Connect with us

ተመስገን ጥሩነህና ሽመልስ አብዲሳ-ማዶ ለማዶ

ተመስገን ጥሩነህና ሽመልስ አብዲሳ-ማዶ ለማዶ
Photo: Facebook

ፓለቲካ

ተመስገን ጥሩነህና ሽመልስ አብዲሳ-ማዶ ለማዶ

ተመስገን ጥሩነህና ሽመልስ አብዲሳ-ማዶ ለማዶ

(በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን)

እነዚህ ሁለት መሪዎች በዚህ እያገባበደድነው ባለነው ሳምንት የተናገሩት ነገር ትኩረት የሚስብ ነው፡፡ የአማራ ክልል ርዕሰመሥተዳድር ተመስገን በክልሉ ምክር ቤት፣ የኦሮሚያው ሽመልስ ደግሞ በክልላቸው ቴሌቭዥን ተናግረዋል፡፡

በአቶ ተመስገን እንጀምር!

‹‹ለውጡን አመጡ የሚበሉ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ በስም አንዳንድ ጊዜ በፎቶ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በቁጥር እነ እከሌ ናቸው ተብሎ መወሰዱ በራሱ ምስቅልቅል ውስጥ ከትቶናል፡፡ የዛኔ ነው ሕግ የሚባለው፣መንግሥት የሚባለው፣ሥርዓት የሚባለው፣የፈረሰው፡፡

2010! ምክንያቱም አንድ ፌደራል ላይ ያለ ሰው፤ ክልል ላይ ያለ ሰው በፍፁም ሕዝብ ሊያስተዳድር አይችልም፡፡የሕዝብ አስተዳዳሪ መሠረቱ ቀበሌ ነው፤ ወረዳ ነው፡፡ ስለዚህ ወረዳንና ቀበሌን አፍርሰን ሕግና ሥርዓት አለ ማለት አንችልም፡፡ ያፈረስነው ደግሞ ያን ጊዜ ነው፡፡ አሁን እያደረግን ያለነው ወረዳንና ቀበሌን መጠገን ነው፡፡ ሌባና ሽፍታ አንቀው የሚያስሩ፣ አርሶ አደር እየገደሉ የሚሸፍቱ ሽፍቶች፣ሌቦች ቀማኞችን አንቀው ያስሩ የነበሩ የወረዳ አመራሮች እኮ ዛሬ ቤታቸው ተቃጥሏል፡፡ በምህረት በወጣ ሌባ!…ግን ደግሞ እኔ ነኝ የነፃነት ታጋይ ብሎ ደረቱን ገልብጦ ሲሄድ አያፍርም፡፡ካልተወሻሸን በስተቀር ሕዝቡ የነፃነት ታጋይ እንዳልሆነ ያውቃል፡፡ግን ይገድለናል ብለን ሁላችንም ፈሪዎች ሆነናል፤የነጋዴን እህል ዘርፎ ሲከፋፈል፣ሲቀማ ዝም ብለናል›› ብለዋል፡፡

በርግጥ አቶ ተመስገን በዚህ አቋማቸው ትክክለኛው መንገድ ላይ ይመስላሉ፡፡ለአንድ ፖለቲካዊ ችግር ዋነኛው መፍትሔ በቅድሚያ እራስን መመልከት ነው፡፡እኔ ለዚህ ችግር ምን ያህል ሚና አለኝ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡አሁን አገሪቱ ላይ ያለው ውጥንቅጥ በለውጡ ሰሞን ለውጥ አምጪ ተብለው በስም ሲጠቀሱ የነበሩት አንድ አምስት ሰዎች እንጂ ተቋም አለመሆኑ እንደሆነ አቶ ተመስገን ተረድተውታል፡፡ልክ ናቸው፡፡ከዓመታት በፊት ቅሬታና አመጽ ያስነሱ ጉዳዮች የሚንፀባረቁት በወረዳና ቀበሌ ባሉ መዋቅሮች እንጂ በቤተመንግሥቱና በፌደራሉ ላይ አይደለም፡፡ የመንግሥት አገልጋይነት ዋነኛ ሥራ ያለው በፌደራሉ ተቋም ላይ ሳይሆን በክልላዊ አስተዳደሩ ላይ ነው፡፡ይህንን ልብ ያላለው የዚያ ሰሞን ፖለቲካዊ ማዕበል ግን ትኩረቱን በኢሕአዴግ ቤት ውስጥ በነበሩ አንድ አምስት ሰዎች ላይ አደረገ፡፡አቶ ተመስገን እንዳሉት ግን እነዚህ ሰዎች የወረዳና የቀበሌን ችግር የሚፈቱ አልነበሩም፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ቀጥለውም እንዲህ አሉ

