Connect with us

ኑ!…ኢህአዴግን ነፍስ ይማር እንበለው?!

ኑ!...ኢህአዴግን ነፍስ ይማር እንበለው?!
Photo: Facebook

ባህልና ታሪክ

ኑ!…ኢህአዴግን ነፍስ ይማር እንበለው?!

ኑ!…ኢህአዴግን ነፍስ ይማር እንበለው?!
(ጫሊ በላይነህ)

የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውህደት አብዮታዊ ዴሞክራቱን ኢህአዴግ አሳጣን። በብሶት ተወልዶ፣ በብሶት ያኖረንን ገዥ ነጠቀን።
አራቱ ፓርቲዎች በሰሞኑ የውህደት ውሳኔያቸው ኢህአዴግን ወደመቃብር ገፉ። ስልጣን በያዘ በ29 ዓመቱ ሩጫውን ጨረሰ።  ኖሮ ኖሮ በወጣትነት አፍላ ዕድሜው ተቀጨ። ወግ ነውና ነፍስ ይማርልን!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ እንዲህ አሉን። “በሦስቱ ቀናት ስብሰባችን ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች አጽድቀናል። የመጀመሪያው በጥልቅ ተወያይተን ያጸደቅነዉ የፓርቲውን ውሕደት፤ አሳታፊነትና አካታችነት ነው። ሁለተኛው ሁሉንም ማኅበረሰብ ወደፊት የሚያራምደውን የፓርቲዉን ፕሮግራም ሲሆን ሦስተኛው ሕገ ደንቡን ነው። የሦስቱም ቀናት ውይይታችን ግልጽና ደሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ተካሂዷል። ውይይቱ ይበልጥ አመራሮቹን ያቀራረበ ሆኖ በመጠናቀቁ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል።”

እንግዲህ ጠቅላያችን ጎምቱውን ኢህአዴግ ማሰናበታቸውን በገደምዳሜ ነግረውናል። አዲሱ ውሁድ ፓርቲ መወለዱን አብስረውናል። እዚህ ላይ ነው እንግዲህ በኢህአዴግ ሞት ያዘኑትን ሁሉ ነፍስ ይማር ብለን እዝን ልንደርስ፣ ልናፅናና የሚገባው።

እስቲ አስበው!… እንደኢህአዴግ የሚያሳዝን ፓርቲ በዓለም ላይ ያለ ይመስልሀል?…በጭራሽ የለም። ሁለት አስርተ አመታት ገደማ ለብሄር ብሄረሰብ መብት ታገልኩ እያለ እየነገረህ ግን ራሱ አዲስ፣ ተረኛ ጨቋኝ ሆኖ በአይንህ በብረቱ አይተኸዋል።

ለዴሞክራሲ፣ ለህዝቦች እኩልነት ስሞት ነበር እንዳላለህ የአንድ ብሄር የበላይነት አንግሶብህ ዴሞክራሲ…ዴሞክራሲ መጫወት ሲያምረው ታዝበሀል። ሀሳብን በነፃ የመግለፅ ነፃነት የተከበረ ነው ብሎህ ሀሳባቸውን የገለፁትን በጠላትነት ፈርጆ ሰዶ ሲያሳድድ ደንግጠሀል።

ሰብአዊ መብት ክቡር ነው እያለህ ጠላቴ ያላቸውን እያደነ በማሰር ወፌ ላላ ሲገርፍ፣ ሲደበድብ፣ ሲገድል፣ አካል ሲያጎድል ስለመኖሩ ታምኖ የማታ ማታ ይቅርታ ተጠይቀሀል። የፀረ ሙስና ኮምሽን አቋቁሞ፣ የባለስልጣናት ሀብት ይመዝገብ ማለቱን ሳትረሳ፤ በሌብነት አባብጦ፣ ሊፈነዳ ደርሶ ስታገኘው ግራ ትጋባለህ።

አስር ሺ ብር ባልሞላ ደመወዝ ባለሚልየን ብር መኪና፣ ባለቪላ፣ ባለህንፃ እየሆነ… ለአንተና ለእኔ ግን “ልማቱ አብቧል…” እያለ ማቀንቀኑን ታዝበሀል። የመሰብሰብ፣ የመደራጀት ነፃነት ህገመንግስታዊ መብት ነው ይልኸና በተግባር ስትጠይቀው የማርያም መቀነት አደናቀፈኝን እያለ ስንቱን ሲፈጀው ተገርመሀል።

በእውነቱ ኢህአዴግ ነፍሴ!… እንዲሁ ለጥቂት ሰዎቹ ምቾትና የበዛ ድሎት ሲለፋ…ላቡን ሲዘራ… ኖሮ ኖሮ አረፈ ማለቱ ይቀላል። መቼም ወግ ነውና ነፍስ ይማር እንበለው?!

ምስኪኑ…ጭቁኑ ሰፊው የኢትዮጽያ ህዝብ!… ይኸ ሁሉ መከራ ሲወርድበት አይቶ እንዳላየ በማለፍ አመታትን ታግሷል። ግን ኢህአዴግ ይኸ የበዛ የህዝብ ትግእስት ልቡን አላራራውም። እንዲያውም በተቃራኒው በትእቢት ወጠረው። “ችግሬ የመልካም አስተዳደር ነው፣ የአፈፃፀም ነው..” የሚለውን ነጠላ ዜማ ጠዋት ማታ እያሰማ ከህዝብ በተቃራኒ መንጎድ ሥራው ሆነ።

ታጋሹ ህዝብ በመጨረሻ አመረረ። “በቃህ…ከትከሻዬ ውረድ” ብሎም ገፋው። ከአራት ዓመት በፊት “መቶ በመቶ በህዝብ ተመረጥኩኝ” ብሎ ባቅራራበት ማግስት ህዝባዊ ማእበል ያናውጠው ያዘ። ኢህአዴግ ከውስጥም ከውጪም ተፈረካክሶ መቃብር አፋፍ ላይ ለመቆም ጊዜ አልወሰደም። በተግባር የበሰበሰ ቡድንን ለመጣል በጥቂቱ ገፋ ማድረግ በቂ ነበር።

ሁኔታው የገባቸው ጥቂት የለውጥ ሀይሎች ፈጥነው ነቁ። ከውስጡ ተወልደው ጥፋቶችን በቶሎ ማረም ባይችሉ ኖሮ ይሄኔ የኢህአዴግ አሟሟቱም ከዚህም በላይ በከፋ ነበር።

እነሆ!… የለውጥ ባቡሩ ሄዶ ሄዶ በኢህአዴግ መቃብር ላይ ህብረብሄራዊ ፌደራሊዝምን ለመወለድ በቃ። የአክራሪ ብሔርተኞች ወላጅ አባት የሆነው ኢህአዴግ ከእነአብዮታዊ ዴሞክራሲው ወደመቃብር ተሸኘ። ጥቂቶች ጥቅማቸውን እያሰቡ በኩርፊያ ቢሸሹም እውነተኛውን ለውጥ ግን መቀልበስ አልቻሉም።

እነሆ የኢህአዴግ የለውጥ ውላጅ የሆነው “የብልፅግና ፓርቲ” ተወልዶ ግቤ ብልፅግና ነው ብሏል። እንግዲህ ብልፅግናን ማን ይጠላል?!.. እነሆ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ ብለናል።

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top