዲጨርስ እንመክራለን – ጀዋር መሀመድ ለቢቢሲ

ህወሓት ራሱን ችሎ ከኢህአዴግ ጋር የጀመረውን እንዲጨርስ እንመክራለን - ጀዋር መሀመድ ለቢቢሲ
Photo: Facebook

ፓለቲካ

ህወሓት ራሱን ችሎ ከኢህአዴግ ጋር የጀመረውን እንዲጨርስ እንመክራለን – ጀዋር መሀመድ ለቢቢሲ

ህወሓት ራሱን ችሎ ከኢህአዴግ ጋር የጀመረውን እንዲጨርስ እንመክራለን – ጀዋር መሀመድ ለቢቢሲ

#BBC: የተለያዩ ፓርቲዎች አብረው ለመሥራት የሚያስችሏቸው እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው። አሁን አንተ ኦፌኮን ተቀላቅለሀል። ሕወሓት ከእናንተ ጋር አብሮ የመሥራት ጥያቄ ቢያቀረብ ትቀበላላችሁ?

ጀዋር፡ በሕወሓትና በእነ ዐብይ መካከል የተፈጠረው በአንድ ቤተሰብ ውስጥ፣ በአንድ ፓርቲ ውስጥ የተከሰተ ግጭት ነው። ይህ ግጭት እንግዲህ ሕወሓት በበላይነት ኢሕአዴግን ሲመራ የነበረ ነው። አብረው አገር ሲዘርፉ ሲጎዱና ሕዝብን ሲያሰቃዩ ነበር። አሁን ይኼ ለውጥ ምስቅልቅላቸውን አውጥቷቸዋል። በመካከላቸው ያለው ግጭት ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን የደህንነትም ጭምር ነው።

ከሁለቱ አንዱን በማቅረብ የዚህ ውስብስብ፣ ብዙ ቆሻሻ ያለበት ግጭት አካል መሆን አንፈልግም። ሕወሓትም ሕገ መንግስቱንና ሕጉን በጠበቀ መልኩ ክልሉን እንደሚያስተዳድር ፓርቲ መብትና ግዴታውን እንደሚወጣ እንጠብቃለን። የፌደራል መንግሥቱም ሆነ የፌደራል መንግሥቱን እየመሩ ያሉት የቀድሞ ኢሕአዴጎችም ግጭትን ባረገበ መልኩ ከሕወሓት ጋር አላስፈላጊ እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተው ትግራይንና የፌደራል መንግሥቱን አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ ከማስገባት እንዲቆጠቡ በተደጋጋሚ ስንመክር ነበር። አሁንም የምንመክረው እርሱኑ ነው።

ግን እንደኔ ግምትም ሆነ ምክር ሕወሓትን አሁን ወደ ተቃዋሚው በማምጣት በኢሕአዴግ መካከል የተፈጠረውን ግጭት ወደ ራሳችን መጋበዝ የለብንም።

ሕወሓትም ራሱን ችሎ ከኢሕአዴግ ጋር የጀመረውን፣ ከቀድሞ ባልደረቦቻቸው ጋር የጀመሩትን፣ በሰላማዊና ሕጋዊ መልኩ እንዲጨርሱ [ነው የምንመክረው]። [ቀሪው ነገር] ወደፊት በሂደት ምናልባት ከምርጫው በኋላ አሸንፈው የሚመጡ ከሆነ የሚታይ ይሆናል።

ከዚያ ወዲህ ግን የኢህአዴግን የበሰበሰና የተበለሻሸ፣ ብዙ ግለሰባዊ ሽኩቻዎች ያሉበት፣ የአገር ደህንነትን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ሽኩቻዎችና ግጭቶችን፣ ወደ ተቃዋሚው በማምጣት ተቃዋሚውን የዚያ ሰለባ ማድረግ ትክክል ነው ብዬ አላምንም። እኔ ያለሁበትም ሆነ ሌሎቹ ፓርቲዎች እዚህ ውስጥ አይሳተፉም።

#BBC: የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የመደመር ፍልስፍና እንደማያምኑ፣ የተቻኮለ መሆኑንም መግለጻቸውን ይታወሳል። በኋላ ደግሞ ተመልሰው አብረው ለመሥራት ተስማምተዋል። እንደዚህ አይነት ልዩነቶች ሲፈጠሩ ይህ የመጀመሪያው አይደለምና እነዚህ መንገራገጮች ያሰጉሀል?

