Connect with us

ቤተ እምነቶቻችንን ግብር የምንከፍለው መንግስት የመጠበቅ አጥፊዎቹንም የመቅጣት ግዴታ አለበት

ቤተ እምነቶቻችንን ግብር የምንከፍለው መንግስት የመጠበቅ አጥፊዎቹንም የመቅጣት ግዴታ አለበት
Photo: Facebook

ህግና ስርዓት

ቤተ እምነቶቻችንን ግብር የምንከፍለው መንግስት የመጠበቅ አጥፊዎቹንም የመቅጣት ግዴታ አለበት

ቤተ እምነቶቻችንን ግብር የምንከፍለው መንግስት የመጠበቅ አጥፊዎቹንም የመቅጣት ግዴታ አለበት፡፡
በእምነት ስም ተነስቶ መድረሻን እከሌ ከቤተ መንግስት ይውጣ ማድረግ ያስተዛዝባል፡፡
****
ከሰለሞን ሃይሉ
ምንም ማመንታት አያስፈልግም የቱንም ቤተ እምነት የሚያቃጥለው አካል የኢትዮጵያ ጠላት ነው፡፡ ቤተ እምነት አንድዶ መሞቅ የሚፈልግ ክፉ ከየትኛውም ወገን ቢሆን አውሬነቱን አምነን መቀበል ይኖርብናል፡፡ በኢትዮጵያ በየትኛውም የታሪክ ምዕራፍ ህዝብ በህዝብ እምነት ላይ ተነስቶ አንዱ የሌላው ጠላት የሆነበት ምዕራፍ የለም፡፡ ያልተማሩት አባቶቻችን ሃይማኖት የግል ነው ብለው ኖረዋል፡፡ ነገስታቱና ኢማሞቹ ብዙ ቢያስቡም የትም ያልደረሰ ምኞት ነበር፡፡

ዛሬ የተማረው በሚቀሰቅሰው ዳፋ ሀገር ሰላም ውላ ማደር አቅቷታል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ቤንዚል ይዞ የሚኖር እስኪመስል ችግሩ ብልጭ ሲል እስኪንቦገቦግ ያቀጣጥለዋል፡፡ ክፋት እንደ ሀገር በኢትዮጵያ ነግሷል፡፡ የኔ ወገን አጥፊ ሊባል ነው ያለ ምን ወንጀል ቢሰራ ወይ ዝምታን ይመርጣል፤ ዓይን አውጣ ከሆነ ደግሞ ምክንያትን ይደረድራል፡፡ ሌላው ወገን እንዲህ አደረገ ብሎ የጥቂቶችን እኩይ ጠባይ ለህዝብ የሚሰጥ ውስጠ መርዝም ብዙ ነው፡፡

የሞጣውን ድርጊት በተከታታይ በሀገራችን ሲፈጸሙ ከቆዩት የቤተ ክርስቲያናትና የመስጂድ ቃጠሎች ለይተን መመልከት የለብንም፡፡ አጀንዳው እንደ ትናንቱ በእምነቱ የተቀራረበውና መንፈሳዊነት የገራውን ህዝብ ወደ ስሜታዊነት ነድቶ በብሔር የተሞከረውን የማጫረስ አጀንዳ ወደ እምነት ለመቀየር የሚደረግ ሙከራ ነው፡፡

ይሄንን አለመረዳችን አንዱ ችግር ነው፡፡ ተቆርቋሪ መስለው በሰው ህይወት የሚነግዱ አረመኔዎችን ማድመጣችን ደግሞ ሌላው መከራ ነው፡፡ እንዴት ችግሩን እንቅረፍ ብለን ተመካከርን አናውቅም፡፡ መከራችንን ባለቤት አንፈልግለትም፡፡ አጋጣሚው መጥፎ ሆኖ ለመወቃቀስ እንደ ወረደ መና እንቆጥረዋለን፡፡ ገና ችግሩ ሳይቆም ጣት የመቀሳሰሩ ስካር ይናኛል፡፡

መንግስት ቤተ እምነቶችን ማስከበር አለበት፡፡ ግብር ከፍለን መንግስት የምናኖረው በዋናነት እንዲህ ላለው እሴታችን ጥበቃ እንዲያደርግልን ነው፡፡ የህግ የበላይነት እንጂ በየተራ መጠፋፋት አልያም ያንተ ጉዳት ከእኔ ይብሳል መባባል፤ ወይም ለጠፋው አጥፍቶ ማካካስን ማሰብ እብደት ነው፡፡ ሰው ከዚህ የሚያልፍ ክቡር ፍጡር ነው፡፡ እንደ ሰው ካሰብን መፍትሔው ህግ የሚከበርባት፣ አጥፊ ወገን አልባ የሚሆንበትና ለህግ የሚቀርብበት አሰራር እንዲፈጠር ከስልጣኔ ጎን መቆም አለብን፡፡

ከዚያ ውጪ እንዲህ ያለውን ችግራችንን ከስሩ መንቀል ሲገባን እከሌ ከቤተ መንግስት ይውጣ፣ እከሌ አክራሪ ነው እያልን ስለ ሁለት ሰዎች ሚሊዮኖች ወገን ለይተን ስንጨቃጨቅ ብንውል እንደ እንስሳ መንጋ ሆነን ወደ ጥፋት ከማምራት በስተቀር እንደ ሰው ችግራችንን መፍታት አንችልም፡፡

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top