Connect with us

ኢዜማ ጠንካራ መግለጫ አወጣ!

ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሠጠ መግለጫ

ህግና ስርዓት

ኢዜማ ጠንካራ መግለጫ አወጣ!

የኢትዮጵያ ህዝብ ለቀረበለት አገርን የማዳን ጥሪ በሕብረት መልስ መስጠት የሚገባው ወቅት ዛሬ ነው!
ከ #ኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (#ኢዜማ) የተሠጠ መግለጫ

ለኢትዮጵያዊያን የነፃነት፣ እኩልነትና የዴሞክራሲ ጥያቄ የህይወታቸው አካል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ከውጭ ወራሪም ሆነ ከውስጥ አምባገነን አገዛዝ ጋር የሚያደርጉት ትንቅንቅ ዛሬም መቋጫ አላገኘም፡፡ በየምዕራፉ ግን የለውጥ ጮራዎች ብልጭ ድርግም ማለታቸው ህዝባችንን ለሠቀቀን ዳርገውታል፡፡

በዘመናዊት ኢትዮጵያ እንኳን ከአራት በላይ የለውጥ ብልጭታዎች ታሪክ ሆነው አልፈዋል፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ለውጥን ማስተዳደር አለመቻል ዛሬም ትልቁ ፈተናችን ሆኗል፡፡

በሁሉም ዜጎች መስዋዕትነት የተገኙ ድሎችን ወደ ራስ የመጠቅለልና የፖለቲካ ፍላጎትን በኃይል በሌሎች ወገኖች ላይ የመጫን ጉዳይ ዛሬም አይኑን አፍጥጦ እየመጣ ነው፡፡

በርግጥ የአሁኑ አጅግ ዘግናኝ ድርጊት መነሻ ኢትዮጵያዊያን ከተዘራባቸው የዘረኝነት እና የአግላይነት ፖለቲካ ለመላቀቅ የነቁበት እና ወደዜግነት ክብር ለመመለስ አበረታች ርምጃዎችን መውሰድ በመጀመራቸው የተነሳ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡

በተለይም ዜጎች በእኩልነትና በወንድማማችነት መንፈስ መቆማቸውን የተመለከቱ የዘውግ ፖለቲካ ነጋዴዎች ጣዕረ-ሞት ላይ መሆናቸውን በሚያሳይ ሁኔታ ተንፈራግጠዋል፡፡ የዚህም የመጨረሻ ማሳያዎች ለችግሩ የዘርና የእምነት ይዘት ለመስጠት መታተራቸው ነው፡፡

ከነዚህም ጋር የሕዝባቸውን የመልካም አስተዳደር፣ የመሠረተ ልማትና የሥራ ዕድል ጥያቄዎችን መመለስ ያልቻሉ የመንግሥት ሹመኞች ጭምር ይህን የዘር በሽታ እያራገቡ መሆናቸውን እየታዘብን ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ያልተረዱት ዛሬ ደም መፋሰስን ያለማመዱት ወጣት ጥያቄው እስካልተመለሰለት ድረስ ነገም እነሱንም በዚሁ ሁኔታ እንደሚያጠፋቸው ነው፡፡ ዘውግን መሠረት ባደረገ የፖለቲካ ሥርዓት በስሙ የያዙትን ሥልጣን ተጠቅመው ቆምንለት የሚሉትን ማኅበረሰብ ከኖረበት ሲያፈናቅሉት እና ሲዘርፉት እንደቆዩ ጸሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡

የሕዝብን በተለይም የወጣቱን ሁለንተናዊ ደኅንነት እና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመመለስ የሚቻለው ከቀበሌ ጀምሮ፣ በወረዳ፣ በዞንና በክልል እንዲሁም በሀገር አቀፍ በየደረጃው ሕዝብ በነጻነት በመረጣቸውና የተሻለ ሀሳብ ባላቸው መሪዎቹ ሲተዳደርና እውነተኛ ፌደራላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ሲሰፍን ብቻ መሆኑን እናምናለን፡፡ ይህ እንዳይሆን የሚኳትኑ ግለሰቦች ባሳለፍነው ሳምንት በሁለት ቀናት ብቻ ባደረሱት የዜጎችን ሕይወት መቀጠፍ፣ የአካል መጉደልና የንብረት መውደም ተሠማንን የልብ ስብራትና ጥልቅ ሀዘን እየገለፅን በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ያለንን አቋም እናሳውቃለን፡-

1. በተለይም ጥቅምት 13 እና 14 ለደረሰው ጥፋት መነሻ ከሆነው ‹‹ተከብቤያለሁ›› በሚል ለመንግስት አካል ማሳወቅ ሲገባው ወደ ህዝቡ ከረጨው ግለሰብ ጀምሮ በየደረጃው በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ አደጋ ያደረሱ ሰዎች በሙሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ፣