‹‹አዴፓ ውስጥ እኮ ቀን አብሮ ሲሰራ ውሎ ማታ ሴራ ሲጎንጉን የሚያመሽ ሰው አለ፡፡ወይም ደግሞ በቴሌቭዥን መስኮት ወጥቶ፣‹ወያኔ ሌባ› ብሎ በፌስቡክም ጀግና ተብሎ፣ሥራ ላይ ግን የፈሰሰ ውሃ የማያቀና አለ፡፡እንዴት አድርገን ነው አንድ የምንሆነው›› እዚህ ጋር ግራ የገባቸው ይመስላሉ፡፡ፈጣሪያቸውና ወዳጆቻቸው እንዲረዷቸው መመኘት መልካም ነው፡፡

ተመስገን ጥሩነህና ሽመልስ አብዲሳ-ማዶ ለማዶ

ሽመልስ አብዲሳ

አቶ ሽመልስ የዛሬ ወር አካባቢ የተናገሩት ንግግር ብዙ አቧራ አስነስቶ ነበር፡፡‹ሰባበርናቸው› የሚለው የዚያ ሰሞን የአደባባይ ድስኩራቸው በርግጥም አነጋጋሪ ነበር፡፡አሁን ደግሞ ሌላ አወዛጋቢ አጀንዳ መዝዘዋል፡፡አቶ ሽመልስ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ዋነኛ ሥራቸው ለክልሉ ሠላም፣ለወጣቱ ሥራ ያመጣሉ ተብሎ ነበር፡፡ይሁን እንጂ ይህንን ማድረግ አለመቻላቸው ሳያንስ ተጠራጣሪ ሕዝብ እንዲፈጠር፣ኦሮሞንና ሌላውን እንዲራራቅ የሚያደርግ ንግግር እየተናገሩ ቀጥለዋል፡፡

ትናንት ማታ በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ቆይታ የነበራቸው እኒህ ርዕሰመስተዳድር፣ስለ ክልሉ ሠላምና ልማት አንዲት ቃል አልተነፈሱም፡፡መንግሥትን በትጥቅ የሚፋለም ቡድን ያለበትን ክልል እየመሩ መሆናቸውን እንኳ እረስተውታል፡፡አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከሚያስተዳድሩት ኦሮሚያ ውስጥ ሰባቱን ዞኖች መከላከያ ነው የሚያስተዳድርላቸው፤በየቀኑ ሰው እየሞተ ያለው ኦሮሚያ ነው፡፡የአንገት ማተብ (የኦርቶዶክሶች መለያ) እየተወለቀ ምዕመን በኃይል ሌላ ሃይማኖት እንዲቀበል ተሰብስቦ እየተገደደ ያለው ኦሮሚያ ነው፡፡አቶ ሽመልስ ሰው በማንነቱ እየተቀጠቀጠ የሚገደልበትን ክልል እየመሩ ቢሆንም እርሳቸው አሁንም ሌላ ከፋፋይ ንግግር ይዘው መጡ፡፡

የአቶ ሽመልስ ንግግር ልምድ አልባ ፖለቲከኛ መሆናቸውን ያሳዩበት ነው፡፡‹‹ከዚህ በኋላ ሥራችን ፖለቲካዊ ሥልጣንን እና ሥርዓትን ከሰሜን (ከአማራና ትግራይ) ነጥቀን ወደ ደቡብ ማምጣት ነው›› ብለዋል፡፡ስለ መደመርና የኢሕአዴግ ውሕደት ለማውራትና የኦሮሞን ሕዝብ ለማሳመን እንዲህ ያለ ሤራ ጉንጎና ውስጥ መግባት አይጠበቅባቸውም ነበር፡፡ ፖለቲካ የአመክንዮ ጉዳይ እንጂ የሰሜንና የደቡብ ጉዳይ አይደለም፡፡ካርል ማርክስ በአንዲት ቤት ውስጥ ተቀምጦ የፃፋት የፖለቲካ ሃልዮት የትመጣነቷ ሳይታይ ዓለምን በሙሉ አዳርሳለች፡፡ስለዚህ የኢሕአዴግ ውሕደት ዋነኛ ግቡ ፖለቲካን ከሰሜን ወደ ደቡብ (ወደ ኦሮሚያ) ለማምጣት ከሆነ አስገራሚ ነው የሚሆነው፡፡አቶ ሽመልስ ግን ይህንን ተናግረዋል፡፡

