የቱሪዝም ፋይናንስ ቦርድ ይቋቋም !
(በአሥራት በጋሻው)
ቱሪዝም በመንግሥት አይንቀሳቀስም። መንግስት ሕግና ደንብ ሊያወጣ ሕግና ደንብ ሊያስከብር ይችላል። ፈጻሚዎች ግለሰቦች እና ግለሰቦች የመሠረቱት ተቋማት ናቸው። ቱሪስቶች ስጋና ደም ያላቸው ሰዎች እንጂ ግዑዛን አይደሉም። እንዚህን የሚያናግሩ የሚያነሳሱት እራሳቸው ሰዎች ናቸው።
መንግስት የማስተባበሩን የመምራትና የመከታተልን ስራ ይሰራል እንጂ በቱሪዝም ውስጥ ዋንኛ ተዋንያን ግለሰቦች እና ድርጅቶቻቸው ናቸው።መንግሥትና ተቋማት በልማት
በማርኬቲንግ እገዛ ማድረግ እንጂ ፈጻሚዎቹ የቱሪዝም ባለሙያዎች ናቸው።
የቱሪዝም ፋይናንስ ቦርድ ስራ መንግስት በግብርም ሆነ በድጋፍ የሚያገኘውን ገንዘብ በቀጥታ በቦርድ በኩል ለዚሁ አገልግሎት እንዲውል ያደርጋል ።
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ለቱሪዝም እድገት የሚጣጣሩ ብዙ ሀሳብ ያሏቸው ግለሰቦች አሉ ።
ግለሰቦቹ እና እነሱ በጋራም ሆነ በግላቸው ባቋቋሙት ተቋም አማካኝነት የተለያየ እቅድ ነድፈው ይለፋሉ ። ሥራቸዉ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ብዙም አይራመድም ወይም በአቅማቸው ልክ አይሰሩም አያድጉም።
በፊልም :በሙዚቃ በቲያትር በስእል በመገናኛ ብዙሐን በፕሮሞሽን ጋይድ የሚያዘጋጁ በኤግዚቢሽን በኢቨንት ኦርጋናይዚንግ በሆስፒታሊቲ በጉዞ ዘገባ በትራቭል ማኔጀመንት ዲጅታል ቴክኖሎጂ : ጥናት እና ምርምር እንዲሁም በቱር ኦፕሬሽን ሥራ እና በመሳሰሉት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ቱሪዝምን ለማሳደግ ለማስተዋወቅ እና የቱሪዝም ሐብቶች እንዲጠበቁ ያሥተምራሉ።የእስከዛሬው ድካም ውጤት አጥጋቢ አይደለም ።ልፋታቸው አልታየላቸውም።
ይህንን ጥረታቸው የሚደግፍ የቱሪዝም ፋይናንስ ቦርድ መቋቋም ጠቃሚ ነው።
የቦርዱ አባላት በየዘርፋ ልምድና እውቀት ያላቸው እና መንግስት በጀቱን በትክክል ያስተዳድሩልኛል የሚላቸውን ግለሰቦች ይሰይማል ።
መንግስት አመታዊ በጀት ይመድባል ።
የአመቱን በጀት ተከትሎ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ፕሮፖዛላቸውን ያቀርባሉ። ቦርዱ ተወዳዳሪዎች ያቀረቡትን ፕሮፖዛል በራሱ መለኪያዎች ይመርጣል።የፋይናንስ ድጋፍ ያደርጋል። ገንዘቡ በአግባቡና በጥራት ጥቅም ላይ እንደዋለ ይቆጣጠራል ።ያመጣውን ለውጥ ይገመግማል። ሚዲያዎቻችን ከስፖርት ባለፈ እንዲሰሩ ይረዳል። የሥራ ፈጠራን በማበረታት ያግዛል። ቱሪዝማችን ያድጋል። በየክልሉ ያሉ የቱሪዝም ሀብቶቻችን ተመልካች ያገኛሉ።ባህላችንን ያዳብራል ።
መንግስት ሆይ ስማ ! ከመንግሥት ጋር ተነጋግሮ የመጣ ቱሪስት የለም።
ቱሪዝም የመንግስት ሥራ አይደለም ። መግስት ሠላም ህግ ያስከብርልን ።የጸጥታ ጥበቃ ያድርግልን።
ሀሳቤን በግል ለዪንዲፒ እና የወርልድ ባንክ ሰዎች አቅርቤ ፎርማል ሆኖ ከመጣ መንግስትን ለማገዝ ፍቃደኛ ናቸው።
መንግስት ሆይ ስማ !የቱሪዝም ፋይናንስ ቦርድ ይቋቋም ።