Connect with us

“ይች ባቄላ ካደረች ከርማለችና መቆርጠሟን እንጃ!”

"ይች ባቄላ ካደረች ከርማለችና መቆርጠሟን እንጃ!"
Photo: Facebook

ፓለቲካ

“ይች ባቄላ ካደረች ከርማለችና መቆርጠሟን እንጃ!”

“ይች ባቄላ ካደረች ከርማለችና መቆርጠሟን እንጃ!” | አፊላስ አእላፍ

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ያሬድ ኃይለማርያም “መደመር በየአዳራሹ ስትምነሸነሽ፤ መቀናነስ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ዱላ እያማዘዘች ነው”ይልሃል፡፡

ነቃሽ ማጠናከሪያ ብትለው ትላንት በአዲስ አበባ ሁለት ትላልቅ ስብሰባዎች በመንደር ጎረምሶች መደናቀፋቸውን፤ ንብረትም ላይ ጉዳት መድረሱን፤ ወጣቶችም ግራና ቀኝ ተሰልፈው ለዱላ መገባበዛቸውን አስረግጦ ይነግርሃል፡፡

በጥቂት ጽንፈኞች የሚመራው ቡድን ዱላና ገጀራ በመያዝ የአማራ ወጣቶች እና ኢዜማ  (የኢትዮጵያ ዜጎች ማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ) በየበኩላቸው የጠሩትን ስብሰባ በትላንትናው ዕለት መበተኑን ሰምተሃል።

የሃገሪቱን ሰንደቅ አላማ መሬት እንደጣሉና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማም በአማርኛ የተፃፉ ፅሁፎችን እያወረዱ ሲሰብሩና ሲያሰዱ መዋላቸውን በፎቶ ግራፍ የተደገፉ መረጃዎችን በአይንህ በብረቱ አይተሃል፡፡

አዎን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመርን ጽንሰ ሃሳብን ለማስረጽ ሲውተረተሩ፤ ተቀናሽ መንጋዎች ግን እንደ ብረት ቆሎ አንቆረጠም እያሉ ነው!…እናስ የኛ አማራጭ ምንድ ነው?

አዲስ አበባስ ጠባቂዋ ማነው? የሃገሪቱን ፀጥታ እና ደህንነት የሚመራው የመንግስት መዋቅርስ ምን እየሰራ ነው? ቆይማ የህግ የበላይነትን ማስከበር፤ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ አይደለምን?

አልያም ተቀናሽ ጽንፈኛው ሰርክ በሀገሪቱ የሚፈጽመው አንቃዥ ድርጊት ሁሉ ህጋዊ ፍቃድ ተሰጥቶት ከሆነ በግልጽ ይነገረን!
እስከ መቼ ነው ነጻነት ስንል ባርነት፤ ህይወት ስልን ሞት፤ ጀግንነት ስንል ፍርሃት የምንከተበው?!
እኛ ለአዲስ የመደመር ትንሳኤ ስንቃትት ስለምን በተስፋ እጦት ማቀን እንምከን?
እሺ ለማን አቤት እንበል?!

አዎን አልደመር ባዩ ተቀናሽ ጽንፈኛ፤ የዘልማድ ባርነቱ፤ እድፉ በፍቅር አልጸዳ አለ!

ነጻነትን ሲግቱት ሰው ከነሕይወቱ ባደባባይ አቃጠለ! ሰው የተሰኘውን የእግዜር ተአምር ተፈጥሮ ዘቅዝቆ ሰቀለ!…አባቶቹ ያወረሱትን ሰብዓዊ የፍቅር ግለት በውስጡ አክስሎ፤ መንጋነቱን ዛሬም በዱላና በገጀራው አስመሰከረ!
አንተ በጥቂት ጽንፈኞች የምትመራው ቡድን ሆይ እባክን ተለመን!

ከአቀበት ወደ ቁልቁለት በወረድንበት በዚህ የምጥ ዘመን፤ የሰው ጣር እንባ መሻት፤ የሰው ሰቀቀን ማነፍነፍ ምን ይረባሃል?
የዘመኑ የለውጥ ድልድይ መሆን ካቃተህ፤ የዘመኑ አዘቅጥ፤ ናዳ ሆነህ በብዙሃኑ እድል አትደግደግበት!!
አዎን ችግራችን የህግ የበላይነትን አለማስፈናችን ነው!

ህግና ሥርአት ማስከበር ካልቻልን ሀገር ወደ ባሰ ቀውስ እንደምታመራ አለማመናችን ነው!

መንግስት ሆይ “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ መደመሩን ከማስረጽ በፊት፤ ሕግን የማስከበሩ ሥራ ይቅደም እንላለን!
አለበለዚያ “ይች ባቄላ ካደረች ከርማለችና መቆርጠሟን እንጃ!”

(ይህ ፅሁፍ የፀሐፊውን እንጂ የድሬቲዩብን ኤዲቶሪያል አቋም አያሳይም)

Continue Reading
Advertisement News.et Ad
You may also like...
Click to comment

More in ፓለቲካ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top