Connect with us

በአሜሪካ ተጠምዝዛ ኢትዮጵያ እጅ ልትሰጥ?

በአሜሪካ ተጠምዝዛ ኢትዮጵያ እጅ ልትሰጥ?

ማህበራዊ

በአሜሪካ ተጠምዝዛ ኢትዮጵያ እጅ ልትሰጥ?

በአሜሪካ ተጠምዝዛ ኢትዮጵያ እጅ ልትሰጥ? | (በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን)

ትናንት አመሻሽ ሁለት ዜናዎች ተደምጠዋል፡፡ አንደኛው፣‹የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ኤል ሲሲ ጋር ደውለው፣ ስለ ሕዳሴ ግድብ አወሯቸው፤ ድርድሩ በአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ቢሮ ውስጥ ይካሄዳል፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዋሽንግተን ገብቷል›› የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹ግብጽ ከደቡብ ሱዳንና ከኡጋንዳ ጋር በመሆን ሕዳሴ ግድብ እንዳይጠናቀቅ እያሴረች መሆኑን አንድ የኡጋንዳ የደኅንነት ከፍተኛ ባለሙያ ገለፁ›› የሚለው ነው፡፡

ሁለቱም አሳሳቢ ናቸው፡፡ ግብጽ ደጋግማ የጠየቀችውን የሶስተኛ ወገን ያደራድረን ጥያቄ ኢትዮጵያ ከስምንት ዓመታት በኋላ ተስማምታበታለች፡፡ ይህንን ጥያቄ ኢትዮጵያ የተቀበለችው ደግሞ ከሁለት ሳምንታት በፊት በሶች፤ ሩሲያ በተካሄደው የአፍሪቃ-ሩሲያ ጉባኤ ላይ ነው፡፡

በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ‹‹ግብጽና ኢትዮጵያ በጣም ትላለቅ አገራት ስለሆኑ በእነርሱ መካከል የሚፈጠር ችግር አፍሪቃ ላይ አደጋ ያመጣል የሚል ፍራቻ ስላላቸው፣ራሺያን ጨምሮ በርካታ አገራት ጣልቃ መግባት ማወያየት ይፈልጋሉ፡፡ ፖለቲካዊ ውይይቱን ከማንም ጋር ብናደርገው ችግር የለውም››ሲሉ ተደምጠው ነበር፡፡

እዚህ ጋር አስገራሚ ነገር አለ፡፡ ይኸውም ጠቅላይሚኒስትሩ ‹‹ከማንም ጋር ብናደርገው ችግር የለውም› ያሉት በውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ መሪነት እየተደራደረ ያለው የኢትዮጵያን ቡድን የሶስተኛ ወገን አደራዳሪነት አስፈላጊ እንዳልሆነና ኢትዮጵያም እንደማትቀበለው በይፋ ከገለፀ ከአንድ ሳምንት በኋላ መሆኑ ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን አሜሪካ ልታደራድር መወሰኗንና የዓለም ባንክም በአደራዳሪነት እንደሚሰየም ዘገቡ፡፡

ኢትዮጵያ በቀደሙት ሁለት ጠቅላይሚኒስትሮች የሶስተኛ ወገንን አደራዳሪነት ያልተቀበለችበት ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ምክንያቶች አሉ፡፡ በአንድ በኩል እነዚህ የምዕራብ መንግሥታትና ተቋማት ኢትዮጵያ እንዲህ ባሉ ድንበር ዘለል ወንዞች ለይ ልማት እንዳትሠራ አንድ ጊዜ በገንዘብ፣ ሌላ ጊዜ በሰብዓዊ መብትና አካባቢ ጥበቃ እያሳበቡ ጫና ሲያደርሱ የነበሩ ናቸው፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ኢትዮጵያ በተለይ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ እንዳትሠራ ቢያንስ ብር ባለማበደርና ባለመለገስ እንዲተባበሯት ግብጽ ስታቀርብ የነበረችውን ጥያቄ ተቀብለው ሲተገብሩ የኖሩ ናቸው፡፡

 

በተለይ አሜሪካና የዓለም ባንክ ከግብጽ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ያላቸው ናቸው፡፡ የካይሮው መንግሥት በየዓመቱ ከዋሽንግተን እስከ ስድስት ቢሊዮን ዶላር የሚሠጠው (ለጦሩ) እና በመንግሥታት መቀያየር ውስጥ ያልዋዠቀ ወዳጅነት ያለው ነው፡፡በአሜሪካ በሚመደቡ ዋና ዳይሬክተሮች የሚመራው የዓለም ባንክም የዚህ ቅጣይ ነው፡፡ በርካታ ግብፃዊያንን የቀጠረ ብቻ ሳይሆን የባንኩን የአፍሪቃ ተልዕኮ የሚመሩትን (ሃፌዝ ጋሕነም) ግብፃዊ ያደረገ አሜሪካ ሠራሽ ድርጅት ነው፡፡

