ግብጽ ሱዳን እና ኢትዮጵያ የዛሬ ሳምንት ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓም ስለ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋሽንግተን ዲሲ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እንደሚነጋገሩ ግብጽ አስታወቀች።
የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ «የተራራቁ አመለካከቶችን በማቀራረብ ትክክለኛ እና ፍትሃዊ ስምምነት ላይ እንዲደረስ፣ በየዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት በውይይቱ ላይ በሸምጋይነት እንደሚገኙ ትናንት ከጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ እንዳሉት፣ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ባለፈው መስከረም ከተካሄደው ከተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በተነጋገሩበት ወቅት በግብጽ እና በኢትዮጵያ መካከል በህዳሴ ግድብ ላይ የተፈጠረውን አለመግባባት አሜሪካን እንድትሸመግል ጠይቀው ነበር።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም የገንዘብ ሚኒስትር ስቴቨን ምኑሽን እንዲሸመግሉ ሃሳብ ማቅረባቸውን እኚሁ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ባለሥልጣን መናገራቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ግብጽ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ይህን ስታረጋገጥ ኢትዮጵያ እና ሱዳን በውይይቱ ላይ ለመካፈል ይስማሙ አይስማሙ ግን እስካሁን ግልጽ አይደለም።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ መሳተፍ አለመሳተፏን ሊያረጋግጥልን አልቻለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ ባለፈው ሳምንት ከፓርላማ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት መልስ እና ማብራሪያ ላይ ኢትዮጵያ ምንም ኃይል ኢትዮጵያን ግድቡን ከመሥራት ሊያስቆማት አይችልም ብለው ነበር።
(ምንጭ፡-የጀርመን ድምጽ)