‹ሁለቱ ዘመዳሞች› አያሉ የሚጠሯቸው አማራና ትግራይ የዚህ አገር የፖለቲካ ሥርዓት ያነበሩ መሆናቸውን በመውቀስ ‹ተገቢ አይደለም‹ ብለዋል፡፡

አቶ ሽመልስ ንግግራቸውን ሲቀጥሉ ‹‹ወደደንም ጠላንም የዚህ አገር ፖለቲካ እና ሥርዓ የሰሜኑ ነው፡፡ይሄንን ወደ ደቡብ እናመጣለን›› በማለት አጽንኦት ሰጡበት፡፡እነ አቶ ሽመልስ አካታች ያልሆነ ፖለቲካ ይዘው እንደመጡ ይህ ጥሩ አስረጂ ይመስለኛል፡፡ከወራት በፊት ‹ሰብረነዋል፤ሰባብረነዋል›› ብለው ከፋፋይ ንግግራቸውን ያሰሙት አቶ ሽመልስ፣ዛሬ ደግሞ በሰሜን ኢትዮጵያ ላይ ሌላ የሰነፍና ተራ ፖለቲከኛ ካራ መዝዘዋል፡፡

ቀጥለው መደመር ለምን እንደ ኢሕአዴግ መዋኸጃ ርዕዮት እንደተወሰደ ሲጠየቁ፣ ቢያንስ አሳማኝ የፖለቲካ ትንታኔ ይሰጣሉ ተብሎ ሲጠበቅ፣ ‹‹በቃ ሰለቸን›› ብለው አረፉት፡፡ከሁሉም ደግሞ በዕውቋ ኢኮኖሚስት ኢለኒ ገ/መድህን የተቋቋመውን ኢሶኤክስ ‹የኦሮሞን አርሶ አደር ለመጉዳት የተመሠረተ› ብለው ማውገዛቸው ነው፡፡ኢሲኤክስ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ጩልሌ ነጋዴዎች የኦሮሞን ቡናና የጥራጥሬ ምርት በአየር ላይ እየተቀበሉ የክልሉን ገበሬ (ሌላውንም ጭምር) ሲያስቸግሩት እጅግ በተጠና መንገድ የተመሠረተ ተቋም ነው፡፡ለዚያውም በዓለማቀፍ ኢኮኖሚስት፡፡የእነ አቶ ሽመልስ ቁጭት ምናልባት ‹እኛም ከዝርፊያው ሳይደርሰን ኢሲኤክስ እንቅፋት ሆነብን› የሚል ከሆነ በግልጽ መናገር ነው፡፡

አቶ ሽመልስ እዚህ ግባ የሚባል የፖለቲካም ሆነ የአስተዳደር ልምድ እንደሌላቸው በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ሰኔ 15/2011 ባለሥልጣናት መገደላቸው እንደተሰማ በቴሌቭዥን መጥተው ‹እርምጃ እንወስዳለን፤አንላቀቅም› ወዘተ ሲሉ ‹እኒህ ሰው የአንድ ክልል ምክትል ርዕሰመስተዳድር ናቸው ወይስ የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ› የሚል ጥያቄ ያነሱ ብዙ ነበሩ፡፡በአቶ ጃዋር ላይ ሊደረግ ነበር በተባለው ጉዳይ ምክንያት ቀወስ ሲመጣም፣በተመሳሳይ መልክ መጥተው ‹የፌደራል መንግሥቱን ባለሥልጣናት እንደሚቀጡ ተናገሩ፡፡ግዴለም እኒህ ሰውዬ የሚመሩትን አላወቁትም!

እንግዲህ ለአቶ ሽመልስ የፖለቲከኛነት ልብ እንዲሰጣቸው ከመመኘት ውጭ ሌላ ነገር ማለት ተገቢ አይደለም፡፡

Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top