ግብጽ ለዓመታት በሠራችው ሥራ የግድቡ ፋይናንስ ከውጭ እንዳይገኝ አድርጋለች፡፡ አሁን ደግሞ ሌላ ኃላፊነት ይዛ ተነስታለች፡፡ከሳምንት በፊት Forum for Social Studies ባዘጋጀው መድረክ ላይ ሕሩይ አማኒኤል (ጡረተኛ አምባሳደር) ‹‹ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ገና አላለቀም፡፡ ግድቡ እየተገነባ ያለው በውጭ ኮንትራክተሮችና ኤክስፕርቶች ነው፡፡ ግብጽና የአረብ ሃገራት ተባብረው ከፍተኛ ጫና ቢያደርጉ ፡ እነዚህ ኮንትራክተሮችና ባለሙያዎች ግንባታውን አቋርጠው ወደ ሃገራቸው ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ ይህ የግድቡ ግንባታ ሊያቋርጠው ይችላል፡፡›› ያሉትም ለዚህ ይመስላል፡፡ ቀጣዩ የግብጽ የዲፕሎማሲ ሥራ ምናልባትም እነ አሜሪካንና ዓለም ባንክን በማሳመንና በመጠቀም በግንባታው ላይ ያሉ ኩባንያዎች ጠቅልለው እንዲወጡ ማድረግ ሊሆን ይችላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእነዚህ አማካኝነት ለመደራደር ነው እንግዲህ፣ ካቢኔያቸውንም ሆነ በጉዳዩ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ሳያማክሩ ተስማምተው የመጡት፡፡ ይህም ለዘመናት በግብጽ በኩል ሲጠየቅ የነበረ በመሆኑ ለካይሮ ትልቅ ድል ነው፡፡ ኢትዮጵያን ግን ዋጋ የሚያስከፍላት በብዙ መልኩ ነው፡፡ በአንድ በኩል፣ ‹ሕዳሴ ግድብን በጋራ እናስተዳድረው› የሚለው የግብጽ ሉዓላዊነትን የሚጋፋ እቅድ፣አደራዳሪ ትሆናለች በተባለችው በአሜሪካ በኩል አስቀድሞ አቋም ተይዞበታል፡፡ ከሳምንታት በፊት የወጣው የዋይታውስ መግለጫ ‹በግድቡ አስተዳደር ላይ ተስማሙ› በማለት ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛቷ ውስጥ የሚሠራን ግድብ ግብፃዊያን መጥተው እንዲያስተዳድሩ (Operation)ትፈቅድ ዘንድ አዟል/ጠይቋል፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ባለሙያች በኩል ውድቅ ቢደረግም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተስማምተው ላለመምጣታቸው አስረጅ የለም፡፡

የአባይ ግድብን ለማደናቀፍ ግብጽ ከዩጋንዳ እና ከደቡብ ሱዳን ጋር እየሠራች ነው

የደቡብ ሱዳን የዩጋንዳ እና የግብጽ መሪዎች የአባይ ግድብን ለመደናቀፍ ሌት ተቀን በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን አንድ ዩጋንዳ የቀድሞ የደህንነት ሠራተኛ በብዕር ስም በጻፈው ባለሶስት ገጽ ዶክመንት አጋለጠ፡፡

በሌላ ወገን ግን በሶች የተደረገው ስምምነት፣ በተለይ ሱዳንን የሚያስከፋ ነው፡፡ ከሕዳሴ ግድብ ጅማሮ ማግስት የኢትዮጵያን አቋም ደግፋ የፀናችው ሱዳን፣ በእያንዳንዱ ውሳኔና እንቅስቃሴ ላይ የጋራ የአቋም ስትይዝ ከርማለች፡፡ የሶስተኛ ወገን አደራዳሪን አላስፈላጊነትም ውድቅ ያደረገችው ከኢትዮጵያ ጋር ሆና ነው፡፡ አሁን ግን የኢትዮጵያ ጠቅላይሚኒስትር ሱዳንን ትተው ምዕራባዊያን ያቀረቡላቸውን ጥያቄ ተቀብለው ተመልሰዋል፡፡ ይህ በቀጥታ ሱዳንን ቅር የሚያሰኝ ብቻ ሳይሆን የአፍሪቃን ችግር በአፍሪቃዊያን እንፈታለን ከሚለው የአፍሪቃ ሕብረት አጀንዳም ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹ፖለቲካዊ ውይይቱን ከማንም ጋር ብናደርገው ችግር የለውም› ያሉት ነገር ትልቅ ስህተት የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡ በአንድ በኩል ግብጽ በወንዙ ላይ ከዚህ በኋላ ሌላ ምንም ዓይነት የልማት ሥራ እንዳይሠራ የሚያደርግ ፕሮፖዛል ይዛ ልትቀርብ ትችላለች፤ እስካሁን ያላነሳቻቸውን አጀንዳዎችም ልትመዝ ትችላለች፡፡ ለዚህ ደግሞ ባንኩና አሜሪካ ያግዟት ዘንድ ለዓመታት ስትሰራ ቆይታለች፡፡ እናም ይህ ድርድር በአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስቴቨን ምኑችን ቢሮ ዛሬ እየተካሄ ያለው ድርድርም የማይመጣጠኑ ኃይሎች የሚያደርጉት በመሆኑ ውጤቱን ከወዲሁ ተገማች ያደርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሆይ አምላክሽ ይከተልሽ!

(ማሳሰቢያ፤ ይህ ጽሁፍ ባሳለፍነው ቅዳሜ ከታተመችው ፍትሕ መጽሔት ሀሳቦችን ወስዷል)

Click to comment

More in ማህበራዊ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top