2. ለዜጎች ሞት ደንታ የሌላቸውና በግጭት የሚነግዱ የማኅበራዊ ድረ-ገፅና የተለያዩ የብዙኃን መገናኛዎች ሕዝባችንን ለሌላ ተከታታይ ግጭቶች ከመዳረጋቸው በፊት ሥልጣን በተሠጠው አካል የማስተካከያ ርምጃ እንዲወሰድ፤

3. በችግሩ ምክንያት በየአካባቢው በአሰቃቂ ሁኔታ የተጨፈጨፉ፣ ከቤት ንበረታቸው የተፈናቀሉና ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች ተገቢውን ካሳ እንዲያገኙና በአስቸኳይ ተመልሰው እንዲቋቋሙ፣

4. በአጥፊዎች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ፈፅሞ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት የፀዳ፣ የፀጥታ ኃይሉን ሕዝባዊ ወገንተኝነት ባረጋገጠ መልኩ እንዲሆንና መበቃቀያ እንዳይሆን ጥንቃቄ እንዲደረግ፤ከዚህ ጋር በተያያዘ መንግስትን መቃወምና በህዝብ ድምፅ መቀየር ህጋዊና ተገቢ ተግባር ሲሆን አገርን የማዋረድና የማፍረስ ተግባር ግን ፈፅሞ የተከለከለና የአገር ክህደት ወንጀል በመሆኑ ይህን በሚፈፅሙት ላይ እርምጃ መውሰድ ተገቢ መሆኑን፤

5. እስካሁን ለተፈፀሙት ሕገ ወጥ ተግባራት መንግሥት አስተማሪ ርምጃ ባለመውሰዱ ሕዝብ መንግሥትን ተጠያቂ እያደረገ ይገኛል፡፡ የመንግሥት ኃላፊነቱን አለመወጣት ደግሞ ሕዝቡ ተደራጅቶ ራስን ወደ መከላከል ደመነፍሳዊ ሁኔታ ይገፋዋል፡፡ ይህም ማንም አሸናፊ ወደማይሆንበት እርስበርስ እልቂት ይከተናል፡፡ ይህንን ለመከላከል እንደ ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ የመሳሰሉ ሕጋዊ አረጃጀቶች በአስቸኳይ ማጠናከር እና ሥራ ላይ ማዋል የሚገባ መሆኑን፣

6. በአዳማ፣ በባሌ፣ በምዕራብ አርሲ ዶዶላ፣ በምስራቅ አርሲ፣ በባቱ (ዝዋይ)፣ በኮፈሌ፣ በቢሾፍቱ፣ በሰበታ፣ በአምቦ፣ በሐረርና በሌሎችም የኦሮሚያ ክልል የተፈፀሙ እኩይ ተግባራት ፈፅሞ የኦሮሞን ሕዝብ የማይወክሉና እንዲያውም ሕዝቡ እንዲከፋፈል፣ የሥራ እድል እንዲጠፋና የልማት እንቅስቃሴዎች እንዲስተጓጎሉ በማድረግ ክልሉ ብሎም ሀገር እንዲዳከም ተግተው የሚሰሩ እኩይ ዓላማ ያነገቡ ግለሰቦች አጀንዳ መሆኑን ሁሉም እንዲረዳው፡፡

7. በአጠቃላይ የሀገር መረጋጋት እና ሰላም እንዲሁም ከቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ ባሉ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ውይይት በፍጥነት መጀመር እንዳለበት እናምናለን፡፡ ለዚህም መንግስት ግንባር ቀደሙን ሚና እንዲወጣ እየጠየቅን በእኛ በኩል ለውይይቱ ያለንን ከፍተኛ ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት እንገልጻለን፡፡

8. በዚህ አጋጣሚ በመፈናቀል፣ በድርቅ እና በአንበጣ መንጋ በመመታትና በልዩ ልዩ ችግሮች የተከበቡ ወገኖችን በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ተጠምደን እንዳንዘነጋቸው የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በፍጥነት እንዲደርሱላቸው ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

በመጨረሻም ሕዝቡ በደረሱት ጥቃቶች ማዘኑን፣ መበሳጨቱንና ይህን የሞራል ስብራት ተቀብሎ በዝምታ ለመቀመጥ መቸገሩን ተረድተናል፡፡ ሆኖም በዚህ ዓይነት ሁኔታ መረጋጋትና አስተውሎ መንቀሳቀስ ወሳኝ መሆኑን ለፓርቲያችን አመራር፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና ለሕዝብ አደራ በማለት ከአምባገነናዊ ሥርዓት ለመውጣትና ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሀገር አድርጎ ለማስቀጠል ከሚሹ ወገኖች ሁሉ ጋር በጋራ ለመሥራት ያለንን ዝግጁነት እንገልጻለን፡፡ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ለሀገር በቀል ማኅበራት፣ ለሀገር ሽማግሌዎች፣ ለሃይማኖት አባቶችና ለሌሎችም የማኅበረሰብ መሪዎች የጋራ ሀገር አድን ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ጥቅምት 18 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Click to comment

More in ህግና ስርዓት

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top