#ጀዋር፡ ለማ መገርሳ የዚህ አገር ታላቅ ባለውለታ ነው። ይህ ትግል እየጦፈ በመጣ ወቅት፣ ሥርዓት ሳይፈርስ አገር ለአደጋ ሳይጋለጥ፣ በድርድር የሚካሄድ ሽግግር እንዲካሄድ፣ የእርሱ ቁርጠኛ አቋም፣ አመራር በጣም በጣም ወሳኝ ነበር። የአገራችን ከፍተኛ ባለውለታ ነው።

ያም ብቻ ሳይሆን ዐብይ አሕመድን ወደ ሥልጣን ያመጣው ራሱ ለማ ነው። ከዚያ በኋላ ዐብይንም አገርንም በከፍተኛ ትዕግሥት አገልግሏል። ልዩነቶች መፈጠር ከጀመሩ ቆይተዋል። ግለሰባዊ አይደሉም። ሽግግሩ የተመራበት አካሄድ ትክክል አይደለም የሚል አቋም ወስዷል። ይህንን በውስጥ የምናውቀው ነው። ሆኖም ግን ሁለቱ ካላቸው ከፍተኛ ሚና አንጻር ሽግግሩ ላይ የሚኖረውን አደጋ ለማ በደንብ አድርጎ የሚረዳ ሰው በመሆኑ የተነሳ ረዥም ጊዜ በውስጥ ብቻ በተወሰኑ ሰዎች መካከል ይዞት ነው የቆየው። መጨረሻ ላይም ተቃውሞ ውህደቱን በአቋም ማክሸፍ ይችል ነበር። ያን ማድረግ ሊያመጣ የሚችለውን ግጭትና አለመረጋጋት በመገንዘብ ውህደቱ ከተፈፀመ በኋላ አቋሙን ለሕዝብ ግልጽ አድርጓል።

ከዚያ በኋላም ነገሮች እየተባባሱ እንዳይሄዱ፣ በኦሮሚያ ውስጥ ሰፊ የሆነ በቢሮክራሲው ችግር መፈጠር ስለጀመረ ነገሮችን በውይይት እንፈታለን በሚል ነገሮችን ወደ መረጋጋት መመለስ ችሏል።

ከዚህ አንጻር ለማ አገርን ለአደጋ የሚያደርስ፣ ክልሉንም ፌዴሬሹኑንም ለአደጋ የሚጥል እርምጃ ይሠራል ብዬ አላምንም። ዐብይም ቢሆን ይህንን የሚረዳ ይመስለኛል። ወደፊትም እንግዲህ እየተወያየን፣ እየተረዳዳን ወደፊት የምንሄድ ነው የሚሆነው። ለማ ቀላል ሰው አይደለም።

አሁን ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊትም አገሪቱ ለምትወስደው እርምጃ ከፍተኛ ሚና የሚኖረው ሰው ነው። ከፍተኛ እውቀት፣ ተሰሚነት፣ ያለው ግለሰብ ነው። ወደፊትም ከተስማሙና ፓርቲውን ማሻሻል ሊያቀራርባቸው የሚችል ከሆነ በዚያ፣ ካልሆነ ግን ከተቃዋሚው ጋር በመሆን በግለሰብ ደረጃም ቢሆን ለአገር የሚጠቅም፣ ይህንን ሽግግር የሚያሳካ ሥራዎችን ይሠራል ብዬ ነው የማስበው።

ለማ እንግዲህ የፖለቲካ መሪ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ አዋቂና እንደአገር ሽማግሌም የሚያረጋጋ ሰው ነው። ወደፊትም ለማ ብዙ ነገር ይሠራል የሚል እምነት አለኝ።

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top