“የመጥፎ ምሳሌ በመሆኔ ይቅር በሉኝ…” ~ ፖፕ ፍራንሲስ
(ታምሩ ገዳ)
የሮማ የካቶሊክ ቤ/ክን ሀይማኖታዊ አባት የሆኑት ፖፕ ፍራንሲስ አዲሱ የፈረንጆቹ አመት ፣ኤእአ 2020ን አንዲት ምእመኒትን እና ተከታዬቻቸውን ይቅርታ በመጠየቅ ጀመሩት።
በአለም ላይ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ተከታዮች ያሏት ፣የሮማ ካቶሊክ ቤ/ን አባት የሆኑት ይቅርታ ለመጠየቅ ያ ስገደዳቸው ምክንያት ባለፈው ማክሰኞ እለት በሰማእቱ በቅዱስ ጴጥሮስ መታሰቢያ አደባባይ ላይ በተደረገ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የሰማኒያ ሶስት አመቱ አቡነ ፍራንሲስ ህጻናትን አቅፈው ሲስሙ፣የአካል ጉዳተኞችን፣አቅመ ደካሞችን ሲያጽናኑ እና ህዝበ ምእመናኖችን በአጠቃላይ ሲባርኩ ቆዩ ።
በብዙ መልካም ነገር ውስጥ ጉድፍ እንደማይጠፋው ሁሉ በብረት ከተከለለው አጥር ማዶ ቆመው የብጹነታቸው በአቅራቢያው ማለፍን ይጠባብቁ ከነበሩ ምእመናኖች መካከል አንዲቷ አቡነ ፍራንሲስ ሲቀርቧት የሰላምታ እጇን ትሰጣለች እርሳቸውም ሳይሰስቱ ይዘረጉላታል።ይሁን እንጂ በመጓዝ ላይ የነበሩት አዛውንቱ አርጀንቲናዊው ፖፑን ሲቲቱ ልታስኬዳቸው አልፈለገችም፣ በሀይል ጎተት ስታደርጋቸው ብስጭት ያሉት አቡነ ፍራንሲስም የቀኝ እጃቸውን ለማስለቀቅ ሲሉ በግራ እጃቸው “ልቀቂኝ ፣ልሂድበት… “አይነት የሴቲቲ እጅን መታ በማደርግ እጃቸውን አስለቅቀው ይጓዛሉ። ያቺ ቅጽበት በርካታ መገናኛ ብዙሃናት እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ማህበራዊ ድህረ ገ ጾች እንደ ጉድ ተቀባበሉት፣የመነጋገሪያ ርእስ ከፈተላቸው።
መጥፎ አጋጣሚ የአይምሮ እረፍት ያልሰጣቸው የሮማ ካቶሊክ ቤ/ቤን ዋና ሀላፊ የሆኑት አቡነ ፍራንሲስ እሮብ እለት በተባሄደው የአዲሱ አመት ክብረ በአል ላይ ባሰሙት ንግግር” እኔን ጨምሮ ብዙዎቻችን ለብዙ ጊዜ ስሜታችንን መግራትእና መቆጣጠር ይሳነናል። በትላንትናው እለት ላደረግኩት የመጥፎ ነገር ተምሳሌትነት ይቅር ትሉኝ ዘንድ እማጸናለሁ። ሲሉ ተደምጠዋል።
በምእመኒቷ እና በብጹነታቸው መካከል ተፈጥሮ የነበረው ያ “ትእግስት አልባ ድርጊት” ብዙዎቹን ዛሬ ድረስ ” እውን ሴቲቱ የወሰደችው እርምጃ ትክክል ነበር?፣ በጉተታው ሳቢያ ተደናቅፈው እንዳይቀሩ ሲሉ ቁጣ እና ጥፊ የተቀላቀለበት እርምጃን የወሰዱት ፣ብዙዎች በትህትናቸው የሚያውቋቸው ፖፕ ፍራንሲስ ምላሽስ ተገቢ ነበር?፣ ይቅርታ መጠየቅ ያለበት በቅድሚያ ጉተታ ያደረገችው ምእመኒቷ? ወይስ በደረሰባቸው ጉተታ ሳቢያ “ተገቢ ላልሆነው ድርጊት” የተገፋፉት አቡነ ፍራንሲስ?፣የጸጥታ ኃይሎች ሚናስ እስከ ምን ድረስ መሆን ነበረበት ?ወዘተ…ሱሉ ዛሬ ድረስ እየተወያዩበት ይገኛል።
የሰው ልጆችን ከሐጢያት ባርነት ነጻ ያወጣ ዘንድ ከነበረው ዘለኣለማዊ ክብሩ ዝቅ በማለት እኤእ የዛሬ 2020 በከብቶች ግርግም ውስጥ የተወለደው ጌታ እየሱስ ክርስቶስ የፍቅር እና የትህትና ምሳሌ መሆኑን ያወሱት አቡነ ፍራንሲስ”በእዚህ አለም በተለያዩ የስልጣን እና የክብር ኮርቻ ላይ ተፈናጠን የምንገኝ ወንድሞች እና እህቶች ሆይ እስቲ ዝቅ ብሎ ታላቅ ክብርን እንዴት ማግኘት እንደሚቻል ከጌታ ከእየሱስ ክርስቶስ እናት ፣ከድንግል ማርያም እንማር።የሰው ልጆች ጠላት የሆነው ዲያብሎስ በፖለቲካ፣በአመለካከት እና በፓርቲ ሽፋን አንድነታችንን እና ሕብረታችንን ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ እየተፈታተነው ይገኛል።” በማለት ዘመኑ በመንፈሳዊው ሆነ በአለማዊው የሰው ልጆች ህይወት ውስጥ እጅግ አስከፊ መሆኑን አስገንዝበዋል።