ዲላ-ተፈጥሮ የሞሸረቻት አረንጓዴዋ መዲና
የውበት ሀገሯ እዚህ ነው፡፡
****
ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ከጌዲኦዎች ጋር ነው፡፡ የዲላ የተፈጥሮ ውበትና አረንጓዴ ቀለም ከሀገሬ ከተሞች ለመኖሪያ ምቹ በመሆን ተስፋ የማደርገው ጸጋ ነው ይለናል በተከታዩ ዘገባው፡፡
ከሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ
ሸለቆ ውስጥ የተዘረጋው ደን ውስጡ ሸጋ ከተማ ይዟል ቢባል ማን ያምናል? እዚህ ደን ውስጥ ዲላ አለች፡፡ ዲላ የጌዲኦ መዲናው ናት፡፡ ጎዳናዎቿ ለጋስ ናቸው፤ ተፈጥሮ በእጽዋት ማዕዛ የከተማዋን ጠረን ከነፍስ የምታስማማበት ምድር ነው፡፡
ከአዲስ አበባ ኬኒያ ናይሮቢ የሚዘልቀው መንገድ ልቡ ቀጥ የምትለው ዲላ ደርሶ እንዲህ ከተፈጥሮ ሲገናኝ፣ እንዲህ ከአረንጓዴ ምድር ሲታረቅ ነው፡፡ እንዲህ ባለ ከተማ መኖር መታደል ነው፡፡ እንዲህ ያለው የተፈጥሮ ቀለም ለዓይን ውበት ብቻ አይደለም ለትውልድ ጤናም እንጂ፤
በዚህ አረንጓዴ ቀለም ደስ ብሎኛል፡፡ በእኔ ሀገር ዛፍ ቆርጦ የመስታወት ሳጥን ማቆም መዘመን ነው፡፡ አየር በእርዳታ ይመጣ ይመስል ከተፈጥሮ ጋር መጣላት የከተሞቻችን የዚህ ዘመን ጠባይ ሆኗል፤ ዲላ ከዚህ ተፈውሳለች፤ ዲላ እንዲህ ያለውን ጥሩ ያልሆነ ባህል በመልካሙ የአረንጓዴ ልማቷ ድል ያደረገች ውብ ከተማ ናት፡፡
ከባህር ጠለል በላይ 1570 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ የገበያ ከተማ፤ ቀኑን ሙሉ ትርምስ ነው፡፡ ምድሯ ቸር ስለሆነ ገበያዋ የለም የለበትም፡፡ ፍራፍሬ መገለጫዋ ነው፡፡ ዲላ በፍራፍሬ ድንቡሽ ያለች የከተማ ሎጋ ናት፤ ከተማ ሎጋ አለው ብሎ መጠየቅ ሞኝነት ነው፤
ጌዲኦ ደን አጥሮ የሚኖር አይደለም፡፡ ራሱን ከተፈጥሮ አቆራኝቶ፣ በባህላዊ እውቀቱ ደኑ ውስጥ ዓለሙን እየቀጨ ከተፈጥሮ ሳይጣላ፤ ከፈጣሪውን ታርቆ የሚኖር ህዝብ ነው፡፡ የዚህ ማሳያው መዲናው ናት፡፡ መዲናውን አረንጓዴ ቀሚስ አልብሶ በዛፎች ጥላ ስር የሚንሸራሸር ህዝብ መካከል ነኝ፡፡ እንዲሁ አልመለስም፤ ስለ አስገራሚዎቹ ትክል ድንጋዮች እነግራችኋለሁ፡፡ አብረንም እንሄዳለን፡፡ ስሟ ዓለም ምላስ የቀረችውን ይርጋ ጨፌ እንዴት ነሽ ብለናት እንመጣለን፡፡
ማታ ሸጋ እራት በላሁ፡፡ የጌዲኦ ምግብ ቤቶች ቦለቄን ድንቅ ሾርባ ይሰሩታል፡፡ ከስጋ የሚተካከል ጣፋጭ ሾርባ ነው፡፡ የቦለቄ ሾርባ የምትጋበዙበት ከተማ ይዣችሁ መጥቻለሁ፡፡ አሁን ወደ ቱቱፈላ ልሄድ ነው፡፡ ከዚያ ውሎዬን ትውሉታላችሁ፡፡